የነገውን የወልቂጤ እና ጅማ ጨዋታ የተመለከቱ ሀሳቦችን እንሆ።
ወልቂጤ ከተማዎች ‘ሠራተኞቹ’ የሚለውን ስማቸውን የሚገልፅ የሊግ መክፈቻ አድርገዋል። ከኋላ ተነስተው ከኢትዮጵያ ቡና ነጥብ የተጋሩበትን ጨዋታም እንደመልካም አጀማመር መውሰድ ይቻላል። ያም ቢሆን ቡድኑ በርካታ ሊያሻሽላቸው የሚገቡ ጉዳዮች አላጡትም። በተገጣሚ ላይ ጫና ለመፍጠር የሚሞክር ግን ደግሞ ያልተደራጀ ሙከራው በቡናው ጨዋታ ለጥቃት ሲዳርገው ይታይ ነበር። ይህም ኳስ የመመስረት ባህሪ ባለው የጅማ አማካይ ክፍል ተመሳሳይ ብልጫ እንዲወሰድበት ሊያደርግ ይችላል። በማጥቃቱም ረገድ በአመዛኙ ወደ ውስጥ መግባትን ምርጫቸው የሚያደርጉት የመስመር አጥቂዎቹ እንቅስቃሴ እና የመስመር ተከላካዮች የተገደበ የማጥቃት ሚናም ተሻጋሪ ኳሶችን ለሚፈልገው የፊት አጥቂው አህመድ ሁሴን መነጠል ምክንያት ሲሆንም ይታይ ነበር። በሌላ ጎኑ ደግሞ የአማካዩ አብዱልከሪም ወርቁ መልካም እንቅስቃሴ በነገው ጨዋታም የዓይን ማረፊያ ሊያደርገው ይችላል።
ከተጋጣሚው በተለየ የመጀመሪያው ሳምንት ለጅማ አባ ጅፋር ጥሩ ትዝታን ትቶ ያለፈ አልነበረም። በዚያ ጨዋታ በእጁ ያሉ ተጫዋቾችን መጠቀም አለመቻሉ ፣ ያለውን ግብ ጠባቂ በቀይ ማጣቱ እና በሰፊ ጎል መሸነፉ ለነገው ጨዋታ የተሸናፊነት መንፈስን ይዞ እንዳይመጣ የአሰልጣኞቹ ሚና ከፍ ያለ ይሆናል። ሆኖም ቡድኑ ምንም ያህል በአዳማ ብልጫ ቢወሰድበትም አልፎ አልፎ ኳስ መስርቶ በተረጋጋ ሁኔታ ከሜዳው የወጣባቸው ቅፅበቶች ለነገው ጨዋታ ግብዓት ተደርጎ መወሰድ የሚችል ነው። እንደንጋቱ ገብረስላሴ ፣ ሱራፌል ዓወል እና ተመስገን ደረሰ ዓይነት ተጫዋቾች በግላቸው መልካም እንቅስቃሴ ማድረጋቸውም እንዲሁ ከወልቂጤ ጋር የሚኖረውን ፍልሚያ ተጠባቂ ያደርገዋል።
በጨዋታው የወልቂጤ ከተማዎቹ አዳነ በላይነህ እና ጆርጅ ደስታ በጉዳት እንዲሁም የጅማ አባ ጅፋሩ አቡበከር ኑሪ በቅጣት የማይሳተፉ ሲሆን አሰልጣኝ ጳውሎስ ጌታቸው አዲስ ያስፈረሟቸውን ተጫዋቾች የመጠቀም ፍቃድ ማግኘታቸው ለጅማ መልካም ዜና ሆኗል። ይህ በመሆኑም ጅማ ከመጀመሪያው ጨዋታ አንፃር በርካታ የተጫዋቾች ለውጥ እንደሚያደርግ ይጠበቃል።
የእርስ በእርስ ግንኙነት
– በተሰረዘው የውድድር ዓመት ጅማ አባ ጅፋር በንጋቱ ገብረስላሴ ብቸኛ ግብ ካሸነፈበት ጨዋታ ውጪ ሁለቱ ቡድኖች በሊጉ ለመጀመሪያ ጊዜ ይገናኛሉ።
ግምታዊ አሰላለፍ
ወልቂጤ ከተማ (4-3-3)
ጀማል ጣሰው
ተስፋዬ ነጋሽ – አሚኑ ነስሩ – ዳግም ንጉሴ – ረመዳን የሱፍ
ፍሬው ሰለሞን – ሀብታሙ ሸዋለም – አብዱልከሪም ወርቁ
አሜ መሀመድ – አህመድ ሁሴን – ያሬድ ታደሰ
ጅማ አባ ጅፋር (4-3-3)
ጃኮ ፔንዜ
ወንድምአገኝ ማርቆስ – መላኩ ወልዴ – ከድር ኸይረዲን – ኤልያስ አታሮ
ሀብታሙ ንጉሴ – ንጋቱ ገብረስላሴ – ሱራፌል ዐወል
ተመስገን ደረሰ – ሳምሶን ቆልቻ – ሳድቅ ሴቾ
© ሶከር ኢትዮጵያ