ሴቶች ፕሪምየር ሊግ | አቃቂ እና ድሬዳዋ ያለ ግብ ጨዋታቸውን አጠናቀዋል

የኢትዮጵያ ሴቶች ፕሪምየር ሊግ አንደኛ ዲቪዚዮን የመጀመሪያ ቀን ሁለተኛ ጨዋታ ቀን 10:00 ሰአት ተደርጎ አቃቂ ቃሊቲ እና ድሬዳዋ ከተማ ያለ ምንም ግብ ጨዋታቸውን አጠናቀዋል፡፡

የኳሱ ፍሰት ያማረ ቢሆንም ወደ ግብ ለመድረስ ሁለቱም ቡድኖች እጅጉን የተዳከሙበት በነበረው በዚህ ክፍለ ጊዜ 18ኛው ደቂቃ ላይ የአቃቂዋ አጥቂ ትደግ ፍሰሀ ግብ አስቆጥራ ከጨዋታ ውጪ የተባለባት እና ሌላኛዋ አጥቂ ሄለን መሰለ ያገኘችውን አጋጣሚ ወደ ግብ መትታ የድሬዳዋ ግብ ጠባቂ ሂሩት ደሴ ያወጣችሁ ሁለት ተጠቃሽ የአጋማሹ ሙከራዎች ናቸው፡፡

በሁለተኛው አጋማሽ ሁለቱም ቡድኖች ኳስን መሠረት አድርገው ለመጫወት የሞከሩ ሲሆን ከመጀመሪያው አጋማሽ የተሻለ የግብ አጋጣሚዎች የታዩበትም ነበር፡፡ 49ኛው ደቂቃ ል ድሬዳዋ ከተማዎች ባገኟት ክፍት አጋጣሚ ራቅ ብለው ከቆዩበት የግብ ክልል መጠጋት መጀመራቸውን ያሳየች አጋጣሚ አግኝተዋል፡፡ በግሏም ሆነ እንደ ቡድን ለድሬዳዋ ከተማ የተደራጀ የመሀል ክፍል እንዲኖረው ስታደርግ የነበረችው ማዕድን ሳህሉ ወደ ግብ ኳስ ይዛ ገብታ ወደ ግብ የለጋቻት ኳስ ግብ ጠባቂ ገነት አንተነህ መልሳባታለች፡፡ በአቃቂ በኩል ትደግ ፍሰሀ ከመሀል ሜዳው ወደ ቀኝ ባጋደለ ቦታ ኪፊያ አብዱራህማን የሰጠቻትን ኳስ በቀጥታ መትታ ቡድኗን ቀዳሚ አደረገች ሲባል በቀላሉ ሒሩት ልታድነው ችላለች፡፡

ደቂቃው እየገፋ ሲመጣ በቀኝ እና በግራ ከማዕድን እግር ስር በሚገኙ ኳሶች ወደ ጎን ሜዳውን ለጥጠው በኃላም አጥብቦ በመግባት የግብ ዕድሎችን ለማግኘት የምስራቁ ክለብ ታትሯል፡፡ በተለይ በቀኝ መስመር ፀጋነሽ አላንቦ ግብ ጠባቂ አልፋ ያልተጠቀመችበት እና ተቀይራ የገባችሁ ሊና መሀመድ በተመሳሳይ ነፃ አጋጣሚን ያመከነችበት ሊጠቀሱ የሚችሉ ዕድሎች ናቸው፡፡ በመጨረሻዎቹ ደቂቃዎች በተመሳሳይ ሄለን መሰለ በክፍት የጨዋታ እንቅስቃሴ የመጣችን ኳስ በአቃቂ በኩል መጠቀም ያልቻለችበት ቅፅበታዊ ዕድል የነበረች ብትሆንም ወደ ጎልነት ሳይለወጥ ጨዋታው ያለ ምንም ግብ ተጠናቋል፡፡

ከጨዋታው መጠናቀቅ በኃላ ልሳን የሴቶች ስፖርት የድሬዳዋ ከተማዋን አማካይ ማዕድን ሳህሉ የጨዋታው ምርጥ ብሎ ሸልሟታል፡፡

የሴቶች ፕሪምየር ሊግ ዛሬ በሁለት መርሀ ግብሮች የጀመረ ሲሆን በጨዋታዎቹ ላይ ካለው የሀዋሳ ሙቀታማ አየር አንፃር የውሀ መጠጫ እረፍት መኖሩ የሚበረታታ መሆኑን ለመግለፅ እንወዳለን፡፡


© ሶከር ኢትዮጵያ