ሴቶች ፕሪምየር ሊግ | ጌዲኦ ዲላ እና አቃቂ ቃሊቲ ነጥብ ተጋርተዋል

በኢትዮጵያ ሴቶች ፕሪምየር ሊግ አንደኛ ዲቪዚዮን የሁለተኛ ሳምንት የመጀመሪያ ጨዋታ ጌዲኦ ዲላ እና አቃቂ ቃሊቲ 1ለ1 ተለያይተዋል፡፡

በሀዋሳ እየተደረገ ያለው የኢትዮጵያ ሴቶች ፕሪምየር ሊግ አንደኛ ዲቪዚዮን ሁለተኛ ሳምንተት የመጀመሪያ ጨዋታ ዛሬ ቀን 10:00 ሰአት በጌዲኦ ዲላ እና አቃቂ ቃሊቲ መካከል ተደርጓል፡፡ ብዙም ማራኪ ያልሆነ እና ብኩን ኮሶች በበረከቱበት በዚህ ጨዋታ ሁለቱም ክለቦች ግብ ያስቆጥሩ እንጂ የሰላ የፊት ተጫዋች የሌላቸው በመሆኑ አብዛኛዎቹ ኳሶች የመጨረሻ ማረፊያቸው ውጤታማ ያልነበር ነበር፡፡ አቃቂዎች በመጀመሪያው አጋማሽ በሄለን መሰለ አማካኝነት ወደ ጌዲኦ የግብ ክልል መድረስ ችሏል፡፡ 15ኛው ደቂቃ ላይ ከመሀል ሜዳው ወደ ዲላዎች ግብ ክልል በተጠጋ ቦታ ያገኙትን ቅጣት ምት አስናቀች ትቤሶ በቀጥታ ወደ ግብ ስትመታ ግብ ጠባቂ መኪያ ከድር በአግባቡ መቆጣጠር ሳትችል በተጨራረፈ ንክኪ የትምወርቅ አሸናፊ እግር ስር ደርሶ ወደ ጎልነት ለውጣው አቃቂን ቀዳሚ አድርጋለች፡፡ወደ መልበሻ ክፍል ሊያመሩ አንድ ደቂቃ ሲቀረው የአቃቂ ተከላካዮች በጉልህ የሰሩትን የአቋቋም ስህተት ዘንድሮ ሀዋሳን ለቃ ጌዲኦ ዲላን የተቀላቀለችሁ ይታገሱ ተገኝወርቅ ግሩም ጎል አስቆጥራ ቡድኗን አቻ አድርጋለች፡፡

ሁለተኛው አጋማሽ ተመሳሳይ አሰልቺነቱን ይዞ የቀጠለው ጨዋታ መሐል ሜዳ ላይ ያመዘነ እና በተጫዋቾች የግል እንቅስቃሴ ብቻ የታጀበ ነበር፡፡ በተለይ በአቃቂ በኩል አማካዮቹ ኪፊያ አብዱራሂም እና ዙለይካ ጁሀድ የሚያገኙት ኳስ በጥሩ ቅብብል ወደ ተቃራኒ ቡድን በተደጋጋሚ ማድረስ ቢችሉም የኳሱ ማረፊያ ግን ውጤት አልባ ነበር፡፡ ጌዲኦ ዲላዎችም በቱሪስት ለማ ከርቀት ካደረጉት ሙከራ ውጪ የጎላ ዕድልን መፍጠር ሳይችሉ ቀርተዋል፡፡ በአጋማሹ ቡድኖቹ ባደረጉት ደካማ እንቅሴቃሴ ባለፈ የእለቱ ዋና ዳኛ መዳብ ተደጋጋሚ የውሳኔ ስህተት ሌላኛው የዚህ ጨዋታ ድክመት ነበር፡፡


ጨዋታው 1ለ1 ከተጠናቀቀ በኃላ የአቃቂ ቃሊቲዋ አማካይ ኪፊያ አብዱራሂም የልሳን የሴቶች ስፖርት የጨዋታ ኮከብ ተብላ ተሸልማለች፡፡

– ከውድድሩ ጋር በተያያዘ በርካታ ክለቦች ወሳኝ ተጫዋቾቻቸው ኮሮና ቫይረስ እየተገኘባቸው በመሆኑ ቡድናቸው ላይ እክል እየፈጠረባቸው መሆኑን ነግረውናል፡፡

– በአንፃሩ ፌዴሬሽኑ የጫማ ማፅጃ እንዲሁም ኳሶችን እና የስታዲየሙን ወሳኝ ቦታዎች በተመሳሳይ በፀረ ተዋህስያን ሲያጥብ በዛሬው ጨዋታ መመልከታችን የሚያበረታታ ተግባር በመሆኑ ሊበረታታ ይገባል እንላለን፡፡


© ሶከር ኢትዮጵያ