“አሰልጣኝ አምኖብኝ የሰጠኝን ዕድል ተጠቅሜ ስኬታማ ሆኜ መውጣቴ የበለጠ እንድሰራ ያደርገኛል” ፋሲል ገብረሚካኤል

በቤትኪንግ የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ የመጀመሪያው ጨዋታ በሰበታ እና ድሬዳዋ መካከል ያለግብ መጠናቀቁ ይታወቃል። ይህን ተከትሎ በጨዋታው ጥሩ ከተንቀሳቀሰው የሰበታው ግብጠባቂ ፋሲል ገብረሚካኤል ጋር ቆይታ አድርገናል።

በዳሽን ቢራ ተስፋ ቡድን የግብጠባቂነት ህይወቱን የጀመረው ፋሲል በ2008 በአሰልጣኝ አጥናፉ በሚመራው ከ17 ዓመት በታች ብሔራዊ ቡድን ውስጥ የቡድኑ አባል ነበር። በየጊዜው እድገቱ እየጨመረ አቅሙ ከፍ እያለ የመጣው ፋሲል በ2010 በደደቢት ቆይታ ካደረገ በኃላ ነው ዓምና ሰበታዎችን በመቀላቀል የመጫወት ዕድል ባገኘባቸው አጋጣሚዎች ሁሉ ተስፋ ሰጪ ነገር ሲያስመለክተን ቆይቷል። ሶከር ኢትዮጵያ ይህን እድገቱን ከግምት በማስገባት በተስፋኛ አምዳችን እንግዳ አድርጋው እንደነበረ ይታወቃል።

በዛሬው የሰበታ ከ ድሬዳዋ ጋር አቻ በተለያዩበት ጨዋታ ላይ አሰልጣኝ አብርሀም መብራቱ ለዚህ ተስፈኛ ወጣት የመጫወት እድል በመስጠት ግልፅ የጎል አጋጣሚዎችን ከማምከኑ ባሻገር አንድ ፍፁም ቅጣት ምት በማዳን የጨዋታው ኮከብ ሆኖ ማጠናቀቅ ችሏል። ይህን ተከትሎ ሶከር ኢርዮጵያ ከዚህ ተስፋኛ ወጣት ግብጠባቂ ጋር ከጨዋታው መጠናቀቅ በኃላ አጭር ቆይታ አድርጋለች።

“የፕሪምየር ሊግ የመጀመርያ ጨዋታን መጫወት በጣም ነው ደስ የሚለው። አሰልጣኝህ አምኖብህ በመጀመርያ ጨዋታ ላይ መሰለፍ ስኬታማ መሆን በጣም ያስደስታል። ሁሌም በስራህ በራስ መተማመንህ እንዲዳብር ያደርጋል። እኔም ከፈጣሪ ጋር በጨዋታው የምችለውን አድርጌ፣ ፍፁም ቅጣት ምት አድኜ በመውጣቴ በጣም አስደስቶኛል። ከበፊት ጀምሮ ፍፁም ቅጣት ምቶች ሲነቱ እና ግብጠባቂዎችን አቋቋማቸውን እመለከት ነበር። በተደጋጋሚ በልምምድ ወቅት ፍፁም ቅጣት ምት መቺዎች ጠንካራ ምቶቻቸውን ወይም ለበረኛ የሚከብዱ ቦታዎች የትኞቹ ናቸው የሚለውን አቅጣጫ ጠብቄ መሄድ እንዳለብኝ ልምምድ እሰራ ነበር። ለዛም ነው እንዳሰብኩት በሄድኩበት መታው ፍፁም ቅጣት ምቱን ለማዳን ቻልኩኝ። ይህ ገና ጅማሬዬ ነው። ከዚህ በኃላ ብዙ የሚቀሩኝ የማሻሽላቸው የቤት ስራዎች አሉኝ። ጠንክሬ በመስራት ወደ ፊት ክለቤን በሚገባ ማገልገል እፈልጋለው። ከዚህ በተጨማሪ የሁሉም ተጫዋች የሚመኘውን የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን በመጫወት ሀገሬን ማገልገል እፈልጋለው። ለዚህም ፈጣሪ ይረዳኛል ብዬ ተስፋ አደርጋለው።”

ከጨዋታው መጠናቀቅ በኃላ አሰልጣኝ አብርሀም መብራቱ ፋሲል ገብረሚካኤል የተባገሩት ሀሳብ ይህ ነበር።

“ደጋግሜ የምናገረው ነገር ነው። ለሀገራችን ግብ ጠባቂዎች ተገቢውን ሥልጠና ከሰጠናቸው እና ዕምነት ከጣልንባቸው የሚፈለገውን አገልግሎት መስጠት ይችላሉ። ፋሲል አዲስ ነው ፤ ገና ወጣት ነው። ለእኔ ግን የጨዋታው ኮከብ እሱ ነበር ማለት እችላለሁ። ቁም ነገሩ ተገቢውን ሥልጠና እና ዕድል መስጠት ላይ ነው። ያ ከሆነ ጥቅሙ ለክለቡ ብቻ ሳይሆን የግብ ጠባቂ ችግር ላለባት ሀገራችንም ጭምር ነው።”


© ሶከር ኢትዮጵያ