የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ አክሲዮን ማኅበር ከዲ ኤስ ቲቪ ጋር የገባውን የአምስት ዓመት ውል አስመልክቶ ለጋዜጠኞች መግለጫ ሰጥቷል።
በሸራተን አዲስ ሆቴል በተከናወነው በዚህ መርሐ-ግብር ላይ የሊግ ኩባንያውን ወክለው መቶ አለቃ ፈቃደ ማሞ እና አቶ ክፍሌ ሰይፈ የተገኙ ሲሆን የሊጉን የብሮድካስት እና ስያሜ መብት የገዛው ዲ ኤስ ቲቪን ወክለው ደግሞ አቶ መታሰቢያ እና አቶ ኢዛና ተገኝተዋል። 11:30 ላይም በሁለቱ አካላት መካከል የተደረገውን ስምምነት አስመልክቶ ገለፃ ተደርጓል። በቅድሚያም የአክሲዮን ማኅበሩ የቦርድ ሰብሳቢ መቶ አለቃ ፍቃደ ማሞ ሀሳባቸውን ለጋዜጠኞች ተናግረዋል።
“በቅድሚያ እንኳን ደህና መጣችሁ። እንደምታቁት አክሲዮን ማኅበሩ ከተቋቋመ 1 ዓመት አልሞላውም። ገና መገቢት 7 ላይ ነው በህጋዊነት በአክሲዮንነት የተቋቋምነው። እንደተቋቋምንም የሊጉን ጨዋታዎች በቀጥታ በቴሌቪዥን ለማስተላለፍ እና ስያሜውን ለመሸጥ እንቅስቃሴ ጀምረን ነበር። በዚህም ጨረታ አውጥተን አሸናፊዎችን ስንጠባበቅ ነበር። በወጣው ጨረታም የኢትዮጵያ ብሮድካስቲን ኮርፖሬሽን (EBC)፣ Canal plus እና Dstv ጨረታውን ለማሸነፍ ተወዳድረው ነበር። ተወዳዳሪዎቹ ባቀረቡት የፋይናንሻል እና ቴክኒካል ፕሮፖዛል መሠረትም Dstv ጨረታውን አሸብፏል። በዚህም ተቋሙ በየዓመቱ በ250 ሺ በሚያድግ ገንዘብ ከ4 ሚሊዮን ጀምሮ እስከ 5 ሚሊዮን ዶላር ድረስ ገንዘብ ለመክፈል ለአምስት ዓመት ተስማምቷል። በአጠቃላይ 68 ሚሊዮን ዶላር ወጪ ለማድረግ ተስማምቷል።
“መልቲ ቾይዝ ኢትዮጵያ ይህንን ስምምነት ለማድረግ 57 ገፅ የያዘ ዝርዝር ውል ተዘጋጅቷል። በተዘጋጀው ውል ላይም በተደጋጋሚ በመገናኘት ውይይቶችን አድርገናል። እስከ ዛሬ ማለዳ ድረስም ድርድር አድርገናል።
“ይህ ስምምነት ከዳር እንዲደርስ የረዱትን ሰዎች ማመስገን እፈልጋለሁ። በቅድሚያ የህግ ጠበቃ ባለሙያ የሆኑት አቶ ሚሊዮን ጉዳዩን እንደ ባለቤት ይዘው ሲደራደሩ ነበር። በተጨማሪም የቅዱስ ጊዮርጊስ የቦርድ አባል አቶ ንዋይ ከመጀመሪያው ጊዜ ጀምሮ እስከ መጨረሻው ሲረዱን ነበር። በዚህም በራሴ እና በ16ቱ የሊጉ ክለቦች ስም ምስጋና ማቅረብ እፈልጋለው።”
የሊጉ አክሲዮን ማኅበር የቦርድ ሰብሳቢ ይህንን ሀሳብ ከተናገሩ በኋላ የመልቲ ቾይዝ ኢትዮጵያ ምክትል ስራ አስኪያጅ የሆኑት አቶ መታሰቢያ ተከታዩን ብለዋል።
“መልቲ ቾይዝ ኢትዮጵያ የተለያዩ የመዝናኛ አማራጮችን ለሀገራችን ህዝቦች ሲያቀርብ ነበር። በተለይ ዓለም ላይ ያሉ የስፖርት ውድድሮችን ለዓመታት ለስፖርት ቤተሰቡ ሲያደርስ ነበር። አሁንም የዋናውን ሊግ ለማገዝ መጥቷል።
“ዲ ኤስ ቲቪ ወደ ሀገራችን መምጣቱ ለስፖርቱ እና ለሀገራችን አጠቃላይ ገፅታ በጣም መልካም ነው። ለዚህ ታሪካዊ ቀንም መድረሳችን በጣም ደስ የሚያሰኝ ነው።”
አቶ መታሰቢያ አጭሩን መልዕክታቸውን በስፍራው ለተገኙ ሰዎች ካጋሩ በኋላ በጋዜጠኞች የተለያዩ ጥያቄዎች ተነስተው ምላሾች መሰጠት ተጀምሯል።
የሊጉ ስያሜን በተመለከተ
የሊጉ የስያሜ መብት በዲ ኤስ ቲቪ ተወስዷል። ዲ ኤስ ቲቪም ከአጋር ድርጅቱ ጋር በመሆን የሊጉን ስያሜ በቤት-ኪንግ እንዲሰየም ፈቅዷል። ስለዚህ የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ የቤት ኪንግ የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ በሚል ይሰየማል።
በቀጥታ የሚተላለፉ ጨዋታዎችን በተመለከተ
በቀጥታ የሚተላለፉት ጨዋታዎች 60 ጨዋታዎች ናቸው። እርግጥ ተቀርፆ ነገርግን በቀጥታ የማይተላለፉ ጨዋታዎች አሉ። ግን አነዚህ ጨዋታዎች በቀጣታ ሳይሆን ዘጎይተው እንዲተላለፉ ይደረጋል። ይህ ብቻ ሳይሆን ጭራሽ የማይቀዱም ጨዋታዎች አሉ። ይህ በተቋሙ የሚወሰን ነው። ግን በቀጥታ የሚተላለፉትም ሆነ የማይተላለፉት ጨዋታዎችን ክለቦች እንዲያገኙ እናደርጋለን።
ጨዋታዎችን ስንት ካሜራ ይቀርፃል?
ቢያንስ ስድስት ካሜራ አንድን ጨዋታ እንዲቀርፅ ይደረጋል። ግን በዋናነት ጥሩ ፕሮዳክሽን እንዲኖር ተስማምተናል። በተለይ ደግሞ ከደቡብ አፍሪካ ጋር የሚመጣጠን ጥራት እንዲኖረው ተነጋግረናል። ይህንንም ለማድረግ ባለሙያዎችን ከውጪ አስመጥተናል።
ክፍያን በተመለከተ?
በየዓመቱ የሚኖረው ክፍያ በሁለት ጊዜ እንዲኖር ተነጋግረናል። 50% መስከረም ወር ላይ ሆኖ ሁለተኛው ደግሞ በዓመቱ መገባደጃ ላይ እንዲሆን ተስማምተናል። የዘንድሮ ደግሞ ታህሳስ 1 እና ሚያዝያ ላይ እንዲፈፀም ተማምነናል።
ደጋፊዎችን በተመለከተ?
ደጋፊዎችን በተመለከተ ምንም አዲስ ነገር የለም። እስካሁን ከመንግስት ደጋፊዎችን እንድናስገባ የመጣልን ነገር የለም። ወደፊት አላውቅም።
ዲ ኤስ ቲቪ ሊጉን መግዛቱ ምን ጥቅም ይሠጣል?
ዲ ኤስ ቲቪ የኢትዮጵያን እግርኳስ ሲያስተላልፍ የተለያዩ ጥቅሞችን ያገኛል። ዋናኛው ጥቅም ሊጉ ዝና እንዲያገኝ ማደረጋችን ነው። ሁለተኛ ደግሞ ለደጋፊዎች መድረሳችን ነው። በተለይ ደጋፊዎች ስታዲየም እንዳይገቡ በተደረገሸት ጊዜ መቅረባችን ትልቅ ነገር ነው። ሦስተኛ ለተጫዋቾቻችን የሚሰጠው ጥቅም ነው። ከምንም በላይ ተጫዋቾቻችን እንዲታዩ ማድረጉ ትልቅ ጥቅም ነው። በአጠቃላይ ግን የሀገራችንን ገፅታ የሚያሳድግ መሆኑ ትልቅ ጥቅም ይሰጣል።
መግለጫው ከተሰጠ በኋላ በሸራተን አዲስ ቅጥር ግቢ ውስጥ የእንኳን ደስ አላችሁ መርሐ-ግብር ተዘጋጅቷል። በዝግጅቱ ላይም ሁለቱ አካላት የስምምነት ፊርማቸውን በይፋ ፈፅመዋል። ይፋዊ ስምምነቱ ከተከናወነ በኋላም በተለያዩ የእግርኳስ ባለሙያዎች መሪነት የፓናል ውይይት ተደርጓል። 11:30 የጀመረው ዝግጅትም 3:30 ላይ ተገባዷል።
© ሶከር ኢትዮጵያ