ሪፖርት | ሰበታ ከተማ የመጀመሪያ ድሉን አሳክቷል

የዓመቱን ውድድሩ ዛሬ የጀመረው ሀዋሳ እና ሳምንት ነጥብ የተጋራው ሰበታ የተገናኙበት ጨዋታ በሰበታ 3-1 አሸናፊነት ተጠናቋል።

በሀዋሳ የመጀመሪያ የሊግ ጨዋታ ሰበታ ከተማ በቀዳሚው ሳምንት የድሬዳዋ ከተማው ጨዋታው ከተጠቀማበት አሰላለፍ ውስጥ ያሬድ ሀሰንን በተከላካዩ አዲሱ ተስፋዬ በመለወጥ እና ቡድኑ ላይ ሽግሽግ በማድረግ ቢያድግልኝ ኤልያስን በአማካይ ክፍሉ ላይ ተጠቅሟል።

እምብዛም ማራኪ ባልነበረው የመጀመሪያው አጋማሽ ሰበታ ከተማዎች በኳስ ቁጥጥሩ ረገድ የተሻሉ ሆነው ታይታዋል። ነገር ግን የጎንዮሽ ቅብብሎች የበዙበት እና የሀዋሳን የመከላከል አደረጃጀት በሚፈለገው መጠን ያልፈተነው የቡድኑ የኳስ ፍሰት የመጨረሻ የግብ ዕድል ሲያስገኝለት አልታየም። 6ኛው ደቂቃ ላይ ቡልቻ ሹራ ከሳጥን ውስጥ የሞከረው እና ሶሆሆ ሜንሳህ ያወጣው የተሻለ ሙከራም በላውረንስ ላርቴ እና በሶሆሆ መካከል በተፈጠረ የቅብብል ስህተት የተገኘ ነበር።

ሀዋሳዎችም አብዛኛውን ደቂቃ የተጋጣሚያቸውን አማካይ መስመር የኳስ ቅብብሎች ለማቋረጥ እና ተጫዋቾችን በመያዝ ላይ አተኩረው ታይተዋል። እንቅስቃሴው በአመዛኙ በራሳቸው የሜዳ ክፍል ላይ እንዲቆዩ ቢያደርጋቸውም የሚቀሟቸውን ኳሶች በቶሎ ለሦስትዮሹ የፊት መስመራቸው ሲያደርሱ አልታየም። ከመስፍን ታፈሰ የርቀት ሙከራዎች ውጪም ቡድኑ የተሻለ አደጋ ፈጥሮ የነበረው 9ኛው ደቂቃ ላይ ቢያድግልኝ ኤልያስ ለአዲሱ ተስፋዬ የሰጠውን ኳስ ተከትሎ በተፈጠረ ስህተት መስፍን ሲሞክር ነበር። በዚህ ሁኔታ ኢላማቸውን ባልጠበቁ ጥቂት ሙከራዎች የቀጠለው ጨዋታ 35ኛው ደቂቃ ላይ ግብ ተቆጥሮበታል። ሰበታዎች ያገኙትን ወደ ግራ ያደላ ቅጣት ምት ጥሩ ሲንቀሳቀስ የነበረው ፉዓድ ፈረጃ በቀጥታ መትቶት እና በሶሆሆ እና የግቡ ብረት ሲመለስ አግኝቶ ዓለማየሁ ሙለታ በቀላሉ በማስቆጠር ቡድኑን ቀዳሚ ማድረግ ችሏል።

ሁለተኛው አጋማሽ ሲጀመር ተከታታይ የማዕዘን ምቶችን ያገኙት ሀዋሳ ከተማዎች 52ኛው ደቂቃ ላይ ቀንቷቸዋል። ብርሀኑ በቀለ ከቀኝ መስመር ያሻማውን ኳስ መስፍን ታፈሰ በግንባር በመግጨት ቡድኑን አቻ አድርጓል። ሀዋሳዎች በቀጣዮቹ ዱቂቃዎችም ከመጀመሪያው አጋማሽ የተሻለ ንቃት ታይቶባቸው የጨዋታውን ሚዛን ወደራሳቸው ለመመለስ ጥረታቸውን ቀጥለዋል። 65ኛው ደቂቃ ላይ በብሩክ በየነ አማካይነት ጥሩ ዕድል ፈጥረውም አባይነህ ፊኖን ቀይሮ የገባው ወንድምአገኝ ተስፋዬ ሞክሮ ተከላካዮች ተደርበውበታል። ሆኖም የፈጠሩት ጫና ፍሬ ሳያፈራ ምኞት ደበበ የቀድሞው የቡድን ጓደኛው ቡልቻ ሹራ ላይ የሰራውን ጥፋት ተከትሎ በተሰጠው ፍፁም ቅጣት ምት ዳዊት እስጢፋኖስ 68ኛው ደቂቃ ላይ 2-1 እንዲመሩ ያደረገችን ግብ አስቆጥሮባቸዋል።

ዱሬሳ ሹቢሳን በታደለ መንገሻ ቀይረው ያስገቡት ሰበታዎች የመጨረሻዎቹ ደቂቃዎች ላይ በዱሬሳ ፍጥነት ታግዘው መጠነኛ ጫና መፍጠር ችለዋል። በዚህ ሂደትም 85ኛው ደቂቃ ላይ ድላቸውን ያረጋገጡበትን ግብ አስቆጥረዋል። ፉዓድ ፈረጃ በረጅሙ ለቡልቻ ያሻገረውን ኳስ ለማውጣት ሶሆሆ ያደረገው ሙከራ ሳይሳካ ቀርቶ ራሱ ፉዓድ ግብ ጠባቂው ቦታውን ከመያዙ በፊት በቀጥታ መትቶ አስቆጥሯል። ጨዋታውም በሰበታ 3-1 አሸናፊነት ተጠናቋል።



© ሶከር ኢትዮጵያ