ሪፖርት | የአቡበከር ናስር ሐት-ትሪክ ቡናን ባለድል አድርጓል

ከአስር ዓመታት በኋላ ከሦስት በላይ ግቦችን ባስተናገደው ሸገር ደርቢ ቡና ጊዮርጊስን 3-2 አሸንፏል።

ሁለቱ ቡድኖች ሰበታን ከገጠሙባቸው ጨዋታዎች አንፃር ቅዱስ ጊዮርጊስ አዲስ ግደይን በጋዲሳ መብራቴ በመተካት ጨዋታውን ሲጀምር ኢትዮጵያ ቡና ግን የተጠቀመበትን የመጀመሪያ አሰላለፍ ሳይለውጥ ቀርቧል።

ተጠባቂነቱን በሚመጥን ግለት የጀመረው የሁለቱ ቡድኖች ጨዋታ ግቦችን ለማስተናገድ ብዙም አልቆየም። ከጅምሩም ሁለቱም ቡድኖች ወደ ተጋጣሚ ሳጥን እየቀረቡ ራቅ ያሉ ሙከራዎችን ማድረግ ጀምረዋል። ከተከላካይ ጀርባ የመግባት ምልክት ያሳዩ የነበሩት ቡናዎችም ቀዳሚውን ጎል ማግኘት ችለዋል። 15ኛው ደቂቃ ላይ ጨዋታው በጀመረበት ደቂቃዎች አካባቢ እንደሆነው ሁሉ አቡበከር ናስር ከተካላካዮች አምልጦ ሳጥን ውስጥ በገባበት ቅፅበት በፓትሪክ ማታሲ ጥፋት ተሰርቶበት ማታሲ በቀጥታ ቀይ ካርድ ከሜዳ ሲወጣ አቡበከር የተሰጠውን ፍፁም ቅጣት ምት ሮቢን ንጋላንዴን ለውጦ በገባው ለዓለም ብርሀኑ ላይ አስቆጥሯል።

ከግቡ በኋላ ቡናዎች ተረጋግተው ኳስ በመያዝ ከጊዮርጊሶች የፊት መስመር ጫና ለመውጣት ጥረት ላይ ሳሉ ግን ስህተት ሰርተዋል። በራሳቸው ሜዳ ኳስ በማንሸራሸር ላይ ሳሉ ሬድዋን ናስር ወደ ኋላ ለግብ ጠባቂው ተክለማርያም ሻንቆ የላካው ኳስ ከመረብ አርፏል። በዚህ የተነቃቁት ጊዮርጊሶች ተጨማሪ ጎል ለማግኘት ወደ ፊት ገፍተው መጫወት ሲጀምሩ እንደመጀመሪያው ሁሉ ቡናዎች ክፍተት አግኝተዋል። የታፈሰ ሰለሞን ተከላካይ ሰንጣቂ ኳስ ተከትለው በድጋሚ በጊዮርጊስ የግራ መከላከል ክፍል በኩል አቤል ከበደ እና አቡበከር ናስር ሰብረው ገብተው አቤል አመቻችቶለት አቡበከር 25ኛው ደቂቃ ላይ እንደገና ቡድኑን መሪ አድርጓል።

በጎዶሎ የተጫዋች ቁጥር ለመጫወት ከተገደዱበት ደቂቃ ጀምሮ ይበልጥ ቀጥተኛነት የታየባቸው ጊዮርጊሶች ከአምስት ደቂቃ በኋላ በሰጡት ምላሽ አቤል ያለው ከሄኖክ አዱኛ የተቀበለውን ኳስ ከቀኝ አቅጣጫ ይዞ በመግባት ሳጥኑ ጠርዝ ላይ ይገኝ ለነበረው ጋዲሳ መብራቴ አመቻችቶለት ጋዲሳ ጨዋታውን ወደ አቻነት የቀየረች ግብ አስቆጥሯል። ቀሪዎቹ የአጋማሹ ደቂቃዎች በንፅፅር ጨዋታው ቀዝቀዝ ብሎ ሲታይ ቡናዎች በጊዮርጊስ ሜዳ ላይ ብዙ ሰዓቱን ኳስ ይዘው ቆይተዋል። በለዓለም ከዳነው የኃይሌ ገብረትንሳይ የርቀት ሙከራ ውጪ ግን ሌላ የግብ ዕድል ሳያገኙ ጨዋታው ወደ ዕረፍት አምርቷል።

ሁለተኛውም አጋማሽ እንደመጀመሪያው ሁሉ በክስተት ጀምሯል። 47ኛው ደቂቃ ላይ የዊልያም ሰለሞንን ኳስ ተከትሎ አሁን ደግሞ በጊዮርጊስ የቀኝ ተከላካይ ክፍል መሀል የገባው አቡበከር ናስር በአስቻለው ታመነ ጥፋት ተሰርቶበት ሌላ ፍፁም ቅጣት ምት አግኝቶ ቢመታም ስቶታል። አቡበከር 54ኛው ደቂቃ ላይም ከአሥራት ቱንጆ የተላከለትን ኳስ ይዞ በተመሳሳይ ሩጫ የጊዮርጊስን ተከላካዮች አምልጦ ገብቶ ለማስቆጠር ቢቃረብም ሙከራውን ለዓለም አድኖበታል። በራሳቸው ሜዳ ላይ መቆየትን የመረጡት ጊዮርጊሶች ሳጥናቸው ዙሪያ ድረስ ለሚቀርቡትን የተጋጣሚያቸው ቅብብሎች ክፍተት ላለመስጠት በረጃጅም ኳሶች ወደፊት ለመሄድ ጥረት ሲያደርጉ ይታይተጠናቋል።

በተቀዛቀዘ መልኩ በቀጠለው ጨዋታ ቡናዎች በጊዮርጊስ የግብ አፋፍ በደረሱበት 74ኛው ደቂቃ ላይ ታፈሰ ከኃይሌ የተቀበለውን ኳስ ወደ ውስጥ ጥሎት ሲመለስ አቡበከር መትቶት ሄኖክ አዱኛ ከመስመር ላይ በደረቱ አውጥቶታል።

በቡናዎች ክፍተት ማፈላለግ እና በጊዮርጊስ ጥንቃቄ እስከመጨረሻው የዘለቀው ጨዋታ በመጨረሻ ደቂቃ በተሰራ ስህተት ጎል ተቆጥሮበታል። 90ኛው ደቂቃ ላይ ፍቅረየሱስ ከሳጥኑ መግቢያ ላይ የመታውን ኳስ ለዓለም ብርሀኑ በአግባቡ መቆጣጠር ሳይችል ቀርቶ አቡበከር ናስር ለራሱ እና ለቡድኑ ሦስተኛውን ግብ አስቆጥሮ ጨዋታው በቡና 3-2 አሸናፊነት ተጠናቋል።


© ሶከር ኢትዮጵያ