ሪፖርት | በአወዛጋቢ ዳኝነት በታጀበው ጨዋታ ኢትዮጵያ ቡና ተከታታይ ድሉን አስመዝግቧል

በቤትኪንግ የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ ሦስተኛ የጨዋታ ሳምንት የመጀመሪያ ቀን ሁለተኛ ጨዋታ በአወዛጋቢ ውሳኔዎች ታጅቦ ኢትዮጵያ ቡና ድሬዳዋ ከተማን 3-2 በሆነ ውጤት አሸችሏል። 

ኢትዮጵያ ቡናዎች ባሳለፍነው ሳምንት ፋሲል ከነማን ከረታው ስብስብ ውስጥ ሁለት ለውጦችን ሲያደርጉ ተመስገን ካስትሮና አቡበከር ናስርን አስወጥተው በምትካቸው ምንተስኖት ከበደና ሚኪያስ መኮንን በማስገባት ሲጀምሩ በአንፃሩ ድሬዳዋ ከተማዎች በቅዱስ ጊዮርጊስ ከተረታው ስብስብ ውስጥ አራት ለውጦችን ያደረጉ ሲሆን በዚህም ፍሬዘር ካሳ፣ አስጨናቂ ሉቃስ፣ ሱራፌል ጌታቸውና እንዳለ ከበደን አስወጥተው በምትካቸው በረከት ሳሙኤል፣ አስቻለው ግርማ፣ ሙኅዲን ሙሳ እና ኢታሙና ኬይሙኒን ወደ መጀመሪያ አሰላለፍ አስገብተዋል።

አዝናኝ በነበረው የሁለቱ ቡድኖች የመጀመሪያ አጋማሽ ጨዋታ ገና በማለዳ ነበር የመጀመሪያው ግብ የተቆጠረው በ7ኛው ደቂቃ የኢትዮጵያ ቡናው የግራ መስመር ተከላካይ አስራት ቱንጆ ተጫዋቾችን አልፎ ከግራ መስመር አጥብቦ በመግባት ያቀበለውን ኳስ ሀብታሙ ታደሰ ግብጠባቂውን አልፎ በማስቆጠር ቡድኑን ቀዳሚ ማድረግ ችሏል።

በመጀመሪያው አጋማሽ ኢትዮጵያ ቡናዎች ኳስ በቁጥጥራቸው ውስጥ ሲሆን ተጫዋቾች በተጋጣሚ አጋማሽ በቁጥር በርከት ማለታቸውን ተከትሎ ድሬዳዋ ከተማዎች ኳስ ሲያገኙ በፈጣን ሽግግሮች የሚቀመሱ አልነበሩም። በዚህም ሒደት ጥሩ ጥሩ የግብ አጋጣሚዎችን በፈጣን ሽግግሮች መፍጠር ችለው ነበር። ድሬዳዋ ከተማዎች በ16ኛው ደቂቃ ጁኒያስ ናንጂቡ ከሳጥን ውጭ በቀጥታ ወደ ግብ የላከውን ኳስ ተክለማርያም ሻንቆ መትፋቱን ተከትሎ ሙኅዲን ሙሳ ከግቡ የቅርብ ርቀት ያገኘውን ኳስ በአስገራሚ መልኩ ከግቡ አናት በላይ በሰደዳት ኳስ የመጀመሪያ ሙከራቸውን ማድረግ ችለዋል።

በ27ኛው ደቂቃ በፈጣን ሽግግር የተገኘውን ኳስ አስቻለው ግርማ ከቀኝ መስመር ሰብሮ በመግባት በተሻለ አቋቋም ላይ ለነበረው ኢታሙና ኬይሙኒ ያቀበለውን ኳስ አጥቂው ከሳጥን ውስጥ በግሩም አጨራረስ ለድሬዳዋ ከተማ የአቻነቷን ግብ ማስገኘት ችሏል።

በ36ኛው ደቂቃ ኢትዮጵያ ቡና መሪነታቸውን ከፍ ሊያደርጉበት የሚችሉትን አጋጣሚ ታፈሰ ሰለሞን ላይ ዘነበ ከበደ የሰራውን ጥፋት ተከትሎ በተገኘ የፍፁም ቅጣት ምት ቢያገኙም ራሱ ታፈሰ ሰለሞን የመታውን ፍሬው ጌታሁን ሊያድንበት ችሏል።

በሁለተኛው አጋማሽ ድሬዳዋ ከተማዎች በመጀመሪያው አጋማሽ የነበረው የፈጣን ሽግግሮች የመጠቀም ፍላጎት ሙሉ ለሙሉ አጥተው ሲገቡ በአንፃሩ ቡናዎች ከመጀመሪያው አጋማሽ የተሻለ የማጥቃት ፍላጎትን አሳይተዋል።

በ55ኛው ደቂቃ አወዛጋቢ በነበረው ክስተት ታፈሰ ሰለሞን ወደ ውስጥ ለማሻገር የሞከርውን ኳስ በረከት ሳሙኤል ተንሸራቶ ሲያወጣ በእጅ ነክቷል በሚል የእለቱ ዳኛ ብርሀኑ መኩርያ አጨቃጫቂ ፍፁም ቅጣት ምት መስጠታቸውን ተከትሎ አማኑኤል ዮሐንስ በመምታት ቡድኑን ዳግም ወደ መሪነት ያመጣች ግብ አስቆጥሯል።

ድሬዳዋ ከተማዎች ቀዝቀዝ ብለው በታዩበት የሁለተኛው አጋማሽ በ50ኛው ደቂቃ ኤልያስ ማሞ ወደ ግራ ካደላ የቅጣት ምት በቀጥታ የሞከረው ኳስ የግቡ ቋሚ የመለሰበት እንዲሁም በ74ኛው ደቂቃ ተቀይሮ የገባው ሱራፌል ጌታቸው ሞክሮ ተክለማርያም ሻንቆ ያዳነበት ኳስ ተጠቃሽ ሙከራዎች ነበሩ። በእነዚህ ደቂቃዎች ድሬዳዋዎች ለጎል ባደረጉት ሙከራ ሒደት አበበ ጥላሁን ኳስ በእጁ በመንካቱ ፍፁም ቅጣት ምት ተከልክለናል በሚል ቅሬታቸውን አሰምተዋል።

ጨዋታው ቀጥሎ በ84ኛው ደቂቃ ከመጀመሪያው የኢትዮጵያ ቡና ግብ ጋር በሚመሳል ሒደት አቤል ከበደ ወደ ውስጥ ያሻገረውን ኳስ አሥራት ቱንጆ ወደ ግብ ሲልከው ሀብታሙ ታደሰ አግኝቶት የኢትዮጵያ ቡናን የማሳረጊያ ግብ ሲያስገኝ በደቂቃዎች ልዩነት ጁንያስ ናንጄቦ ላይ በተሰራ ጥፋት የተገኘውን የፍፁም ቅጣት ምት ዘነበ ከበደ አስቆጥሮ ጨዋታው 3-2 እንዲጠናቀቅ አስችለዋል።

በጨዋታው ዳኝነት ደስተኛ ያልነበሩት የድሬዳዋ ከተማ ተጫዋቾች የኃይል አጨዋወትን የመረጡ ሲሆን በዚህም በጨዋታው መገባደጃ ደቂቃዎች በረከት ሳሙኤልና ዳንኤል ደምሴን በሁለተኛ ቢጫ ካርድ ከሜዳ ለማጣት ተገደዋል።


© ሶከር ኢትዮጵያ