የአሰልጣኞች አስተያየት | ቅዱስ ጊዮርጊስ 2-3 ኢትዮጵያ ቡና

ከሸገር ደርቢ መጠናቀቅ በኋላ ሱፐር ስፖርት ከቡድኖቹ አሰልጣኞች ጋር ተከታዩን ቆይታ አድርጓል።

አሰልጣኝ ማሂር ዴቪድስ – ቅዱስ ጊዮርጊስ

ስለጨዋታው

“ተጫዋቾቹ ኃላፊነት ወስደው የተጫወቱበት መንገድ እጅግ ድንቅ ነው። በሰራነው ስህተት ግብ አስተናግደናል። እርግጥ ነው ተሸንፈናል፤ ነገርግን ወደ ፊት ማሰብ ይኖርብናል። ውድድሩ በዛሬው ዕለት አይጠናቀቅም። ከጨዋታው በፊት እንዳልኩት ከጨዋታው ሦስት እንጂ አራት ወይንም አምስት ነጥብ አይገኝም። ስለዚህ በዛሬው ዕለት የነበረውን ብቃት ለቀጣይ ጨዋታዎች መውሰድ ይኖርብናል።”

አሰልጣኝ ካሣዬ አራጌ – ኢትዮጵያ ቡና

ስለጨዋታው

“ውጤቱ ጥሩና የምንፈልገው ነበር። በመሠረቱ ሁሉንም ጨዋታ ለማሸነፍ ነው የምንገባው ጨዋታውም ጥሩ ነበር። እነሱ ገና በጊዜ ነበር አንድ ተጫዋች በቀይ የወጣባቸው ስለዚህ ያንን ትርፍ ሰው ለመጠቀም ነበር ያሰብነው። መጀመሪያ ላይ ትንሽ መዘናጋት ነበር ፤ ተጫዋች ቢወጣባቸውም እንዲጫወቱ ቦታና ጊዜ ፈቅደንላቸው ነበር። ከእረፍት መልስ ግን ያንን ክፍተት በመድፈን ያገኘውን የሰው ብልጫ በአግባቡ ተጠቅመን ለማሸነፍ ነበር የገባነው። በዚህም በመጨረሻ ተሳክቶልናል።”

ተጫዋቾቹ ሜዳ ላይ የሰጣቸውን ነገር ከመተግበር አንፃር ስለነበረው ስኬት

“ማዳበር የሚገቡን ነገሮች እንዳሉ ሆኖ ተሳክቶልናል ብዬ አስባለሁ። እነሱ ጎዶሎ ስለነበሩ አብዛኛውን ጊዜ በራሳቸው ሜዳ ተከማችተው ነበር። ስለዚህ ልንገባ የምንችልበት ሜዳ የትኛው ነበር የሚለው ነገር ትዕግሥት ይፈልግ ነበር።”


© ሶከር ኢትዮጵያ