በ17 ዓመት በታች ቡድኑ ዝግጅት ዙሪያ መግለጫ ተሰጥቷል

ዛሬ ከቀትር በኋላ በፌዴሬሽኑ ፅህፈት ቤት የሴካፋ ተካፋይ በሆነው ታዳጊ ቡድን ዙሪያ ገለፃ ተደርጓል።

ኢትዮጵያ ከታህሳስ 03-13 ድረስ በሩዋንዳ አስተናጋጅነት የሚከናወነው የምስራቅ አፍሪካ ከ17 ዓመት በታች ውድድር ላይ ተሳታፊ ናት። ውድድሩ ከክፍለ አህጉር ውድድርነት ባለፈ በዕድሜ መደቡ በሞሮኮ ለሚዘጋጀው አፍሪካ ዋንጫ ለመካፈልም እንደማጣሪያነት ያገለግላል። ከዩጋንዳ ፣ ኬኒያ እና ደቡብ ሱዳን ጋር የተመደበው የኢትዮጵያ ከ17 ዓመት በታች ብሔራዊ ቡድንም በአሰልጣኝ እንድሪያስ ብርሀኑ እየተመራ ልምምዱን ሲያካሂድ ቆይቷል። ይህን የዝግጅት ጊዜን የተመለከተው መግለጫም ዛሬ በፌዴሬሽኑ ፅህፈት ቤት በአቶ ዳንኤል እና በአሰልጣኝ እንድሪያስ አማካይነት ተሰጥቷል።

በመግለጫው በከባድ የምርጫ እና የዝግጅት ጊዜ ውስጥ ባለፉት ጊዜያት የተለያዩ ክለቦች ፣ አካዳሚዎች ፣ ፕሮጀክቶች እንዲሁም አዲስ አበባ እና በክልሎች ለሚገኙ የማዘውተሪያ ስፍራዎች ውጤት ለሆኑ ታዳጊዎች ትክክለኛውን ዕድሜ ከግምት ውስጥ ባስገባ መልኩ ዕድሉን በመስጠት ምርጫው ተከናውኗል። ለምርጫው ከሰባት መቶ እስከ ስምንት መቶ የሚሆኑ ታዳጊዎች ቢመጡም ከኮቪድ 19 እና ከሜዳ እጦት ጋር በተያያዘ የማጥራት ስራው ከባድ እንደናበር አሰልጣኝ እንድሪያስ ገልፀዋል።

ከምርጫውም በኋላ በዕድሜ እና በህክምና ምርመራዎች የተወሰኑ ተጫዋቾች ከምርጫ ውጪ በመሆናቸው የመጨረሻው የቡድን ስብስብ ላይ ለመድራስ ሁለተኛ እና ሦስተኛ ዕቅድ ማውጣትም አስፈልጎ ነበር። በቀን ሁለት ጊዜ ይሰጥ በነበረው ልምምድም ታዳጊዎቹ በኮቪድ 19 ምክንያት በነፃነት ከቤት ወጥተው ለመስራት ፍቃድ ያጡ የነበረ መሆኑ እንደተግዳሮት ተጠቅሷል።

የብሔራዊ ቡድኑ አባላት የኮቪድ ምርመራ ያደረጉ ቢሆንም በተመሳሳይ ምርመራ ያከናወነ ቡድን ማግኘት አዳጋች በመሆኑ ከመከላከያ ቡድን ጋር ብቻ የወዳጅነት ጨዋታ ያደረጉ መሆኑን የገለፁት አሰልጣኙ ከውድድሩ መልስ ቡድኑ ልምድ አካብቶ እንዲመጣ እና እንደከዚህ ቀደሙ ከመበተን ይልቅ ቀጣይ ስራዎች ተስርተው የሚያድግ ቡድን እንዲሆን ከበላዮቻቸው ጋር ለመስራት እንደሚጥሩ ገልፀዋል።

አሰልጣኙ ከላይ የተጠቀሱትን ሀሳቦች አብራርተው ከጨረሱ በኋላ ከጋዜጠኞች ለተነሱላቸው ጥያቄዎች ቀጣዮቹን መልሶች ሰጥተዋል።

ስለምርጫው ሂደት…

ኮንትራት የፈረምኩት ጥቅምት 23 ነበር። ከዚያ በኋላ ነው ወደ ምርጫ የገባነው። ታዳጊዎቹን በአንድ ቦታ መሰብሰብ የማይቻል ስለነበር በሰዓት ከፋፍለን በቡድን በመለያየት ከ15 እስከ 20 ተጫዋቾች በማድረግ ከለሊት 10:30 ጀምረን በመነሳት ከጤና ቢሮዎች መግቢያ ሰዓት ጋርም በመናበብ ነው ምርጫውን ያከናወንነው። እስከ ምሽት 12 ሰዓት ድረስም የሚያቆይ ምርጫ ነበር። የመጨረሻውን ምርጫ በአዲስ አበባ ስታዲየም እና በካፍ የልህቀት ማኅከል አድርገናል።

ስለኮቪድ ተፅዕኖ…

ከመጡት ተጫዋቾች ብዛት አንፃር እና ከኮቪድ ምርመራም አንፃር ምርጫው እጅም ጊዜ ወስዷል። በቀን ሁለት ጊዜ የመጨረሻ ልምምድ የነበረን ወደ 20 ለሚጠጉ ቀናት ነበር። ይህን ማድረግ በተጫዋቾች ያልተለመደ ጫና መሆኑ ሊከብዳቸው ቢችልም የተሻለ ዝግጅት ማድረግ ስለነበረብን በዚህ መንገድ ሄደናል።

ስለሚጠበቀው ውጤት…

ምንም ዓይነት ልምድ የሌላቸው ታዳጊዎች ናቸው። በመሆኑም የተቻለንን ያህል ተፎካካሪ ሆነን ለመምጣት ነው የምናስበው። በዚህ ቡድን ላይ ተመስርቶ ቀጣዩ የዕድሜ ዕርከን ላይ ለመስራት ግን አመራሮቻችም ሊያግዙን ይገባል።

ከ20 ዓመት በታች ቡድኑ ስለተገኘው ልምድ…

ከ20 ዓመት በታች ቡድን ጨዋታዎች ላይ እንዳየነው ተጫዋቾቻችን ኳሶች እንዳይሻሙ ለማድረግ እንዲችሉ ባለን ትንሽ ጊዜም ቢሆን ለመዘጋጀት ሞክረናል።

ስለመጨረሻው የቡድን ስብስብ

ሦስት ግብ ጠባቂዎች እና አስራ ሰባት የሜዳ ተጫዋቾች ተመርጠዋል። ከጉዳት እና ከሌሎች ነገሮች ጋር በተያያዘ ችግር እንዳይገጥመን በአመዛኙ ብዙ ቦታዎች ላይ መጫወት የሚሉ ተጫዋቾችን ለመያዥ ሞክረናል።


© ሶከር ኢትዮጵያ