በሳምንቱ የመጨረሻ ጨዋታ ሀዲያ ሆሳዕና አዳማ ከተማ 3-1 በሆነ ውጤት አሸንፏል።
ሀዲያ ሆሳዕና ዳዋ ሆቴሳን ከቅጣት መልስ በዱላ ሙላቱ ምትክ ሲጠቀም ግብጠባቂው ደርጄ ዓለሙ ቅጣት ላይ በሚገኘው መሀመድ ሙንታሪ እንዲሁም መድኃኔ ብርሀኔ በሄኖክ አርፌጮ ቦታ ተሰልፈዋል። በአዳማ ከተማ በኩል በተደረገው ብቸኛ ለውጥ በግብ ጠባቂው ዳንኤል ተሾመ ቦታ ኢብሳ አበበ ጨዋታውን ጀምሯል። በዚህም ቡድኑ በአምስት ጨዋታ ሦስተኛ ግብ ጠባቂውን ተጠቅሟል።
ጅምሩ አካባቢ ተደጋጋሚ ግጭቶች የነበሩበት የመጀመሪያ አጋማሽ በእንቅስቃሴ የተቀዛቀዘ ነበር። ሀዲያ ሆሳዕና በተሻለ የማጥቃት ሀሳብ ውስጥ ሆኖ ቢታይም በተጋጣሚ ሜዳ ላይ ከመታየት ባለፈ ጠንካራ የግብ ዕድል ሲፈጥር አልታየም። ቅድሚያ ለጥንቃቄ የሰጡት አዳማዎችም ቢሆኑ አልፎ አልፎ ወደ ሀዲያ ሳጥን ለመቅረብ ቢጥሩም ፊት ላይ ሲደርሱ በቁጥር አንሰው መገኘታቸው ምንም እንዳይፈጥሩ አድርጓቸዋል። ጨዋታው አልፎ አልፎ ከሳጥን ውጪ የሚደረጉ ሙከራዎች እየታዩበት ቆይቶም 36ኛው ደቂቃ ላይ ግብ ተቆጥሮበታል። የሱለይማን ሀሚድን የማዕዘን ምት ቢስማርክ አፒያ ሲገጨው አክሊሉ ተፈራ ቢመልሰውም በሳልፉ ፎፋና ተመትቶ እና በአይዛክ ኢሲንዴ ተጨርፎ ከመረብ ተገናኝቷል። አጋማሹ ሊጠናቀቅ ሲል የአዳማው በላይ አባይነህ ከቀኝ መስመር አሻምቶት ወደ ጎል ያመራው ኳስ አዳማ ለጎል የቀረበበት ቢሆንም በደረጄ ዓለሙ ድኗል።
ከሙከራ አንፃር መሻሻል ታይቶበት በጀመረው ሁለተኛ አጋማሽ 49ኛው ደቂቃ ላይ ሳሊፉ ፎፋና ከካሉሻ አልሀሰን በደረሰው ኳስ ከኢብሳ አበበ ጋር ተገናኝቶ ያዳነበት እንዲሁም ሙጃይድ መሀመድ ከሳጥን ጠርዝ መትቶት በአይዛክ ኢሲንዴ ተጨርፎ ደረጄ ያወጣው ኳስ የቡድኖቹ ጠንካራ ሙከራዎች ነበሩ። ከዚህ ውጪ ሌላ አደገኛ ኳስ ሳይታይበት የቆየው ጨዋታ በሦስት ደቂቃዎች ውስጥ ሁለት ግቦችን አስተናግዷል። 68ኛው ደቂቃ ላይ ሳጥን ውስጥ የተነካካን ኳስ አግኝቶ ትዕግስቱ አበራ አዳማን አቻ ሲያደርግ ጨዋታ ቀያሪው ዱላ ሙላቱ ተቀይሮ ከመግባቱ በሙጃይድ መሐመድ ተጠልፎ ሀዲያ ሆሳዕና ያገኘውን ፍፁም ቅጣት ምት ዳዋ ሆቴሳ 72ኛው ደቂቃ ላይ ግብ አድርጎታል። ከግቡ በኋላ ዳዋ ደስታውን ባለመግለፅ ለቀድሞው ክለቡ ያለውን ክብር አሳይቷል።
በድምሩ ከስድስት የቀድሞው ተጫዋቾቹ ጋር የተጋፈጠው አዳማ ከተማ የአቻ ጎል ፍለጋ ወደ ፊት ለመሄድ ቢሞክርም የፍሰሀ ቶማስ እና አብዲሳ ጀማል ተቀይሮ መግባትም ማጥቃቱን አስፈሪ አላረገለትም። ይልቁንም 89ኛው ደቂቃ ላይ ሳሊፉ ፎፋና ዳዋ ሆቴሳ ከዱላ ሙላቱ ተቀብሎ ባመቻቸለት ኳስ የሀዲያ ሆሳዕናን የግብ ቁጥር ወደ ሦስት ከፍ አድርጎታል። ጨዋታውም በነብሮቹ 3-1 አሸናፊነት ተጠናቋል።
© ሶከር ኢትዮጵያ