ወላይታ ድቻ እና ሀዲያ ሆሳዕና ጨዋታን መጠናቀቅ ተከትሎ የቡድኖቹ አሰልጣኞች ከሱፐር ስፖርት ጋር ቀጣዩን ቆይታ አድርገዋል።
አሰልጣኝ ደለለኝ ደቻሳ – ወላይታ ድቻ
ስለጨዋታው…
“ቀድመን ብንመራም በጥንቃቄ ጉድለት በተቆጠሩብን ግቦች ልንሸነፍ ችለናል። በሁለተኛው አጋማሽ በተጫዋቾቻችን ላይ የመጓጓት ነገር ነበር። መጀመሪያ የያዝነውን ነገር ይዘን መግባት ፈልገን ነበር ፤ ያው አልሆነም።”
ስለአጨራረስ ችግራቸው…
“ጎል ላይ እንደርሳለን ነገር ግን ቁጥራችን ያንሳል። በተወሰነ መልኩ ይሄን ነገር አይቻለሁ። በአጠቃላይ ግን ብዙ ነገር መስራት እንዳለብን ይሰማኛል።”
ወጣቶችን መጠቀሙ የሚያሳጣው ነገር ስለመኖሩ…
“ምንም ነገር ያሳጣኛል ብዬ አላስብም። ወጣቶች ናቸው ፤ ለሊጉም አዲስ ናቸው ከሃያ ዓመት በታች ያደጉም ተጫዋቾች አሉ። በእነሱ ላይ የሥነ-ልቦና ስራዎችን በመስራት በቀጣይ ጨዋታዎች ተሻሽለን እንቀርባለን የሚል እሳቤ አለኝ።”
ም/አሰልጣኝ እያሱ መርሐፅድቅ – ሀዲያ ሆሳዕና
ስለጨዋታው…
“በአጠቃላይ ጥሩ ነው። መጀመሪያ ላይ ግን የተወሰኑ መዘናጋቶች ነበሩ። ያም የመጀመሪያው ጎል እንዲቆጠርብን አድርጓል። በተለይ ከዕረፍት በፊት ብልጫ እንዲወስዱ ያደረጋቸው መዘናጋታችን እና ያገኙት የግብ ዕድል ነው። በሁለተኛው ግን ያንን አስተካክለን የጨዋታ ብልጫም ወስደን ተጨማሪ ሁለት ግብ አግብተን አሸናፊ መሆን ችለናል።”
ስለዱላ ሙላቱ ቅያሪ…
“የዱላ ብቻ ሳይሆን የተስፋዬም ቅያሪ ነው። የሁለቱም ቅያሪ በጥምር ያመጣው ውጤት ነው። ዱላም ጎል ማስቆጠር ብቻ ሳይሆን ጨዋታውን ለመቀየር ችሏል። ቅያሪው መልካም ነበር ብለን እናምናለን።”
በቶሎ ወደ ጨዋታው መንፈስ ስላለመመለሳቸው…
“የተፈጠረውን ክፍተት እንዴት ነው ? የተፈጠረውስ ምንድነው ? የሚለውን ቀስ ብለህ ነው የምታየው። መጀመሪያ ላይ የተሰጠህን ነገር ተግባራዊ ለማድረግ ስትል አንዳንድ የምትፈጥራቸው ክፍተቶች ሊኖሩ ይችላሉ። የመጀመሪያዋ ሰዓት ወሳኝ ናት።”
ስለዳዋ ሆቴሳ ብቃት…
“ስለዳዋ ምንም መናገር አይቻልም። ዳዋ እንደ ክለብ ብቻ ሳይሆን እንደሀገርም አሉን ከምንላቸው ተመራጭ አጥቂዎች አንዱ ነው። ግብ አካባቢም የተሻለ ተፅዕኖ አለው ቅጣት ምትም በማስቆጠር ይታወቃል። ያንን ነው ዛሬም ተግባራዊ ያደረገው። ልምምድ ላይ የሚያሳየውን ጨዋታ ላይም ደግሞታል። የዕለቱ ኮከብ ነው ማለት እንችላለን።”
© ሶከር ኢትዮጵያ