የሁለተኛው ሳምንት የቤትኪንግ ፕሪምየር ሊግ የመጨረሻ ጨዋታ በሀዲያ ሆሳዕና እና ባህር ዳር ከተማ መካከል ተካሂዶ ሆሳዕና በዳዋ ሆቴሳ የመጨረሻ ደቂቃ ጎል ካሸነፈ በኋላ የሁለሁ ቡድኖች አሰልጣኞች አስተያየታቸውን ሰጥተዋል።
አሰልጣኝ አሸናፊ በቀለ – ሀዲያ ሆሳዕና
ስለ ጨዋታው
በጨዋታው አልተደሰትኩም። ከጨዋታው በፊት እኛ እና ባህር ዳር እንጫወታለን ብለን ያሰብነውን ጨዋታ አልተጫወትንም። መከላከል የበዛበት ነበር። መጨረሻ ግን ጎል አስቆጥረን አሸንፈን ወጥተናል። ተጋጣሚያችን ባህር ዳር ግን በጣም ጥሩ ቡድን ነው። ይሄን ሳላደንቅ አላልፍም።
ስለ ተከታታይ ድል
ሁለት ተከታታይ ጨዋታዎችን አሸንፈናል። ይህ በቡድናችን ቀጣይ ሥነ ልቦና ላይ ለሚፈጥረው በራስ መተማመን ትልቅ አስተዋፆኦ አለው። በቀጣይ ያሉብንን ድክመቶች እያረመን በሊጉ ጠንካራ ተፎካካሪ እንሆናለን።
ስለ ዳዋ በቀጣይ ጨዋታ አለመኖር
ዳዋ ለእኛ ክለብ ብቻ አይደለም ለሀገርም የሚጠቅም ተጫዋች ነው። በቀጣይ ጨዋታ የእርሱ አለመኖር በጣም ነው የሚጎዳን።
አሰልጣኝ ፋሲል ተካልኝ – ባህር ዳር ከተማ
ስለ ጨዋታው
በመጀመርያ ለተጋጣሚ ቡድናችን እንኳን ደስ አላችሁ ማለት እፈልጋለሁ። በመቀጠል የመጀመርያው አርባ አምስት ግጭት የበዛበት ዳኛውም በዝምታ ያለፈበት በዚህ ሁኔታ ውስጥ ሆነን የመጨረሻው የማጥቃት መንገዳችን የተበላሸ ነበር። በሁለተኛው አጋማሽ ከሜዳችን ቀስ ብለን ወጥተን በተቃራኒ የሜዳ ክፍል በፍጥነት ለማጥቃት ፈልገን ነበር። ተጋጣሚያችንን ለማጥቃት በምንሄድበት ጊዜ የሚያገኛቸውን ነፃ የሜዳ ክፍል በረጃጅም ኳሶች ሲያጠቃን ነበር። በመጨረሻም ተሳክቶላቸው አሸንፈው ወጥተዋል። እግርኳስ ነው፤ በቀጣይ ስህተቶቻችንን አስተካክለን እንመጣለን።
በአንድ ሽንፈት እና በአንድ ድል ውስጥ ቀጣይ ጉዞ
ገና ረዥም ነው። በየጨዋታው ተጫዋቾቼን ማዘጋጀት ነው የምፈልገው። ዛሬ ከጨዋታው ነጥብ ተጋርተን ብንወጣ ተገቢ ነው ብዬ አምናለሁ። እግርኳስ እንዲህ ነው። ከፊታችን ያሉ ጨዋታዎች በአሸናፊነት እንመለሳለን። በተለይ የመጨረሻው የሜዳ ክፍል ስንደርስ የውሳኔዎች ስህተት በደንብ ይታያሉ፤ እርሱን እንቀርፋለን።
© ሶከር ኢትዮጵያ