ኢትዮጵያ ቡና ተጨማሪ ስፖንሰር ሊያገኝ ነው

ከቅርብ ጊዜያት ወዲህ ክለቡን በፋይናስ አቅሙ ጠናከራ ለማድረግ ከሚሰሩ ተግባራቶች መካከል አንዱ እንደሆነ የተነገረለት የስፖንሰር ስምምነት ኢትዮጵያ ቡና ሊፈፅም ነው።

ከቡና ላኪዎች፣ ከሀበሻ ቢራ፣ ከስታዲየም ገቢ እና በተለያዩ መንገዶች ከሚሰበሰቡ ዓመታዊ ገቢዎች ብቻ እየተንቀሳቀሰ የሚገኘው ኢትዮጵያ ቡና በቅርቡ ለክለቡ የፋይናስ አቅም ግንባታ አንድ እርምጃ ወደ ፊት እንደሚያስኬድ የታመነበት የስፖንሰር ስምምነት ከሁለት ተቋማት ጋር እንደሚያደርግ ሰምተናል።

አንደኛው ተቋም ማን እንደሆነ ለጊዜው መረጃውን ለማግኘት ያደረግነው ጥረት ባይሳካም አንደኛው ቡና ኢንተርናሽናል ባንክ እንደሆነ ለማረጋገጥ ችለናል። ከረቡዕ ጀምሮ ኢትዮጵያ ቡና ባለሜዳ በሚሆንበት ጨዋታ ሁሉ የቡና ባንክ ማስታወቂያ እንደሚቀመጥ አረጋግጠናል። አጠቃላይ በስምምነቱ ዙርያ እና ኢትዮጵያ ቡና ከስፖንሰሮቹ የሚያገኘውን ጥቅም አስመልክቶ በቅርቡ ዝርዝር መረጃ በይፋ እንደሚሰጥ ለማወቅ ተችሏል።

ክለቡን በበላይነት የሚመሩት አካላት ከቅርብ ጊዚያት ወዲህ ክለቡን ለማዘመን እና ከአነስተኛ ገቢዎች አላቀው ጠንካራ ቁመና ያለው ህዝባዊ ክለብ እንዲሆን ለማድረግ ወደ ፊትም የተለያዩ ተግባሮች እያከናወኑ እንደሚገኙ መረጃዎች እየወጡ ይገኛል።


© ሶከር ኢትዮጵያ