ቅድመ ዳሰሳ | ፋሲል ከነማ ከ ኢትዮጵያ ቡና

ሁለተኛው የሊጉ ሳምንት ሁለተኛ ቀን የሚጀምርበትን ጨዋታ ላይ ተከታዮቹን ነጥቦች አንስተናል።

ሊጉን በድል የጀመረው ፋሲል ከነማ ሌላኛውን የመዲናዋን ክለብ በመግጠም ሁለተኛውን ጨዋታ ያደርጋል። ቅዱስ ጊዮርጊስን ባሸነፈበት ግጥሚያ ላይ ከሌሎቹ ቡድኖች የተሻለ ንቃት የታየበት ፋሲል በአፍሪካ ኮንፌዴሬሽን ዋንጫ ጨዋታዎች ላይ መሳተፉ እንደጠቀመው በግልፅ ታይቷል። ከጨዋታ ዝግጁነት ባለፈ በጊዮርጊሱ ጨዋታ ጥሩ ሆኖ የታየው የሀብታሙ ተከስተ እና ይሁን እንዳሻው ጥምረት ነገም ከኢትዮጵያ ቡና ፈጣሪ አማካዮች ጋር ብርቱ ፉክክር ይጠብቀዋል። በአመዛኙ በሱራፌል ዳኛቸው የማጥቃት ሚና ላይ የተመሰረተው እና በሽመክት ጉግሳ አቅጣጫ በሚያመዝነው የቡድኑ የማጥቃት ኃይል ካለፈው ጨዋታ በተለየ በተጋጣሚው የተከላካይ ክፍል ላይ ከኳስ ውጪ ጫና ለመፍጠር ሊንቀሳቀስ ይችላል ተብሎም ይጠበቃል።

በእጁ የገባውን ውጤት አሳልፎ የሰጠው ኢትዮጵያ ቡና ነገ የመጀመሪያ ሙሉ ሦስት ነጥቡን ለማግኘት ይጫወታል። ኳስ ከኋላ ሲጀምር በተጋጣሚ የፊት መስመር ተሰላፊዎች በቀላሉ ጫና ውስጥ ሲገባ እና ከትኩረት ማነስ ስህተቶችን ሲሰራ የታየው ቡድኑ በንፅፅር ከወገብ በላይ የተሻለ ውህደትን አሳይቷል። በአቡበከር ነስሩ የግራ መስመር እንቅስቃሴ የሚመራው ማጥቃቱ የኳስ ቅብብሉ ከራሱ ሜዳ ከወጣ በኃላ የተሻለ ፍጥነት ይታይበታል። የኋላ ክፍሉን ከጫና የማላቀቅ እና በቶሎ የፊት መስመሩን በቅብብሎች ማግኘት የሚጠበቅበት የፍቅረየሱስ እና ታፈሰ ጥምረት ነገ በተመሳሳይ የኳስ ቁጥጥር ፍላጎት ካለው የፋሲል አማካይ መስመር ጋር ከባድ ፍልሚያ የሚጠብቀው ይሆናል።

ጥሩ ፉክክር ያስመለክተናል ተብሎ በሚጠበቀው በዚህ ጨዋታ በቡድኖቹ የማጥቃት ሂደት ውስጥ ሽመክት ጉግሳን ከኃይሌ ገብረትንሳይ አቡበከር ነስሩን ከሰዒድ ሁሴን የሚያገናኙ ቅፅበቶች ተጠባቂ ይሆናሉ።

እርስ በእርስ ግንኙነት

– ከ2009 የውድድር ዓመት ጀምሮ ክለቦቹ በተገናኙባቸው ስድስት ጨዋታዎች ተመጣጣኝ ውጤት አላቸው። ሁለት ሁለት ጊዜ ሲሸናነፉ ሁለት ጊዜ ያለግብ ተለያይተዋል። ኢትዮጵያ ቡና ሰባት ፋሲል ከነማ ደግሞ አምስት ግቦችን አስቆጥረዋል

ግምታዊ አሰላለፍ

ፋሲል ከነማ (4-3-3)

ሚኬል ሳማኬ

ሰዒድ ሀሰን – ከድር ኩሊባሊ – ያሬድ ባየህ – አምሳሉ ጥላሁን

ይሁን እንደሻው – ሀብታሙ ተከስተ

በረከት ደስታ – ሱራፌል ዳኛቸው – ሽመክት ጉግሳ

ሙጂብ ቃሲም

ኢትዮጵያ ቡና (4-3-3)

አቤል ማሞ

ኃይሌ ገብረትንሳይ – ወንድሜነህ ደረጄ – አበበ ጥላሁን – አስራት ቱንጆ

ታፈሰ ሰለሞን – አማኑኤል ዮሀንስ – ፍቅረየሱስ ተ/ብርሀን

ሚኪያስ መኮንን – ሀብታሙ ታደሰ – አቡበከር ናስር


© ሶከር ኢትዮጵያ