ነገ 09፡00 ላይ የሚደረገውን የጅማ እና አዳማ ጨዋታን የተመለከቱ ሀሳቦችን እንዲህ አሰናድተንላችኋል።
ይህ ጨዋታ ዘንድሮ በምን ዓይነት መልክ ሊቀርቡ እንደሚችሉ ለመገመት የሚከብዱ ቡድኖች የሚገናኙበት ነው ማለት ይቻላል። በተለይም የጅማ አባ ጅፋር የውድድር ዝግጁነት ብዙ ጥያቄ የሚነሳበት ሆኗል። እጅግ ጥቂት የሚባል የቅድመ ውድድር የዝግጅት ጊዜ የነበረው ጅማ አባ ጅፋር ወደ አዲስ አበባ ከመጣም ጥቂት ቀናት ብቻ ናቸው የተቆጠሩት። ከዚህም በላይ ክለቡ ከቀድሞው ግብ ጠባቂው ዳንኤል አጃዬ ጋር የነበረው ውዝግብ በፊፋ የዝውውር እገዳ እንዲጣልበት ማድረጉ እና ከእግዱ ጋሮ የተያያዙት ጉዳዮች እስካሁን ባለመፈታታቸው የሊጉን አጀማመር ከባድ ያደርግበታል። እስከነገ ድረስ የሚፈጠር አዲስ ነገር የማይኖር ከሆነም አባ ጅፋር እንዲጫወቱለት የተስማማቸውን አዳዲስ ተጫዋቾች የመጠቀም ዕድል አይኖረውም። በተለይም በቡድኑ ውስጥ ያሉት ግብ ጠባቂዎች በሙሉ አዲስ መሆናቸው እና ምንም ነባር ግብ ጠባቂ አለመያዙ የአዳማውን ጨዋታ ይበልጥ ውስብስብ ያደርገዋል። በቡድኑ ውስጥ ኮንትራት ኖሯቸው የቀሩ 15 ተጫዋቾችን ብቻ የመጠቀም ግዴታው ለአሰልጣኝ ጻውሎስ ጌታቸው ከባድ የቤት ሥራ እንደሚሆንም ይታሰባል።
በአሰልጣኝ አስቻለው ኃይለሚካኤል እየተመራ ከአንድ ወር በፊት የቅድመ ውድድር ዘመን ዝግጅቱን የጀመረው አዳማ ከተማ እንደከነዓን ማርክነህ እና በረከት ደስታ የመሳሰሉ ያለፉት ዓመታትን የቡድኑን ይዘት የሚገልፁ ተጫዋቾች ጋር መለያየቱ ‘ምን ዓይነት መልክ ኖሮት ይመጣ ይሆን ?’ እንዲባልለት ያደርጋል። ታሪክ ጌትነት ፣ ደሳለኝ ደባሽ ፣ ደስታ ጌቻሞ ፣ በቃሉ ገነነ ፣ ትዕግስቱ አበራ ፣ ታፈሰ ሰረካ ፣ አክሊሉ ተፈራ ፣ ወንድይፍራው ጌታሁን ፣ ቴዎድሮስ ገብረእግዚአብሔር ፣ አካሉ አበራ እና ሌሎች ተጫዋቾችንም ያስፈረመው አዳማ ለቀድሞው ምክትል አሰልጣኙ ኃላፊነት መስጠቱ እና አዳዲስ ተጫዋቾች ከአዲስ መጤ አሰልጣኝ ጋር እንዳይገናኙ ማድረጉ ሲታይ ደግሞ የሚኖረው ለውጥ ምንአልባትም ስር ነቀል ላይሆን እንደሚችል ያመላክታል። በጥቅሉ ግን 2010 ላይ ለዋንጫ እስከመፎካከር ደርሶ የነበረው ቡድኑ ቁልፍ ተጫዋቾች ቀስ በቀስ በአመዛኙ በመልቀቃቸው ክለቡ ሌላ ለተከታታይ ዓመታት ዕድገቱን ጠብቆ የሚሄድ ቡድን የመገንባት ፈተና ይጠብቀዋል። አዳማ ከተማ በነገው ጨዋታ የመስመር ተከላካዩ ሱለይማን መሀመድን ግልጋሎት አያገኝም። ከዚህ በተጨማሪ አሁን በደረሰን መረጃ አዳማ ከከፍተኛ ሊግ ካስፈረማቸው የተወሰኑ ተጫዋቾች ጋር መለያየቱ ተሰምቷል።
እርስ በርስ ግንኙነት
– ሁለቱ ቡድኖች በሊጉ ለአራት ጊዜያት ተገናኝተው ጅማ ሁለት ጊዜ በማሸነፍ ቀዳሚው ሲሆን ሁለት ጊዜ አቻ ተለያይተዋል። አዳማ እስካሁን ጅማ ላይ ድል ማስመዝገብ አልቻለም።
– በአራቱ ግንኙነቶች ጅማ 8 ሲያስቆጥር፤ አዳማ 1 ብቻ አስቆጥሯል።
© ሶከር ኢትዮጵያ