የኢትዮጵያ ሴቶች ፕሪምየር ሊግ አንደኛ ዲቪዚዮን ሁለተኛ ቀን ጨዋታ ዛሬም በሀዋሳ ከተማ ሲቀጥል ኢትዮ ኤሌክትሪክ አዲስ አበባ ከተማን 1ለ0 አሸንፏል፡፡
ተመሳሳይ የጨዋታ ስልት የታየበት የመጀመሪያው አጋማሽ ሁለቱም ቡድኖች ለማጥቃት ያላቸው ፍላጎት ቀዝቀዝ ያለ የነበረ ቢሆንም በአመዛኙ ግን አዲስ አበባ ከተማዎች ከተሻጋሪ ኳሶች እና በረጅሙ በሚጣሉ ዕድሎች በአጥቂዋ ቤተልሄም ታምሩ ግብ ለማስቆጠር የተወሰነ ጥረትን ማድረግ ችለዋል፡፡ በአንፃሩ ኤሌክትሪኮች ከቆመ ኳስ ወርቅነሽ ሜልሜላ እና ምንትዋብ ዮሀንስ አማካኝነት ሙከራን አድርገው ግብ ጠባቂዋ ቤተልሄም ዮሀንስ ካዳነችሁ አጋጣሚ ውጪ የረቡ ነገሮች መከወን አልቻሉም፡፡ ፈጣን ኳሶችን ከአማካዩዋ ትርሲት መገርሳ በፍጥነት ወደ አጥቂዋ ቤተልሄም በሚጣሉ ኳሶች ፍጥነትን መሠረት በማድረግ በተጨማሪነት የኤሌክትሪኮችን የተከላካይ መስመር ስህተት ተጠቅመው ጥሩ ዕድሎችን አዲስ አበባ ከተማዎች ቢያገኙም ደካማ የአጨራረስ ክፍተት ታይቶባቸዋል፡፡
በሁለተኛው አጋማሽ ኢትዮ ኤሌክትሪኮች የለወጧቸው ሶሦት ቅያሪዎች ወደ ጨዋታ በመመለስ ጥሩ ዕድሎችን ለመፍጠራቸው እና አጋጣሚዎችን እንዲያገኙ የረዳቸው ነበር፡፡ በተለይ በቀኝ መስመር ልደት ቶሎአ፣ እፀገነት ብዙነህ እና ሲሳይ ገብረዋህድ መግባታቸው የአሰልጣኝ መሠረት ማኔን ቡድን ቅርፅ በተወሰነ መልኩ ያስተካከለ ነበር፡፡ ሆኖም ተመሳሳይ አጨዋወትን እንደ መጀመሪያው አጋማሽ መንቀሳቀስ የቻሉት አዲስ አበባ ከተማዎች አስቆጪ የሚባሉ ዕድልን አምክነዋል፡፡ 50ኛው ደቂቃ ትርሲት ብልጠቷን ተጠቅማ መሀል ለመሀል ለቤቴልሄም የሰጠቻትን ቤተልሄም አንድ ለአንድ ከግብ ጠባቂ ጋር ተገናኝታ ወደ ውጪ ሰዳዋለች፡፡ ተቀይራ የገባችሁ ድንቅነሽ በቀለ ሌላ የሚገርም ሙከራን አድርጋ የግቡ ቋሚ መልስበታል፡፡
70ኛው ደቂቃ ላይ ተቀይራ የገባችው ታዳጊዋ አማካይ ሲሳይ ገብረዋህድ ብልጠቷን ተጠቅማ በቀኝ በኩል ባጋደለ መልኩ ያቀበለቻትን ሌላኛዋ ተቀይራ የገባችሁ እፀገነት ብዙነህ ወደ ግብ መታ የአዲስ አበባዋ ተከላካይ አበበች በተራ በግንባር ነክታ ወደ ግብነት ኳሷ ተለውጣለች፡፡ ግቧም በእፀገነት ብዙነህ ተመዝግባለች፡፡ ጨዋታው ሊጠናቀቅ ሲል ጤናዬ ወመሴ መልካም አጋጣሚን አግኝታ ከርቀት መታ ለኢትዮ ኤሌክትሪክ ሁለተኛ ጎል አስቆጠረች ሲባል ግብ ጠባቂዋ ቤተልሄም በግሩም ሁኔታ አውጥታው ጨዋታው 1ለ0 በሆነ በኤሌክትሪክ አሸናፊነት ተደምድሟል፡፡
© ሶከር ኢትዮጵያ