የቤትኪንግ ፕሪምየር ሊግ 1ኛ ሳምንት ዓበይት ጉዳዮች (፫) – አሰልጣኞች ትኩረት

የቤትኪንግ የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ ጨዋታዎች በሳምንቱ መጨረሻ መካሄድ ሲጀምሩ በጨዋታ ሳምንት አንድ የተዘብናቸውን ትኩረት ሳቢ አሰልጣኝ ነክ ጉዳዮች እና የሳምንቱ አበይት አስተያየቶችን በተከታዩ ፅሁፋችን ተካተዋል።

👉አብርሃም መብራህቱ ዳግም በክለብ አሰልጣኝነት

ከ1996 የውድድር ዘመን ለመጨረሻ ጊዜ ወንጂ ስኳርን በኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ በዋና አሰልጣኝነት ከመሩበት ወቅት በኋላ አሰልጣኝ አብርሃም መብራህቱ በሊጉ ሲታዩ የዘንድሮው የመክፈቻ ጨዋታ የመጀመርያ ነው። በ1997 ወደ ብሔራዊ ሊጉ ኢትዮጵያ መድን ተሻግረው ከሰሩ በኋላ ወደ የመን አቅንተው ለቀጣይ 13 ዓመታት በሀገሪቱ ብሔራዊ ቡድን እና ክለቦች ከአሰልጣኝነት እስከ ቴክኒክ ዳይሬክተርነት ድረስ ሲሰሩ ቆይተው ወደ ኢትዮጵያ በመመለስ ዋልያዎቹን መረከባቸው ይታወሳል።

ባሳለፍነው ክረምት ለሁለት ዓመታት የቆዩበት የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን አሰልጣኝነት ቆይታቸው መጠናቀቁን ተከትሎ የሰበታ ከተማ አሰልጣኝ ለመሆን መስማማታቸው ይታወቃል። ባሳለፍነው ቅዳሜ ሰበታ ከተማ ከድሬዳዋ ከተማ ያደረጉት ጨዋታም አሰልጣኝ አብርሃም መብራቱ ከ17 የውድድር ዓመታት በኋላ በፕሪምየር ሊግ ጨዋታ ቡድናቸውን የመሩበት ሆኗል።

👉ኢያሱ መርሐፅድቅ ከቢሮ ወደ ቴክኒካል ኤሪያ

እስካሳለፍነው የካቲት 2012 ድረስ የኢትዮጵያ እግርኳስ ፌደሬሽን ዋና ፀሀፊ በመሆን ያገለገሉት እና ከዚህ ቀደም በሀሮማያ ዩኒቨርስቲ በመምህርነት ሲያገለግሉ የቆዩት ኢያሱ መርሐፅድቅ (ዶ/ር) አሁን ደግሞ በአዲስ ሚና ብቅ ብለዋል።

በቅርቡ የሀዲያ ሆሳዕናው አሰልጣኝ አሸናፊ በቀለ ረዳት አሰልጣኝ በመሆን የተሾሙት ኢያሱ መርሃፅድቅ በሀገራችን እግርኳስን በተለምዶ የእግርኳስ አሰልጣኝ ለመሆን የግድ ተጫውቶ ማለፍ አለበት የሚለውን ብሒል በመስበር እግርኳሱን የሚያግዙ ሙያዎች የሰለጠኑ ግለሰቦች በዚህ ደረጃ ባሉ የሥራ ኃላፊነት መሰማራታቸው ለሌሎች ባለሙያዎች ተስፋን ከመሰጠት በዘለለ እግርኳሳችን በጥቅሉ ያጣውን በዘመን የተዋጀ አስተሳሰብ እና ስልጠናን በማስረፅ ረገድ መሰል ሙያተኞች ዓይነተኛ ሚናን ይወጣሉ ተብሎ ይጠበቃል።

👉እጅጉን የከበደው የጳውሎስ ጌታቸው ኃላፊነት

በአሁኑ ወቅት በኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ በማሰልጠን ከሚገኙ አሰልጣኞች እንደ ጅማ አባጅፋሩ አለቃ ጳውሎስ ጌታቸው ባልተመቻቸ ሁኔታ ውስጥ እየሠራ የሚገኝ አሰልጣኝ ፈልጎ ማግኘት ከባድ ይመስላል።

እርግጥ ነው ይብዛም ይነስም አብዛኛዎቹ የሀገራችን ክለቦች ካለበት ወቅታዊ ቁመና አንፃር በንፅፅር የተሻለ ብሎ ማስቀመጥ ይችል ይሆናል እንጂ ለሥራ ምቹ የሆነ ከባቢ ፈልጎ ማግኘቱ አዳጋች ነው። ሆኖም የአሰልጣኝ ጳውሎስ ጌታቸውን ስራ የከፋ የሚያደርገው በነጠፈው የክለቡ ፋይናንስ አቅም መነሾነት የሚፈልገውን ተጫዋቾች ለማስፈረም መቸገሩ፤ ብሎም ያስፈረማቸውን ማፀደቅ አለመቻሉን ጨምሮ ፣ ለቀናት ልምምድ ያልሰሩ ተጫዋቾችን ወደ ሜዳ ይዞ መግባትን ፣ ለወራት ደሞዝ ያልተከፈላቸውን ተጫዋቾችን ለጨዋታ ማነሳሳት ፣ በስነልቦና ረገድ የተዳከመ ስብስብን መምራት ብቻ በብዙ ችግሮች ውስጥ የሚገኘውን ይህን ስብስብ በሀላፊነት ከመምራት ባሻገር የከበደ ስራ ፈልጎ ማግኘት ከባድ ነው።

👉 የመጀመርያ ጨዋታዎች

ሊጉ ዐምና በኮሮና ምክንያት የተቋረጠ ከመሆኑ አንፃር አብዛኛዎቹ ክለቦች የአሰልጣኝ ለውጥ ከማድረግ ተቆጥበው ለአዲሱ የውድድር ዓመት ቀርበዋል። አምስት ክለቦች ደግሞ በአዲስ አሰልጣኝ ሊጉን ጀምረዋል። የቅዱስ ጊዮርጊሱ ማሂር ዴቪቭስ ሊጉን በሽንፈት ሲጀምሩ፣ የሰበታ ከተማው አብርሀም መብራቱ በአቻ ስራቸውን ጀምረዋል። የአዳማ ከተማው (ከምክትልነት ዋና የሆኑ) አስቻለው ኃይለሚካኤል እና ምንም እንኳን ቡድናቸውን መምራት ባይችሉም የሀዲያ ሆሳዕናው አሸናፊ በቀለ ደግሞ በድል ጀምረዋል። የሀዋሳው ሙሉጌታ ምህረት ቡድኑ አራፊ የነበረ በመሆኑ የመጀመርያ ጨዋታውን በሁለተኛ ሳምንት ከሰበታ ከተማ ጋር ያደርጋል።

ዐበይት አስተያየቶች

👉ጳውሎስ ጌታቸው ስለሳሳው ስብስባቸው እና ቀጣይ ዕጣ ፈንታው…

“እነዚህ ተጫዋቾች ያልቅላቸዋል አያልቅላቸውም የሚለው የእኔ የቤት ስራ አይደለም። ዛሬ የተመለከታችኋቸው ተጫዋቾች ወጣቶች ናቸው። ተጠባባቂ ላይ ያሉት ዘጠኝ ተጫዋቾችም ከጨዋታ ውጪ ናቸው። ጥሩ ዝግጅትም አላደረግንም ፤ የቀን እጥረትም ነበር። ፈታኝ ነው ፤ ሰቆቃ ላይ ነው ያለነው። እኔ ውጤቱ ቅር አላሰኘኝም። ወደፊት ግን የሚፈጠረው ነገር ምን ይሆናል የሚለውን ከዚሁ ለመተንበይ ከባድ ነው። ተጫዋቾቹ ካለቀላቸው እና ተሟልተን ከገባን ሁለት በረኞች አሉን በተዘጋጀንበት አጭር ጊዜ የአቅማችንን ለመስራት እንታገላለን።”

👉አስቻለው ሃይለሚካኤል ግብ ስላስቆጠሩት ታፈሰ ሰርካ እና አብዲሳ ጀማል …

“አብዲሳ ጉዳት ላይ የነበረ ተጫዋች ነው ፤ በዝግጅት ወቅት ጉዳት አስተናግዶ በማገገም ላይ የነበረ ተጫዋች በመሆኑ ነው ቀይረን ያስገባነው። ጥሩ አቅም ያለው ተጫዋች ነው ወደፊትም ለሀገር ከፍተኛ ጥቅም ማበርከት የሚችል ልጅ ነው። ታፈሰ ደግሞ በራስ መተማን ሰጥተነው ያለውን ልምድ ተጠቅሞ ሁለት ግቦችን አስቆጥሯል።”

👉ካሳዬ አራጌ ስለ ወልቂጤው ጨዋታ እና ስለ አቡበከር ተፅዕኖ

“የመጀመሪያ ጨዋታ ስለሆነ ነፃ ሆኖ ያለመጫወት ነገር ተጫዋቾች ላይ ይታይ ነበር። ጥንቃቄ የበዛበት ጨዋታ ነበር ፤ እንደዛም ሆኖ ግን የተሻሉ ዕድሎችን መፍጠር ችለን ነበር ፤ እነዛን ወደ ጎል መቀየር አልቻልንም። የገቡብን ጎሎች ላይ ሳይሆን የምንሄዳቸውን ኳሶች ውጤታማ ማድረግ ቢቻል ውጤቱን መቀየር ይቻል ነበር ብዬ አስባለሁ። ያ ነው መቋረጥም የሌለበት። እንደዚህ ዓይነት ክፍተቶች ሊፈጠሩ ይችላሉ። እነዚህን ክፍተቶች ተጋጣሚ እንዳይጠቀም ዕድሎች በቀላሉ እንዳይባክኑ ማድረግ ይኖርብናል።”

“የለም። ምክንያቱም አቡበከር እነዛን ዕድሎች ያገኘው በሌሎቹ የቦታ አያያዝ ነው። ስለዚህ በቡድናችን ውስጥ የምናስበው እያንዳንዱ ተጫዋች ሂደቱን የሚጠብቅ ፣ ለመጨረሻ ኳስ ራሱን የሚያዘጋጅ ፣ የመጨረሻ ኳስ የሚሰጥ እንዲሆን ነው። እንደአንድ ተጫዋች አይደለም የምናስበው። ሌሎቹ በሚፈጥሩት ዕድል ውስጥ አንድ ተጫዋች ተደጋጋሚ ዕድል ሊያገኝ ይችላል።”

👉ደግአረግ ይግዛው ስለ ወልቂጤ ከተማ

“ይህ ጨዋታ ለኛ የማንቂያ ጨዋታ ነው፡፡ ለውድድሩ በምን ያህል መጠን መዘጋጀት እንዳለብን ያየንበት ነው፡፡ በመጀመርያው አጋማሽ በጉልህ ይታይ የነበረው የኛ ድክመት ጨዋታውን ተቆጣጥረን ማሸነፍ እንደምንችል በራሳችን ዕምነት አልነበረንም ነበር፡፡ በዚህም በጣም አፈግፍገን በነፃነት እንዲጫወቱ ዕድል ሰጥተናቸው ነበር፡፡ የዛሬው ጨዋታ ብዙ ነገር አሳይቶናል፡፡ በአካልም በአዕምሮም ዝግጁ ለመሆን እንጥራለን፡፡”

👉 ሥዩም ከበደ ቅዱስ ጊዮርጊስን መርታታቸው ስለሚኖረው ጥቅም

“በኮፌዴሬሽን ካፕ ውድድር መሳተፋችን በጣም ጠቅሞናል። በሁሉም ረገድ የተሻለ ሆነን እንድንቀርብም አግዞናል። ቅዱስ ጊዮርጊስን የሚያክል ትልቅ ቡድን ካላሸነፍክ ለሻምፒዮንነት አትጫወትም። ስለዚህ ከቅዱስ ጊዮርጊስ ዓይነት ቡድኖች የምትወስዳቸው ነጥቦች ናቸው ለሻምፒዮንነት የሚያበቁህ። የሚገባንን አድርገን የምንፈልገውን ነጥብ አግኝተናል። እነርሱም የሚቻላቸውን ለማድረግ ሞክረዋል፤ ግን ሊያሳኩ አልቻሉም።”

👉ማሂር ዴቪድስ ቡድኑን ዋጋ ስላስከፈለው የማታሲ ስህተት

“እርሱን በሚያክል ከፍተኛ ልምድ ባለው ትልቅ ግብጠባቂ የማይጠበቅ ስህተት ነው የሰራው”

👉 አብርሃም መብራቱ ስለወጣቱ ግብ ጠባቂ ፋሲል ገብረሚካኤል

“ደጋግሜ የምናገረው ነገር ነው። ለሀገራችን ግብ ጠባቂዎች ተገቢውን ሥልጠና ከሰጠናቸው እና ዕምነት ከጣልንባቸው የሚፈለገውን አገልግሎት መስጠት ይችላሉ። ፋሲል አዲስ

ነው ፤ ገና ወጣት ነው። ለእኔ ግን የጨዋታው ኮከብ እሱ ነበር ማለት እችላለሁ። ቁም ነገሩ ተገቢውን ሥልጠና እና ዕድል መስጠት ላይ ነው። ያ ከሆነ ጥቅሙ ለክለቡ ብቻ ሳይሆን የግብ ጠባቂ ችግር ላለባት ሀገራችንም ጭምር ነው።”

👉ፋሲል ተካልኝ ስለ ወሳኙ ተጫዋቻቸው ጉዳት

“ስለዚህ ጉዳይ አሁን ላይ ለመናገር ይቸግረኛል። ከጨዋታው በፊት ልምምድ ላይ የነበረበት ጉዳት ይሁን ወይስ አዲስ ጉዳት የደረሰበት የሚለውን መረጃ ስለሌለኝ ምንም አልልም። ግን አመቱን ሙሉ እንዲያገለግለን ስለምንፈልግ በቀጣይ ማሳረፍም ካለብን እናሳርፈዋለን። ግን እንደ ጉዳቱ ይወሰናል።”

👉ዘርዓይ ሙሉ ስለ አዲስ ግደይ ቡድኑን መልቀቅ እና ተፅዕኖው…

ዛሬ ይህ ነው ብሎ ለመናገር አስቸጋሪ ነው። ምክንያቱም 6 እና 7 ተጫዋቾቻችን በተለያዩ ምክንያቶች አልተጫወቱም። በቀጣይ ግን ይደርሳሉ ብዬ አስባለሁ። በአዲስ ምትክም የመጣ ተጫዋች አለ። እርሱም በተመሳሳይ በጉዳት አልተጫወተም። በጨዋታው ግን ተፅዕኖ የፈጠረብን እኛ ስንለማመድበት የነበረው የሰው ሰራሽ ሜዳ እና ዛሬ የተጫወትንበት የተፈጥሮ ሜዳ መለያየቱ ነው። ይህ ብቻ ሳይሆን የአየር ሁኔታውም ትንሽ ተጫዋቾቹን ከብዷቸው ነበር። ለዛም ነው አጥቅተን በቶሎ መመለስ ያልቻልነው። ከዚህ በኋላ ግን ቆይታችን እዚሁ ስለሆነ ሁለቱን ነገር እንለምዳለን ብዬ አስባለሁ። ቡድናችን ግን በአንድ ግለሰብ ላይ ብቻ መሠረት ያደረገ ቡድን አደለም። የእርሱም መኖር እና አለመኖር አደለም ክፍተታችን።


© ሶከር ኢትዮጵያ