የቤትኪንግ ፕሪምየር ሊግ 1ኛ ሳምንት ዓበይት ጉዳዮች (፪) – ተጫዋች ትኩረት

የቤትኪንግ የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ የመጀመሪያ ሳምንት ጨዋታዎች መጠናቀቅን ተከትሎ ከዚህኛው የጨዋታ ሳምንት ትኩረት የሳቡ ተጫዋቾችን በተከታዩ ፅሁፋችን ለመዳሰስ ሞክረናል።
👉ተስፈኛው የግብ ዘብ

ፋሲል ገብረሚካኤልን በተሰረዘው የውድድር ዘመን በተወሰኑ ጨዋታዎች ላይ የዳንኤል አጃይን አለመኖር ተከትሎ በጥቂት ጨዋታዎች ላይ ተመልክተነዋል። ዘንድሮ ደግሞ በሊጉ የመክፈቻ ጨዋታ ሰበታ ከተማ ድሬዳዋን ሲገጥም ተሰልፎ ጥሩ ጥሩ ኳሶችን ከማዳን በዘለለ የበረከት ሳሙኤልን የፍፁም ቅጣት ምት በአስደናቂ ሁኔታ በማምከን ብቃቱን አስመስክሯል። ኳሶችን ከማዳን በዘለለ ቡድኑን ከኋላ ሆኖ ይመራበት የነበረው መንገድ እና በራስ መተማመኑ በእሱ የዕድሜ ደረጃ ከሚገኙ ግብ ጠባቂዎች የተሻለው ነው ቢባል ማጋነን አይሆንም።

ገና በእግርኳስ ህይወቱ ጅማሬ ላይ የሚገኘው ግብጠባቂው በቀጣይ የእግር ኳስ አጠቃቀሙ እና በውሳኔ አሰጣጥ ላይ የሚታዩበትን የተወሰኑ ጉድለቶች በሒደት እያረመ የሚሄድ ከሆነ ቀጣዩቹ ዓመታት ይበልጥ የሚደምቅበት ይሆናል ተብሎ ይጠበቃል።

👉ሁለት ግቦችን ያስቆጠሩ ተጫዋቾች

በ2013 የቤት ኪንግ ኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ የመጀመሪያ የጨዋታ ሳምንት ሦስት ተጫዋቾች ሁለት ሁለት ግቦቹን ለቡድቸው ማስቆጠር ችለዋል።

በዘንድሮው የውድድር ዘመን የመጀመሪያው በአንድ ጨዋታ ከአንድ በላይ ግብ ማስቆጠር የቻለው ተጫዋች የኢትዮጵያ ቡናው አቡበከር ናስር ነው። ቡናማዎቹ ከወልቂጤ ከተማ ጋር 2-2 አቻ በተለያዩበት ጨዋታ አቡበከር የኢትዮጵያ ቡናን ሁለት ግቦችን ማስቆጠር ችሏል።

በተመሳሳይ እለት በ9 ሰዓት በተደረገው ጨዋታ አዳማ ከተማ ጅማ አባጅፋር 4-1 ሲረታበት የአዳማዎቹ ታፈሰ ሰርካ እና አብዲሳ ጀማል ለአዳማ ከተማ ሁለት ሁለት ግቦችን በማስቆጠር የቡድናቸውን የሊጉን ጅማሮ አሳምረዋል።

ሌላኛው ዐምና እጅግ አስደናቂ ብቃቱን ያስመለከተን ፍፁም ዓለሙ ትናንት ባህር ዳር ከተማ ሲዳማን 3-1 ሲረታ ሁለት ግቦችን አስቆጥሯዋል።

ከሦስቱ ተጫዋቾች የአብዲሳ ጀማልን ሁለት ግቦች ለየት የሚያደርጋቸው ተጫዋቹ በሁለተኛው አጋማሽ ተቀይሮ በመግባት ነው ግቦቹን ማስቆጠር የቻለው።

👉ድንገተኛው ግብ ጠባቂ ኢደል አሚን ናስር

ጅማ አባጅፋር በአዳማ ከተማ 4-1 በረታበት ጨዋታ ገና በ8ኛው ደቂቃ የጅማ አባጅፋሩ ግብጠባቂ አቡበከር ኑሪ በሰራው በጥፋት በቀጥታ ቀይ ካርድ ከሜዳ ይሰናበታል፤ ይህን ተከትሎ በተጠባባቂ ስፍራ ላይ ምንም አይነት ግብጠባቂ ያልነበራቸው የጅማ አባጅፋሩ አሰልጣኝ ጳውሎስ ጌታቸው ከድር ኸይዲንን በማስወጣት የተከላካይ መስመር ተሰላፊው ኢደል አሚን ናስርን በግብ ጠባቂነት ለመጠቀም ተገደዋል።

ጉዳዩን ለየት የሚያደርገም ከዚህ ቀደም በብዛት የሜዳ ላይ ተጫዋቾች ጓንት አጥልቀው በቋሚሙ መካከል ሲቆሙ የሚስተዋለው ቡድኖች የተፈቀደላቸውን የቅያሬ ኮታ ሲጨርሱ አልያም ዋናው እና ተጠባባቂው ግብ ጠባቂ ጉዳት ሲያስተናግዱ ነበር። ይህን ክስተት ለየት የሚያደርገው ታድያ ይህ ገጠመኝ ነበር።

ከጨዋታው መጠናቀቅ በኃላ ከሶከር ኢትዮጵያ ጋር ቆይታን ያደረገው ተጫዋቹ ከዚህ ቀደም ይህ ነው የሚባል የግብ ጠባቂነት ቆይታ ያልነበረው ሲሆን በተጠባባቂ ወንበር ከነበሩ ተጫዋቾች የተሻለ አካላዊ ቁመና ስለነበረው እንደተመረጠ ገልጿል።

👉ተወንጫፊው ጁኒያስ ናንጂቡ

በተሰረዘው የውድድር ዓመት በወልዋሎ ጥሩ ብቃቱን ያስመለከተን ናሚቢያዊው ጁኒያስ ናንጂቡ ዘንድሮ ያንኑ ተመሳሳይ አቅሙን ከወዲሁ በድሬዳዋ ከተማ ማሳየቱን ጀምሯል።

እጅግ አስደናቂ የሆነ ፍጥነት ባለቤት የሆነው ተጫዋቹ ሦስት ያህል ጥሩ ጥሩ የግብ አጋጣሚዎችን ቢያመክንም በሙሉ 90 ደቂቃ የጨዋታ ክፍለ ጊዜ ለሰበታ ከተማ የተከላካይ ክፍል ከፍተኛ የራስ ምታት ሲሆን ተስተውሏል።

በመልሶ ማጥቃት ከአጥቂ አማካያቸው ኤልያስ ማሞ እግር በሚነሱ ኳሶች ናንጂቡን ከተከላካይ ጀርባ በሚገኘው ጥልቀት በማስሮጥ ተደጋጋሚ ሙከራዎች ፈጥረዋል።

ተጫዋቹ ከተቃራኒ ተጫዋቾች ዘግይት ብሎ ወደ ማፈትለክ ቢገባም ባጠሩ ሰከንዶች ከተጋጣሚ ተጫዋቾች ቀድሞ የሚገኝበት መንገድ እጅግ አስገራሚ ነው።

👉ባለ አዲስ አድማሱ የመስመር ተከላካይ

ባለፈው ዓመት በስሁል ሽረ እጅግ ግሩም የሚባሉ ጊዜያትን አሳልፏል። በክረምቱ አምና ከነበረው እንቅስቃሴ በሰንጠረዡ አናት ከሚፎካከሩ ክለቦች ወደ አንዱ ያመራል ተብሎ ቢጠበቅም በመጨረሻም የረመዳን የሱፍ ማረፊያው ወልቂጤ ከተማ ሆኗል።

በመከላከሉ ሆነ በማጥቃት ረገድ በከፍተኛ ብርታት ቡድኑን ማገልገል የሚችለው ተጫዋቹ በሀገራችን የመስመር ተከላካዮች ብዙም ባልተለመደ መልኩ በሜዳው ስፋት ብቻ ከመገደብ ይልቅ የተለጠጠውን አቋቋም ለመስመር አጥቂዎች በመተው ወደ መሀል አጦብቦ በመግባት በተደጋጋሚ ሳጥን ውስጥ ለመግባት ሲጥር ይስተዋላል። ይህም ኳሶችን በማሻማትም ሆነ ወደ መሀል በማቀበል ላይ ከመገደብ ይልቅ በማጥቃት ሒደቶች ላይ ለግቡ በቀረበ አቋቋም ላይ በመገኘት የመጨረሻ ተሳትፎ እንዲያደርግ ያስችለዋል።

በእሁዱ ጨዋታ በተለይ በመጀመሪያው አጋማሽ ወልቂጤ ከተማዎች ሜዳውን ወደ ጎን ለጥጠው ለመንቀሳቀስ ይሞክሩ የነበሩትን ሁለቱ የኢትዮጵያ ቡና የመስመር አጥቂዎችን እንቅስቃሴ ለመመከት የወልቂጤ የመስመር ተከላካዮች በመከላከሉ ተጠምደው ቢቆዩም በተለይ በሁለተኛው አጋማሽ ግብ ካስተናገዱ ወዲህ ረመዳን የሱፍ በኩል ተደጋጋሚ ጥቃቶችን ከመሰንዘር አልፈው ከላይ በተገለፀው መልኩ ራሱ ረመዳን የሱፍ የአቻነቷን ግብ ለክለቡ ማስገኘት ችሏል።

👉ድንቅ ቀን ያሳለፈው ዳዋ ሆቴሳ

ባለፉት አራት ዓመታት በወጥነት ከደመቀበት አዳማ ከተማ ተለያይቶ የቀድሞ አሰልጣኙን አሸናፊ በቀለን ተከትሎ ወደ ሀዲያ ሆሳዕና ያመራው ዳዋ ሆቴሳ በአዲሱ ክለቡ አጀማመሩ ያማረ ይመስላል።

ሀዲያ ሆሳዕና ወላይታ ድቻን ከመመራት ተነስ 2-1 በረታበት ጨዋታ ዳዋ ግሩም የቅጣት ምት ጎል ከማስቆጠሩም በዘለለ ዱላ ሙላቱ ላስቆጠራት የማሸነፊያ ግብ ከርቀት አመቻችቶ ያቀበለበት መንገድ በራሱ አድናቆት የሚቸረው ነው።

ዳዋ በሀገራችን ከሚገኙ 9 ቁጥሮች በተሻለ በተለዋዋጭ የቦታ አያያዙ የሚታወቅ ሲሆን በድቻውም ጨዋታ እንዲሁ ይህ ተለዋዋጭ ባህሪው ለተጋጣሚ ቡድን ተከላካዮች ፈታኝ ሆኖ ተስተውሏል።

👉ያልተዘመረለት ፍፁም ዓለሙ

በሊጉ ከሚጠቀሱ ድንቅ የአጥቂ አማካዮች አንዱ የሆነው ፍፁም ዓለሙ መጠርያ ስሙን ብቻ ሳይሆን የአጨዋወት መንገዱንም የለወጠ ይመስላል። ከዓምና ጀምሮ የተዋጣለት ጎል አስቆጣሪ መሆኑን እያሳየ የሚገኘው ፍፁም በጨዋታ እንቅስቃሴ ላይ የበዛ ተሳትፎ ከማድረግ ይልቅ በጥቂት ቅፅበቶች ወሳኝ ተግባራትን ሲፈፅም መመልከት እየተለመደ መጥቷል። ትናንት ከጉዳት ጋር እየታገለ የተጫወተው ፍፁም በሁለት አጋጣሚዎች ያገኛቸውን የጎል አጋጣሚዎች በአስገራሚ የቴክኒክ ችሎታ፣ እርጋታ እና የአካል ብቃት ጥንካሬ ወደጎልነት ቀይሮ ለጣና ሞገዶቹ የጨዋታውን ሒደት ቀላል አድርጎታል።

👉 የባህር ዳር የኋላ ክፍልን ያረጋጋው መናፍ ዐወል

በሊጉ ከሚገኙ ጥቂት ተስፈኛ ተከላካዮች አንዱ የሆነው መናፍ ዐወል ባለፈው ዓመት ያሳየውን ድንቅ አቋም ዘንድሮም የሚደግመው ይመስላል። ተጫዋቹ ብዙ ዓመት መጫወት ልምድ ባይኖረውም በእንቅስቃሴ ላይ እርጋታን የተላበሰ እና ውሳኔ አሰጣጡ ድንቅ ነው። ይህም ባለፈው ዓመት ባስቆጠራቸው ልክ ጎሎች ለሚያስተናገደው የባህር ዳር የኋላ ክፍል መረጋጋት አይነተኛ በጎ ሚና እንደሚጫወት በትናንቱ የሲዳማ ቡና ጨዋታ ላይ አሳይቷል።

በጨዋታው ከሲዳማ አጥቂዎች ጋር በነበረው የአንድ ለአንድ ግንኙነት በአመዛኙ አሸናፊ ሆኖ የተወጣ ሲሆን የማጥቃት እንቅስቃሴያቸውንም በቀላሉ ሲቆጣጠር ተስተውሏል። በመጨረሻው ደቂቃ ከማዕዘን የተመታውን ኳስ በእጁ በመንካት ለተገኘው የፍፁም ቅጣት ምት ምክንያት ከመሆኑ ውጪም የጨዋታው ኮከብ ሊያስብለው የሚችል ድንቅ ቀን አሳልፏል።

👉የተቀያሪ ተጫዋቾች ሚና

በዚህ ሳምንት በተደረጉ ጨዋታዎች ተቀይረው የገቡ ተጫዋቾች ጎላ ያለ ሚና ሲወጡ ተስተውሏል። አዳማ ከተማ ጅማ አባ ጅፋርን 4-1 በረታበት ጨዋታ የመጀመርያ የፕሪምየር ሊግ ጨዋታውን ያደረገው አብዲሳ ጀማል ሁለት ጎሎችን ማስቆጠር ሲችል በተመሳሳይ በዚህ ጨዋታ ተከላካዩ አድልአሚን ናስር ለ82 ደቂቃዎች ግብ ጠባቂ በመሆን ተፈጥሯዊ የቦታው ተጫዋች ካለመሆኑ አንፃር ጥሩ ተንቀሳቅሷል። ወልቂጤ በቡና ከመመራት ተነስቶ አቻ ሲለያይ ያሬድ ታደሰ ተቀይሮ በመግባት የመጀመርያውን ጎል አስቆጥሮ ቡድኑን ሲያነቃቃ ሆሳዕና ድቻን በረታበት ጨዋታም ዱላ ሙላቱ የማሸነፍያ ጎል ከተጠባባቂ ወንበር ተነስቶ አስቆጥሯል። በሳምንቱመጨረሻ ጨዋታ ደግሞ ባለክህሎቱ አማካይ ሄኖክ አወቀ ፍፁምን ቀይሮ ገብቶ ለባዬ ገዛኸኝ ጎል ኳስ አመቻችቷል።

👉የወንድማማቾቹ ፍልሚያ

በአንደኛ ሳምንት የቤትኪንግ ፕሪምየር ሊግ የመጨረሻ መርሐግብር ባህርዳር ከተማን ከሲዳማ ቡና ባገናኘው ጨዋታ ሁለቱን ወንድማማቾች በተቃራኒ ተፋልመዋል።

ባዬ ገዛኸኝ እና ሐብታሙ ገዛኸኝ በተቃራኒ የሁሉቱን ቡድኖች የአጥቂ መስመር እየመሩ በተገናኙበት ጨዋታ የባዬ ገዛኸኙ ባህርዳር ከተማ 3-1 ማሸነፍ ችሏል። በጨዋታው ባዬ ገዛኸኝ ለአዲሱ ክለቡ ባህርዳር ከተማ አንድ ግብ ማስቆጠር እና አንድ ማመቻቸት ሲችል በተቃራኒው ታናሽ ወንድሙ ሀብታሙ ተቀዛቅዞ ውሏል።

በተመሳሳይ በዚሁ ጨዋታ ላይ የወዴሳ ወንድማማቾች በተቃራኒ ቡድን ተገናኝተዋል። የሲዳማው ግብ ጠባቂ ፍቅሩ ወዴሳ በተጠባባቂ ወንበር ላይ ሆኖ ጨዋታውን ሲጨርስ ታናሽ ወንድሙ ሰለሞን ወዴሳ በባህር ዳር ከተማ የተከላካይ ክፍል ጥሩ ተንቀሳቅሶ ወጥቷል።

👉ህይወት ያለ አዲስ ግደይ በሲዳማ

ላለፉት ዓመታት በሲዳማ ቡና ድንቅ ጊዜያትን በማሳለፍ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን ተቀዳሚ ተመራጭ ተጫዋች መሆን የቻለው አዲስ ግደይ በክረምቱ የዝውውር መስኮት በአምበልነት ይመራው የነበረውን ሲዳማ ቡናን ለቆ ፈረሰኞቹን መቀላቀሉ ይታወሳል። አዲስ በተለይ የመጨረሻዎቹን ሦስት ዓመታት የሲዳማ ቡና እጅግ ወሳኙ ተጫዋች ነበር። በእሱ ደረጃ ተፅዕኖ ተፈጣሪ የሆነን ተጫዋች እንደው እንደነገሩ በቀላሉ መተካት በአንድ የዝውውር መስኮት የሚሳካ አይመስልም።

ይህን ክፍተት ለመድፈን አሰልጣኝ ዘርዓይ ሙሉ ጫላ ተሺታን ከወልቂጤ እንዲሁም ማማዱ ሲዲቤን ከባህርዳር ከተማ ማስፈረም ችለዋል። ይህም በአዲስ ጫንቃ ላይ ተንጠልጥሎ የከረመው የሲዳማን ቡና የግብ ማምረት አቅምን ሐብታሙ ገዛኸኝን ጨምሮ ለሦስቱ አጥቂዎች ለማከፋፈል የታለመ ዝውውር ይመስላል። ይህ የሚሆነው ግን አዳዲስ ፈራሚዎቹ በፍጥነት ቡድኑን ተላምደው በቀድሙ ክለቦቻቸው ይሰጡ የነበረውን ግልጋሎት መስጠት ከቻሉ ብቻ ነው።


© ሶከር ኢትዮጵያ