በኢትዮጵያ ሴቶች ፕሪምየር አንደኛ ዲቪዚዮን የአንደኛ ሳምንት የመጨረሻ ጨዋታ ዛሬ ሲቀጥል ኢትዮጵያ ንግድ ባንክ አርባምንጭ ከተማን 8 ለ 0 ረምርሟል፡፡
ብዙም ሳቢ ያልሆነ ነገር ግን የንግድ ባንክ ተጫዋቾች የካበተ ልምድ የአሰልጣኝ ብርሀኑ ግዛውን ቡድን ለውጤታማነት ያበቃ የዛሬው ጨዋታ የመጀመሪያ አጋማሸ ትዕይንት ነበር፡፡ ንግድ ባንኮች ገና ጨዋታው በተጀመረ 2ኛ ደቂቃ ኳስ እና መረብን አገናኝተዋል፡፡ ህይወት ዳንጊሶ መሐል ለመሐል የሰጠቻትን ኳስ እመቤት አዲሱ ግሩም ግብ አስቆጥራ ቡድኗን መሪ ማድረግ ችላለች፡፡ አርባምንጭ ከተማዎች ግብ ለማስቆጠር ጥረት ከማድረግ ያገዳቸው ባይኖርም ረጃጅም ኳሶችን ከተለያየ አቅጣጫ ወደ ሰናይት ባሩዳ በሚያሻግሩበት ወቅት ተጫዋቿን ሊረዳት የሚችል አጋዥ ማግኘት ባለመቻሏ በተደጋጋሚ ኳሶቹ ይመክኑ ነበር፡፡ ይሁንና ግብ ለማስቆጠር እንከን ያልታየባቸው ባንኮች ሁለተኛ ግባቸውን አስቆጥረዋል፡፡ 23ኛው ደቂቃ የማልታውን ክለብ ቢርኪርካራን ለቃ ክለቡን የተቀላቀለችው ሎዛ አበራ ከርቀት ግብ አስቆጥራ የቡድኗን የግብ መጠን ወደ ሁለት ከፍ አድርጋለች፡፡
በፊት መስመር ላይ ተሰላፊ የነበረችው ሎዛ አበራ መቀዛቀዝ ቢታይባትም ሌላኛዋ አዲስ ፈራሚ አረጋሽ ካልሳ የምትቀመስ አልነበረችም። የብርቱካን ገብረክርስቶስን ተሻጋሪ ኳስ ያገኘችው አማካዩዋ ግሩም ግብ ከመረብ አዋህዳ የግብ መጠኑን አሳድጋለች፡፡ 36ኛው ደቂቃ ላይ የአርባምንጯ ግብ ጠባቂ ድንቡሽ አባ ስህተት ታክሎበት ሰናይት ቦጋለ አራተኛ ግብ ስታስቆጥር ጨዋታው ወደ መልበሻ ክፍል ሊያመራ ሁለት ደቂቃ ሲቀረው አረጋሽ ካልሻ ለራሷ ሁለተኛ ለንግድ ባንክ አምስተኛ ግብ ከመረብ አዋህዳለች፡፡
ከእረፍት መልስ ከመጀመሪያው አጋማሽ እንቅስቃሴያቸው በመጠኑ መሻሻል የታየባቸው ንግድ ባንኮች የአርባምንጭ ከተማን የመከላከል ድክመት በሁለተኛው አጋማሽም ተጠቅመውበታል፡፡ አርባምንጮች ወደ ጎል መድረስ ደካማ ጎናቸው ሆኖ የታየ የነበረ ቢሆንም በመቅደስ ከበደ እና መሠረት ወርቅነህ የግል ጥረት ሙከራን ማድረግ ችለዋል፡፡ በተለይ መቅደስ ከበደ መታ የግቡ አግዳሚ ብረት የመለሰበት ክስተት አርባምንጭን ለማንሰራራት ልትዳርግ ምትችል ዕድል ነበረች፡፡
65ኛው ደቂቃ ጥሩ ቅብብልን የፈጠሩት ሰናይት ቦጋለ እና ብርቱካን ገብረክርስቶስ ጥረታቸው ሰምሮ በመጨረሻም ብርቱካን ከሳጥን ውጪ ኳስ እና መረብ አገናኝታለች፡፡ 68ኛው ደቂቃ ሰናይት ቦጋለ ሁለተኛ ለራሷ ለቡድኑ ሰባተኛ ጎል ማስቆጠር ስትችል አረጋሽ ካልሳ ሐት-ትሪክ የሰራችበትን ጎል ከመረብ አዋህዳ ጨዋታው በንግድ ባንክ 8 ለ 0 አሸናፊነት ተጠናቋል፡፡
ከጨዋታው መጠናቀቅ በኃላ የንግድ ባንኳ አማካይ እና በጨዋታው ሐት-ትሪክ የሰራችው አረጋሽ ካልሳ የልሳን የሴቶች ስፖርት የጨዋታ ኮከብ ተብላለች፡፡
© ሶከር ኢትዮጵያ