” ዘንድሮ ማሳካት የምፈልገው ዕቅድ አለኝ ” – ሀብታሙ ታደሰ

ባሳለፍነው ዓመት ከተጠባባቂ ወንበር እየተነሳ ያለውን ጎል የማስቆጠር አቅም አሳይቷል። ዘንድሮም ሦስት ጎል በማስቆጠር ጥሩ የውድድር ጅማሮ እያደረገ ካለው ከሀብታሙ ታደሰ ጋር ቆይታ አድርገናል።

ከከፍተኛ ሊግ ስኬታማ ቆይታ በኋላ ኢትዮጵያ ቡናን ከተቀላቀለበት ጊዜ አንስቶ የተለየ ጎል የማግባት አቅም እንዳለው አሳይቶናል። ባሳለፍነው የውድድር ዓመት በተጫወተባቸው ዘጠኝ ጨዋታዎች ስድስት ጎሎችን አስቆጥሯል። በዘንድሮ የቤትኪንግ ፕሪምየር ሊግ በመጀመርያው ሳምንት ጨዋታ ተጠባባቂ የነበረው ሀብታሙ ከሁለተኛው ሳምንት ጀምሮ ወደ መጀመርያ አሰላለፍ በመግባት ጎሎችን በተከታታይ በማስቆጠር በቡድኑ ውጤታማ ጉዞ ውስጥ አስተዋፆኦ እያደረገ ይገኛል። በዚህ አያያዙ መቀጠል ከቻለ በከፍተኛ ጎል አስቆጣሪነት ፉክክር ውስጥ መዝለቅ እንደሚችል ከወዲሁ መገመት ይቻላል። ብዙም ማውራት የማይቀናውና ትኩረቱን ስራው ላይ እንዳደረገ የሚነገርለት ይህ አጥቂ ከዛሬው ጨዋታ መጠናቀቅ በኃላ ከሶከር ኢትዮጵያ ጋር አጭር ቆይታ አድርጓል።

” እንደ መጀመርያ ዓመት ዓምና የነበረኝ ጊዜ ጥሩ ነበር። በኮሮና ውድድሩ እስከ ተቋረጠ ጊዜ ድረስ ስድስት ጎሎችን ማስቆጠር ችያለው። አብረውኝ ከነበሩት ልጆች ጋር ጥሩ በመግባባት፤ የቡድኑን መንፈስ በመጠበቅ በፍጥነት ሊጉን ለመላመድ ችያለው። ዘንድሮ ደግሞ ልምምድ የጨዋታ ነፀብራቅ ነው። ልምምድ ላይ የምታሳየው ነገር፤ አሰልጣኙ የሚሰጥህን ተግባራዊ ማድረግ ከቻልክ እና የራስህን ኃላፊነት እየተወጣህ የጓደኞችህን እንቅስቃሴ እየጠበክ ከሄድክ ወደ መጀመርያ አሰላለፍ ውስጥ ትገባለህ። የተሰጠህን ዕድል ደግሞ በአግባቡ ከተጠቀምክ ቋሚ ለመሆን አይቸግርህም።

“እኔ ዘንድሮ ማሳካት የምፈልገው ዕቅድ አለኝ፤ ይሄውም ከፍተኛ ጎል አስቆጣሪ ሆኖ ማጠናቀቅን አስባለሁ። ለዚህም ተጨማሪ ልምምድ እየሰራሁ፤ ራሴንም እየጠበኩ አሰልጣኞቼ የሚሰጡኝን ማንኛውም ትዕዛዝ በመፈፀም ዓላማዬን አሳካለው ብዬ ተስፋ አደርጋለው። አሁን ደግሞ ዲኤስ ቲቪ መጥቶልናል። ራሳችንን የበለጠ የምናሳይበት ስለሆነ ከኢትዮጵያ ቡና ጋር ጥሩ ጊዜ አሳልፋለው ብዬ አስባለው።

” ሜዳ ውስጥ ያለኝ መረጋጋት የመጣው አንዳንዴ ራስህን ስታየው ምድነው የኔ ኃላፊነት ከእኔ ምንድነው የሚጠበቀው የሚለውን ራስህን እያዳመጥክ መሄድ ይገባል። አጥቂ እንደመሆኔ ጎል ማስቆጠር አለብኝ። አድርግ የተባልኩትን ነገር ማድረግ ስለሚገባኝ ይሆናል እርጋታው የመጣው። ብቻ አንዴ የተገኘውን የቋሚነት ዕድል ለመጠቀም እና ሌላ የምቆጭበት ዕድል እንዳይፈጠር ለማድረግ ጠንክሬ እየሰራሁ ነው።

“በነገራችን ላይ በመጨረሻ መናገር የምፈልገው በከፍተኛ ሊግም ሆነ በፕሪምየር ሊጉ ደረጃ እስካሁን የድሬዳዋ ቡድኖች ላይ አስራ ሦስት ጎሎችን አስቆጥሬለሁ።”


© ሶከር ኢትዮጵያ