በቤት ኪንግ የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ ሁለተኛ ሳምንት መርሐግብር በጎዶሎ ተጫዋች 45 ያክል ደቂቃዎች ያሳለፈው ኢትዮጵያ ቡና ፋሲልን ከረታበት ጨዋታ መጠናቀቅ በኋላ የሁለቱ ቡድኖች አሰልጣኞች ለሱፐር ስፖርት ተከታዩን አስተያየት ሰጥተዋል።
ካሣዬ አራጌ – ኢትዮጵያ ቡና
ስለ ጨዋታው
” የመጀመሪያው አጋማሽ በሁለታችንም በኩል ቀስ ብለን ጨዋታውን ተቆጣጥረን ለመጫወት ጥረት ያደረግንበት ነበር፤ በዚህ መነሻነት እንቅስቃሴው ዝግ ያለ ነበር። ሁለተኛው አጋማሽ ደግሞ ገና በጊዜ ነበር ተጫዋች በቀይ የወጣብን ከዚያ በኃላ በነበረው ሒደት የተጫዋቾች አደራደር ለውጥ ለማድረግ ሞክረናል፤ በዚህም መስመሮችን ዘግተን ወደ መሀል አጥብበን ኳሱን እየተጫወትን እድሎችን ለመፍጠር ሞከረናል ነገርግን የተጫዋቾች ቁጥር ብልጫ ስለነበራቸው ወደ ኃላ ሰዎችን ለማብዛት ሞክረናል። ይህም ወደ ፊት ስንሄድ የቁጥር ብልጫ ይወሰድብን ነበር። ቢሆንም የተገኙትን ጥሩ አጋጣሚዎችን ተጠቅመናል።”
በሁለተኛው አጋማሽ ስለተደረጉ የተጫዋቾች ለውጥ
” ከቀይ ካርዱ በኃላ በነበረው ሒደት መሀል ሜዳውን በሦስት ተጫዋቾች እየተቀያየሩ እንዲሸፈን ለማድረግ ሞክረናል። አቤል ፣ ታፈሰ እና አማኑኤል ተጠቅመን ከሁለቱ የመስመር ተከላካዮች ጋር በመሆን እየተቀያየሩ መሀል ሜዳውን ለመሸፈን ሞክረናል። አቤልን ወደ ኃላ ለመሳብ ሞክረን ነበር ምናልባት ያንን የሚከፈት ቦታ መሸፈን ይቸገራል በሚል ቀይረን አስወጥተነዋል።”
ስለ ቡድኑ መሻሻል
“ወደ ፊት ስንሄድ አሁንም ችግሮች አሉ። በሰጪው እና በተቀባዩ መካከል ትክክለኛ የሆነ መግባባት አትመለከትም። ተቀባዩ የሚጠይቅበትና አቀባዩ የሚሰጥበት እንዲሁም አንዳንዴ ሰጪው ባልተጠየቀበት አቀባዩ የሚሰጥበትን ሂደት ትመለከታለህ። ስለዚህም በሚገኙ ክፍተቶች ላይ ውጤታማ ለመሆን በሰጪው እና ተቀባዩ መሀል ፍፁም መግግባት እንዲኖር መስራት ይኖርብናል።”
ሥዩም ከበደ – ፋሲል ከነማ
ስለ ጨዋታው
“እስከ እረፍት ድረስ ጥሩ ነበርን በሁለተኛው አጋማሽም በዚያው ልክ እንገባለን የሚል እምነት በሁላችንም ውስጥ ነበር። በሁለተኛው አጋማሽ ተጋጣሚያችን ሜዳ ላይ በተለየ መንገድ ሲቀርብ ለዚያ ምላሽ መስጠት አልቻንም። የራስ መተማመኑን ለእነሱ በሰጠናቸው ቁጥር የጨዋታ ሚዛኑን እየወሰዱት ሄደዋል። እንደ ቡድን እገሌ በዚህ ደረጃ ነው የሚገኘው ብሎ ለመገምገም ከባድ ነው የነበረው። ነገር ገግ ብቅ እልም የሚል ነገር ነበር። የዛሬው ጨዋታ ለሻምፒዮንነት እንደሚጓዝ ቡድን ብዙ ያስተማረን ጨዋታ ነው። ስለዚህም ሁላችንም በጋራ ቁጭ ብለን ስህተቶቻችንም ለማረም መስራት ይኖርብናል።”
© ሶከር ኢትዮጵያ