በመቐለ 70 እንደርታ፣ ወልዋሎ ዓ/ዩ እና ስሑል ሽረ የሚገኙ ተጫዋቾችን የተመለከተ አዲስ የዝውውር ደንብ መውጣቱ ታውቋል።
እንደ ስሑል ሽረ ሁሉ በ2013 የቤትኪንግ የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ የመሳተፋቸው ነገር ያከተመ የሚመስለው መቐለ 70 እንድርታ እና ወልዋሎ ዓ/ዩ የያዟቸው ተጫዋቾችን በተመለከተ የተለያዩ ጥያቄዎች ሲነሱ ሰንብቷል። በተለይ ክለቦቹ በሊጉ የማይሳተፉ ከሆነ የተጫዋቾቹ ቀጣይ ህይወት አጣብቂኝ ውስጥ እንደሚገባ ከተለያዩ አካላት ሲገለፅ ነበር። እርግጥ የመቐለ 70 እንደርታ 11፣ የወልዋሎ ዓ/ዩ 4 እንዲሁም የስሑል ሽረ 16 ተጫዋቾች ከሰሜኑ የሀገሪቱ ክፍል ወደ መሐል ሀገር መምጣታቸው ቢታወቅም ሌሎቹ ተጨዋቾች ግን እስካሁን ከክለቦቹ መቀመጫ ከተማ እንዳልወጡ ተጠቁሟል።
ብዙዎች እንደሚገምቱት ክለቦቹ በውድድር ላይ የማይሳተፉ ከሆነ በስራቸው የያዟቸው ተጫዋቾች መደበኛ ስራቸውን በልዩ ሁኔታ እንዲከውኑ የሚያደርግ ህግ እንዲወጣ ሲጠየቅ ነበር። ይህንን ተከትሎም እሁድ በነበረው የኢትዮጵያ እግርኳስ ፌዴሬሽን 12ኛ መደበኛ ጠቅላላ ጉባኤ ላይ የፌዴሬሽኑ ፕሬዝዳንት አቶ ኢሳይያስ ጂራ በክለቦቹ የሚገኙ ተጫዋቾች እና አሰልጣኞች ስራ መሰራት ስላለባቸው ክለብ የሚያገኙ ከሆነ ቢዘዋወሩ የሚል ውሳኔ እንደተወሰ ሲገልፁ ነበር። በተወሰነው ውሳኔ መሠረትም ፌዴሬሽኑ በእነዚህ ሦስት ክለቦች ብቻ የሚገኙ ተጫዋቾች የሚስተናገዱበት እና ለአንድ ዓመት ብቻ ክፍት የሆነ የአንደኛና ሁለተኛ ዙር የዝውውር ጊዜ የሚመራበት ደንብ በልዩ ሁኔታ አዘጋጅቶ ጨርሷል።
ይህ ደንብ ለዘንድሮ ዓመት ብቻ የሚሰራ ሲሆን አንድ ዓመት ውል ከክለቦቹ (ከትግራይ ክለቦች) ጋር ያለው ተጫዋች ግን በ2014 በክለቦቹ ፍቃደኝነት ተመልሶ ያለውን ውል እንዲጨርስ ይደረጋል። የቀድሞ ክለቡ ካልፈለገው ግን በዛው ወደ ሌላ ክለብ መጓዝ እንደሚችል ተጠቁሟል።
©ሶከር ኢትዮጵያ