በመጀመሪያው ሳምንት የሊጉ ሦስተኛ ጨዋታ ቡና እና ወልቂጤ 2-2 ሲለያዩ አሰልጣኞቻቸው ከሱፐር ስፖርት ጋር ተከታዩን ቆይታ አድርገዋል።
አሳልጣኝ ካሳዬ አራጌ – ኢትዮጵያ ቡና
ስለ ጨዋታው…
“የመጀመሪያ ጨዋታ ስለሆነ ነፃ ሆኖ ያለመጫወት ነገር ተጫዋቾች ላይ ይታይ ነበር። ጥንቃቄ የበዛበት ጨዋታ ነበር ፤ እንደዛም ሆኖ ግን የተሻሉ ዕድሎችን መፍጠር ችለን ነበር ፤ እነዛን ወደ ጎል መቀየር አልቻልንም። የገቡብን ጎሎች ላይ ሳይሆን የምንሄዳቸውን ኳሶች ውጤታማ ማድረግ ቢቻል ውጤቱን መቀየር ይቻል ነበር ብዬ አስባለሁ። ያ ነው መቋረጥም የሌለበት። እንደዚህ ዓይነት ክፍተቶች ሊፈጠሩ ይችላሉ። እነዚህን ክፍተቶች ተጋጣሚ እንዳይጠቀም ዕድሎች በቀላሉ እንዳይባክኑ ማድረግ ይኖርብናል።”
የጎል ዕድል ለመፍጠር ከአቡበከር ውጪ ሌሎች ተጫዋቾችን የመጠቀም ድክመት ስለመኖሩ…
“የለም። ምክንያቱም አቡበከር እነዛን ዕድሎች ያገኘው በሌሎቹ የቦታ አያያዝ ነው። ስለዚህ በቡድናችን ውስጥ የምናስበው እያንዳንዱ ተጫዋች ሂደቱን የሚጠብቅ ፣ ለመጨረሻ ኳስ ራሱን የሚያዘጋጅ ፣ የመጨረሻ ኳስ የሚሰጥ እንዲሆን ነው። እንደአንድ ተጫዋች አይደለም የምናስበው። ሌሎቹ በሚፈጥሩት ዕድል ውስጥ አንድ ተጫዋች ተደጋጋሚ ዕድል ሊያገኝ ይችላል።”
ስለወልቂጤ ከተማ ሁለተኛ አጋማሽ ወደ ጨዋታ መመለስ
“ሲጀመርም ለመጫወት ይሞክሩ ነበር ፤ ብዙ አልቀጠሉበትም። ብዙ ጊዜ መጠቀም የሚፈልጉት እኛ በምንከፍተው ቦታ ላይ ፊት ላይ ባላቸው ፈጣን ተጫዋች ለመጠቀም ነበር ፤ ያንን አስበንበት ነበር።”
ስለቀጣይ ዕቅድ…
“ጨዋታውን በተመለከተ አሁን ያየናቸውን ክፍተቶች የማየት ዕድል ስለሚኖረን እነዛን ስህተቶች እያረምን የተሻለ ውጤት ይዞ ለመውጣት ነው የምናስበው።”
አሰልጣኝ ደግአረገ ይግዛው – ወልቂጤ ከተማ
ስለጨዋታው…
“ቡናዎች ኳሱን ይዞ በመጫወት ረገድ የተሻለ እንቅስቃሴ ያሳዩበት ነበር ፤ በተለይም በመጀመሪያው አጋማሽ። እኛም በጋራ በመደራጀት የእነሱን የኳስ ቁጥጥር ለማክሸፍ ጫና አድርገን ለመጫወት እየሞከርን ነበር። ባሰብነው ልክ ሄዶልናል ብለን አላሰብንም። ሆኖም ግን እንደጨዋታው እንቅስቃሴ በመጀመሪያው አጋማሽ ጎሎችን ያስተናገድን ቢሆንም በሁለተኛው የተሻለ ለመንቀሳቀስ ሞክረናል። ኳስ የሚይዙ ተጫዋቾችንም ለማስግባት ሞክረናል ፤ ይህም ተሳክቶልን ውጤቱን መቀየር ችለናል።”
ስለ በኃይሉ ተሻገር እና ያሬድ ታደሰ ቅያሪ
“የመጀመሪያው አጋማሽ ስህተቶቻችንን ለማረም ብዙ ዕቅዶች ይዘን ነው ከተጫዋቾች ጋር የተነጋገርነው። ሆኖም ግን ብልጫ ይወሰድብን የነበረው መሀል ሜዳ ላይ ኳስን በነፃነት እንፈቅድላቸው ስለነበር ነው። ያንን ለመቆጣጠር የመስመር አጥቂ ቀንሰን የአማካይነት ባህሪ ያለውን ያሬድን ለማስገባት ሞክረናል። በተወሰነ መልኩ ተሳክቶልናል ብዬ አስባለሁ። ነገር ግን ብዙ የሚቀሩን ነገሮች እንዳሉ ጨዋታው አሳይቶናል። ከዕረፍት መልስ ተጫዋቾች ወደ ጎል ለመቅረብ የነበራቸው ተነሳሽነት ጥሩ ነበር። በመጀመሪያው አጋማሽም ከእነሱ የተሻለ የጎል ዕድሎችን መፍጠር ችለናል። አጨራረሳችን በምንፈልገው ልክ ባለመሆኑ ተመርተን ለመውጣት ተገደናል። በሁለተኛው አጋማሽ ያስገባናቸው ተጫዋቾች በተወሰነ መልኩ ጨዋታውን ለመቀየር ጥረት አድርገዋል ፤ ይሄም ተሳክቶልናል ብዬ ነው የማስበው።”
ስለቀጣይ ጨዋታዎች…
“ይህ ጨዋታ ለኛ የማንቂያ ጨዋታ ነው፡፡ ለውድድሩ በምን ያህል መጠን መዘጋጀት እንዳለብን ያየንበት ነው፡፡ በመጀመርያው አጋማሽ በጉልህ ይታይ የነበረው የኛ ድክመት ጨዋታውን ተቆጣጥረን ማሸነፍ እንደምንችል በራሳችን ዕምነት አልነበረንም ነበር፡፡ በዚህም በጣም አፈግፍገን በነፃነት እንዲጫወቱ ዕድል ሰጥተናቸው ነበር፡፡ የዛሬው ጨዋታ ብዙ ነገር አሳይቶናል፡፡ በአካልም በአዕምሮም ዝግጁ ለመሆን እንጥራለን፡፡”
ስለረመዳን ናስር ብቃት…
“ጎል ማስቆጠሩ ብቻ ሳይሆን ተጨማሪ ጎል የሚሆን ዕድል ፈጥሮ ነበር፡፡ ኢነርጄቲክ ነው ፤ በማጥቃትም በመከላከልም ጥሩ እና ንቁ ነበር፡፡ እኛም መስመሩን ለመጠቀም አስበን ነው የገባነው፡፡ ያሰብነውም ስኬታማ ነበር፡፡ ይህንን በቀጣይ ጨዋታዎችም መደጋገም ነው የሚጠበቅብን፡፡ በአጠቃላይ ተጨዋቾቼ ከመመራት ተነስተው ውጤት ይዘው ለመውጣት ያደረጉት ጥረት መልካም ነበር፡፡ ምን ያህል የአዕምሮ ጥንካሬ እንዳላቸውም ያየንበት ነው፡፡”
© ሶከር ኢትዮጵያ