የአራተኛው ሳምንት ሁለተኛ ቀን ጨዋታ በድሬዳዋ ከተማ እና ጅማ አባ ጅፋር መካከል ተደርጎ ድሬዳዋ 2-0 አሸንፏል።
ድሬዳዋ ከተማ በቡናው ጨዋታ በቀይ ካርድ የወጡት በረከት ሳሙኤል እና ዳንኤል ደምሴን በያሬድ ዘውድነህ እና አስጨናቂ ሉቃስ ሲተካ በሙኃዲን ሙሳ ቦታም ሱራፌል ጌታቸውን ተጠቅሟል። ጅማ አባ ጅፋር ደግሞ ከፋሲሉ ጨዋታ ውብሸት ዓለማየሁን በአዳላሚን ናስር ፣ ሀብታሙ ንጉሤን በሳምሶን ቆልቻ በመተካት ለጨዋታው ቀርቧል።
በእንቅስቃሴ ደረጃ እምብዛም አዝናኝ ያልነበረው የመጀመሪያው አጋማሽ ከስህተቶች የሚመነጩ በርካታ የጎል ዕድሎች ሲፈጠሩበት ትታይቷል። አብዛኛዎቹን ደቂቃዎች የተሻሉ ሆነው የተገኙት ድሬዎች የፊት መስመር አጥቂዎቻቸውን ፍጥነት ለመጠቀም የሚረዱ አጫጭር ቅብብሎችን አንዳንዴም ከኋላ በቀጥታ የሚላኩ ኳሶችን ለመጠቀም ሞክረዋል። 15ኛው ደቂቃ ላይ ኢታሙና ኬይሙኒ ከሱራፌል ጌታቸው ተቀብሎ ወደላይ የላከው ኳስም የቡድኑ እጅግ ለጎል የቀረበ ሙከራ ነበር። ቀስ በቀስ የፈጠሩትን ጫና እያጡ የመጡት ድሬዳዋ ከተማዎች በሳጥናቸው ዙሪያ እና ውስጥ ከሚሰሯቸው ስህተቶች ለጅማ አጥቂዎች በርካታ ዕድሎችን ፈጥረዋል።
ሆኖም በቅብብል መግባባት ችግር ይታይበት የነበረው የጅማ የፊት ክፍል በብዙአየሁ እንዳሻው ፣ ሳድቅ ሴቾ እና ሳምሶን ቆልቻው ከቅርብ ርቀት የተገኙ ኳሶችን በደካማ አጨራረስ አምክኗል። አደጋዎቹ ያለፏቸው ድሬዎችን 41ኛው ደቂቃ ላይ ከሱራፌል በተነሳ እና ጁኒያስ ናንጂቡ ባመቻቸው ኳስ አስቻለው ግርማ አስቆጥሮ መሪ አድርጓቸዋል። አስቻለው 44ኛው ደቂቃ ላይም ናንጂቡን ከግብ ጠባቂ ጋር የገናኘውን ኳስ በማመቻቸት ብድሩን ቢመልስም ናሚቢያዊው አጥቂ ጄኮ ፔንዜን ማሳለፍ ተስኖታል።
ሁለተኛውን አጋማሽ ጅማዎች የአቻነት ግብ ፍለጋ ወደፊት ገፍተው ለመጫወት ሲሞክሩ ድሬዎች ወደ ጥንቃቄው አመዝነዋል። ያም ቢሆን የጅማዎች በድሬዳዋ ሜዳ ላይ ኳስ ይዘው መቆየት ከ54ኛው ደቂቃ የብዙዓየሁ እንዳሻው ኢላማውን ያልጠበቀ ሙከራ ሌላ ዕድል ሲፈጥርላቸው አልታየም። የጅማዎችን ለመሀል ሜዳው መቅረብ ተከትሎም ድሬዎች በርካታ የመልሶ ማጥቃት ዕድሎችን ቢያገኙም ሳጥኑ ጋር ከመድረሳቸው በፊት አብዛኞቹ በቅብብል ስህተቶች ምክንያት መክነዋል።
75ኛው ደቂቃ ላይ ኤልያስ ሞም ከቅጣት ምት ያደረገው ሙከራ ብቻ ነበር የጄኮ ፔንዜን ጥረት የጠየቀው። ጨዋታው ወደ ማብቂያው በተቃረበ ቁጥር ጅማዎች ይበልጥ እየተከፈቱ መጥተው በመጨረሻም ድሬዎች የመልሶ ማጥቃታቸውን ፍሬ አግኝተዋል። 81ኛው ደቂቃ ላይ ጁኒያስ ናንጂቡ ከአስቻለው ግርማ የተቀበለውን ኳስ ይዞ በመግባት አክርሮ መትቶ ኳስ ከጃኮ ፔንዜ እጆች አምልጣ ግብ ሆናለች። ጨዋታውም ሌላ ግብ ሳይቆጠርበት በድሬዳዋ ከተማ 2-0 አሸናፊነት ተጠናቋል።
© ሶከር ኢትዮጵያ