የአሰልጣኞች አስተያየት | አዳማ ከተማ 0-2 ወላይታ ድቻ

የአዳማ እና ድቻ ጨዋታን መጠናቀቅ ተከትሎ የቡድኖቹ አሰልጣኞች ከሱፐር ስፖርት ጋር ያደረጉት ቆይታ ይህንን ይመስላል።


አሰልጣኝ ደለለኝ ደቻሳ – ወላይታ ድቻ

ስለጨዋታው

“ኳሱን መስርተን ለመጫወት ነበር ተዘጋጅተን የመጣነው። ሙሉ ለሙሉ ባይባልም ፣ መስተካከል ያለባቸው ነገሮች ቢኖሩም ኳስ ይዘን ለመጫወት ሞክረናል። በመጀመሪያው አጋማሽ ተሳክቶልናል ብዬ አስባለሁ። እኛ ሜዳ ላይ ጀምረን የእነሱን ጀርባ ለመጠቀም ነበር የሰራነው። ባለፈው የሰራናቸውን ስህተቶች ለመቅረፍ ሙከራ አድርገናል። እግር ኳስ ሂደት ነው እና በሂደት ወደምንፈልገው ደረጃ እንደርሳለን ብዬ አስባለሁ። ነገር ግን ውጤት አስፈላጊ ነገር ነው ፤ ዛሬ በማሸነፋችን ደስ ብሎኛል።”

ስለቀጣይ ጨዋታዎች…

“እግር ኳስ ሂደት ነው ብያለሁ። ለውጦች ያስፈልጉናል እነዛ ለውጦች ላይ መስራት እንዳለብን እናምናለን። በአዕምሮም ልጆቹ ወጣት ስለሆኑ እነሱ ላይ መስራት ያለብን ብዙ ነገር አለ። እነዛን ስራዎች እየሰራን እንደየጨዋታው የምንጠቀማቸውን ተጫዋቾች እየተጠቀምን እንሰራለን ብዬ ነው የማስበው።”

አሰልጣኝ አስቻለው ኃይለሚካኤል – አዳማ ከተማ

ስለጨዋታው…

“መጀመሪያ ላይ በመዘናጋታችን ጎሎቹ ተቆጥረውብናል። ራሳችን በፈጠርናቸው ጥቃቅን ስህተቶች ነው ፤ የመጀመሪያው 15 ደቂቃ ላይ ጥንቃቄ ማድረግ ነበረብን። በሁለተኛው አጋማሽ ያን ስህተት አርመን ተሻሽለን ቀርበናል። በተጫዋቾች ጉዳት እና ሌሎች ምክንያቶች ያልገቡ ተጫዋቾች አሉ። በሚቀጥለው ተሻሽለን እንቀርባለን።”

ስለቀጣይ ጨዋታ

“ስህተትህን አይተህ በቀጣይ ጨዋታ እርማት አድርገህ ልምምድ ሰርተህ ነው የምትጫወተው። ከስህተታችን ተምረን ለመቅረብ እንሞክራለን በእግርኳስ መሸነፍ ማሸነፍ ያለ ነው። በፀጋ እንቀበላለን ፤ ድቻዎችን እንካን ደስ ያላችሁ እላለሁ።”


© ሶከር ኢትዮጵያ