አቤል ያለው በደመቀበት የሦስተኛው ሳምንት የመጀመሪያ ጨዋታ ቅዱስ ጊዮርጊስ ሀዋሳ ከተማን 4-1 አሸንፏል።
ቅዱስ ጊዮርጊስ ድሬዳዋ ከተማን ሲያሸንፍ ከተጠቀመበት የመጀመሪያ አሰላለፍ ውስጥ ጋዲሳ መብራቴን በጌታነህ ከበደ የቀየረበትን ብቸኛ ለውጥ አድርጓል። ሀዋሳ ከተማ በበኩሉ በሰበታው ሽንፈት ጉዳት ያስተናገዱት መስፍን ታፈሰ እና ምኞት ደበበን ጨምሮ ብርሀኑ በቀለ ፣ ዓባይነህ ፊኖ እና ዘነበ ከድርን በማሳረፍ በምትካቸው አዲስዓለም ተስፋዬ ፣ ዳንኤል ደርቤ ፣ ደስታ ዮሐንስ ፣ ዘላለም ኢሳይያስ እና ዮሐንስ ሴጌቦን አሰልፏል።
የመጀመሪያው አጋማሽ የጨዋታ እንቅስቃሴ ቀዝቀዝ ብሎ የጀመረ ነበር። ሁለቱም ተጋጣሚዎች ኳስ ተቆጣጥረው ለመጫወት በሞከሩባቸው የመጀመሪያ ደቂቃዎች እንቅስቃሴው መሀል ሜዳ ላይ ተወስኖ ቆይቷል። ቀስ በቀስ ለተጋጣሚ ሜዳ የቀረበ እንቅስቃሴ ማድረግ የጀመሩት ጊዮርጊሶች 19ኛው ደቂቃ ላይ በጌታነህ ከበደ አማካይነት ሁለት ሙከራዎችን አድርገዋል። 22ኛው ደቂቃ ላይ ሀዋሳዎች ከማዕዘን ምት ያገኙትን ዕድል ሳይጠቀሙ ከሄኖክ ድልቢ የተቀማውን ኳስም አቤል ያለው ግብ ድረስ በመንዳት መሞከር ችሎ ነበር። ከዚህ በኋላ የተሻለ መነቃቃት ታይቶባቸው የነበሩት ሀዋሳዎች ወደ ጊዮርጊስ ሜዳ ኳስ ይዘው የገቡባቸውን አጋጣሚዎች ቢፈጥሩም ከጋብርኤል አህመድ የርቀት ሙከራው ውጪ ሌላ ዕድል ማግኘት አልቻሉም።
የሀዋሳዎችን መነቃቃት በቶሎ ማክሰም ለቻሉት ቅዱስ ጊዮርጊሶች ቀሪዎቹ የአጋማሹ ደቂቃዎች የፌሽታ ሆኖላቸዋል። 33ኛው ደቂቃ ላይ አቤል ያለው በግራ መስመር አዲስዓለም ተስፋዬን በማለፍ ገብቶ ያቀበለውን ያለቀለት ኳስ ሮቢን ንጋላንዴ ከመረብ አሳርፏል። ከአምስት ደቂቃዎች በኋላም በደጋሚ አቤል ከሶሆሆ ሜንሳህ ጋር ተገናኝቶ በተሰራበት ጥፋት ፍፁም ቅጣት ምት ተሰጥቶ ጌታነህ ከበደ ሁለተኛውን ጎል ማስቆጠር ችሏል። ከሀዋሳዎች ቁጥጥር ውጪ የሆነው አቤል ያለው እንደገና ከግራ መስመር ለጌታነህ አመቻችቶ ያቀበለውንም ኳስ ጌታነህ በግንባሩ በመግጨት 43ኛው ደቂቃ ላይ ሦስተኛ ጎል አድርጎታል። ጊዮርጊሶች ጨዋታው ወደ ዕረፍት ከማምራቱ በፊትም በአዲስ ግደይ ያደረጉት ሌላ ሙከራም በግቡ አግዳሚ የተመለሰ ነበር።
ሁለተኛው አጋማሽ ጌታነህ ከአዲስ ተቀብሎ ከሳጥኑ መግቢያ ላይ ባደረገው ሙከራ ጀምሯል። አጥቂው 50ኛው ደቂቃ ላይም የአቤልን የማዕዘን ምት በግንባሩ ሞክሮ ለጥቂት ወጥቶበታል። ሀዋሳዎች አሁንም ቅብብሎችን ሲከውኑ ቢታዩም ወደ ፊት ማለፍ ግን አልሆነላቸውም። 53ኛው ደቂቃ ላይ ዮሐንስ ሴጌቦ ከዘላለም ኢሳይያስ ተቀብሎ ከርቀት ካደረገው ሙከራ ሁለት ደቂቃ በኃላ አራተኛ ግብ አስተናግደዋል። አቤል ያለው ያነሳው የማዕዘን ምት ጋብርኤል አህመድን ቀይሮ በገባው ዳዊት ታደሰ ተጨርፎ ከመረብ አርፏል። 65ኛው ደቂቃ ላይም የጌታነህ ከበደ የሳጥን ውጪ ሙከራ ግብ ሳይሆን የቀረው በግቡ አግዳሚ ተመልሶ ነበር።
በተቀዛቀዘ እንቅስቃሴ ወደ ማብቂያው በተቃረበው ጨዋታ በመጠኑ የተነቃቁት ሀዋሳዎች ከዮሐንስ ሴጌቦ የተመታን ኳስ ምንተስኖት አዳነ ያገኙትን ፍፁም ቅጣት ምት ብሩክ በየነ ወደ ግብ መለወጥ ችሏል። በቀጣዮቹ ደቂቃዎችም ሀዋሳዎች የተሻለ ጫና ሲፈጥሩ ተስተውለዋል። በሄኖክ ድልቢ እና ዮሃንስ ሴጌቦ አማካይነት ያደረጋቸው ሙከራዎችም ውጤቱን ለማጥበብ የተቃረቡ ነበሩ። ሆኖም የአብስራ ተስፋዬ ፣ ከነዓን ማርክነህ እና አማኑኤል ገብረሚካኤልን አከታትለው አስገብተው የነበሩት ጊዮርጊሶች በቀሪዎቹ ደቂቃዎች የሀዋሳን ጫና ቀንሰው ጨዋታውን በ 4-1 ውጤት ጨርሰዋል።
© ሶከር ኢትዮጵያ