ሪፖርት | የዳዋ ሆቴሳ ልዩነት ፈጣሪነት ቀጥሏል

የሁለተኛው ሳምንት የመጨረሻ ጨዋታ በሀዲያ ሆሳዕና እና ባህር ዳር ከተማ መካከል ተደርጎ ሀዲያ ሆሳዕና 1-0 በመጨረሻ ደቂቃ ጎል አሸናፊ ሆኗል።

ሀዲያ ሆሳዕና ወላይታ ድቻን ከረታበት ጨዋታ ጋር ሲተያይ ባደረገው ሁለት የተጫዋች ለውጥ መድኃኔ ብርሀኔን እና ሳሊፉ ፎፋናን አሳርፎ ለተስፋዬ በቀለ እና ለተስፋዬ አለባቸው የመሰለፍ ዕድልን ሰጥቷል። የሁለት ተጫዋች ለውጥ ያደረጉት ባህር ዳር ከተማዎች ደግሞ በሲዳማው ድላቸው ካስጀመሩት ቡድን ውስጥ አህመድ ረሺድ እና ግርማ ዲሳሳን አሳርፈው ሣላአምላክ ተገኝ እና ምንይሉ ወንድሙን አሰልፈዋል።

የመጀመሪያው አጋማሽ ለዓይን አሰልቺ የሚባል ዓይነት ባይሆንም የጨዋታውን ተጠባቂነት የሚመጥን ግን አልነበረም። ጥቂት የግብ ሙከራዎች የታዩበት እና የኃይል አጨዋወት ላይ ያተኮረው አጋማሹ በርካታ የርቀት ቅጣት ምቶች የተመለክትንበትም ነበር። 10ኛው ደቂቃ ላይ ከኋላ በረጅሙ የተላከ እና ሄኖክ አርፌጮ በግንባር ለመሀመድ ሙንታሪ ለማቀበል የሞከረውን ኳስ ዜናው ፈረደ አግኝቶ በቀጥታ ሞክሮ ሙንታሪ ያዳነበት የጨዋታው የመጀመሪያ ሙከራ ነበር። ከዚህ ሙከራ በኋላ ባህር ዳሮች በመከላከል ወቅት ከኋላ አምስት የሚሆነውን የተጋጣሚያቸውን አጥር በቅብብሎች ለማለፍ የቻሉባቸው አጋጣሚዎች ጥቂት ነበሩ።

ከሄኖክ አርፌጮ እና ዳዋ ሆቴሳ የርቀት ኢላማቸውን ያልጠበቁ ሙከራዎች ውጪ ንፁህ የግብ ዕድል መፍጠር ያልቻሉት ሀዲያ ሆሳዕናዎችም በማጥቃት ወቅት ፊት መስመራቸው ላይ የቁጥር ብልጫ ይወሰድባቸው ስለነበር በቀላሉ በባህርዳሮች ቁጥጥር ስር ውለዋል። ተቀዛቅዞ እና መሀል ላይ በሚደረጉ ጉሽሚያዎች ታጅቦ የተጠናቀቀው አጋማሽ ሌላ ሙከራ የታየበት 38ኛው ደቂቃ ላይ ነበር። ዜናው ፈረደ ከፍፁም ዓለሙ የተቀበለውን ኳስ ከቀኝ መስመር ይዞ ገብቶ ሲሞክር ሙንታሪ አድኖበታል።

ሁለተኛው አጋማሽ ሲጀምር በሄኖክ አርፌጮ ቦታ ሳሊፍ ፎፋናን ቀይረው ያስገቡት ሆሳዕናዎች ከአራት ተከላካዮች ወደሚጀምረው አደራደራቸው ተመልሰዋል። ቅያሪውን ተከትሎ ሀዲያዎች ፊት ላይ በርከት ብለው ቢታዩም የመጀመሪያ ሙከራቸውን ያደረጉት 62ኛው ደቂቃ ላይ ነበር። በሙከራው ሳሊፍ ፎፋና ከአዲስ ህንፃ የተቀበለውን ኳስ ገፍቶ ከሳጥን ውስጥ ቢሞክርም ሀሪሰን ሄሱ በቀላሉ አድኖበታል። ባህር ዳሮችም የተጋጣሚያቸው የኋላ ክፍል አንድ ሰው ቢቀንስም እንደተጠበቀው በቶሎ የመጨረሻ ዕድሎችን ሲፈጥሩ አልታዩም። የተሻለ በነበረው የቡድኑ ሙከራ 70ኛው ደቂቃ ላይ ሚኪያስ ግርማ ከቀኝ በረጅሙ ያሻማውን ኳስ ምንይሉ ወንድሙ ከግራ አቅጣጫ በቀጥታ ሞክሮ ወደ ውጪ ወጥቶበታል።

ሀዲያዎች ዱላ ሙላቱን ዘግየት ብለውም አልሀሰን ካሉሻን ቀይረው በማስገባት የማጥቃት ጉልብፕታቸውን በመጨመር የተሻለ ጫና ሲፈጥሩ ታይተዋል። ዳዋ ሆቴሳ 80ኛው ደቂቃ ላይ ከግራ መስመር ከሚኪያስ ጋር ታግሎ ወደ ውስጥ በመግባት አክርሮ የመታውም ኳስ ለጥቂት ነበር በግቡ ወግዳሚ ስር የወጣው። አህመድ ረሺድ እና ሄኖክ አወቀን ቀይረው ያስገቡት ባህር ዳሮችም የማጥቃት አማራጬቻቸውን ለማስፋት ቢጥሩም እየተፈጠረባቸው የነበረውን የሀዲያን ማጥቃት የዘነጉት ይመስሉ ነበር። በመሆኑም በጭማሪ ደቂቃ ከተጠባባቂ ወንበር በመነሳት ልዩነት እየፈጠረ የሚገኘው ዱላ ሙላቱ ከቀኝ መስመር በረጅሙ የላከውን ኳስ ዳዋ ሆቴሳ ከተከላካዮች ጀርባ በመገኘት በቀጥታ መትቶ በማስቆጠር ቡድኑን ባለድል ማድረግ ችሏል።

ዳዋ ጎሉን ማስቆጠሩን ተከትሎ ወደ ደጋፊዎች ሄዶ ደስታውን በመግለፁ በሁለተኛ ቢጫ ከሜዳ ተወግዷል።



© ሶከር ኢትዮጵያ