እንደተለመደው የዓበይት ጉዳዮች ጥንቅራችንን የምናገባድደው በሳምንቱ የትኩረት ማዕከል የነበሩ ሌሎች ጉዳዮችን በማንሳት ነው።
👉በሞዛይክ የደመቀው የሸገር ደርቢ
ለወትሮው ስታዲየሙ ጠጠር መጣያ እስኪጠፋ በሁለቱ ቡድኖች ደጋፊዎች በሚጣበብበት በዚህ ጨዋታ ዘንድሮ ግን የተወሰነ ቁጥር ባላቸው የሁለቱ ቡድኖች ደጋፊዎች ታጅቦ ተካሂዷል።
ሆኖም ምስጋና ለሁለቱ ቡድኖች የደጋፊ አስተባባሪዎች ይግባና በጨዋታው ዕለት የደጋፊዎች አለመኖር ጨዋታውን በእጅጉ ቢያጎድለውም በሞዛይክና በልዩ ልዩ የጨርቅና የሸራ ህትመቶች የስቴዲየሙ መንፈስ ላይ ነፍስ ዘርተውበታል። በተለይ የቅዱስ ጊዮርጊስ ደጋፊዎች ሞዛይኮች እንዲሁም በኢትዮጵያ ቡናዎች በኩል የክለቡ ደጋፊዎችን የሚያሳዩ የህትመት ውጤቶች ስታዲየሙን የተለየ ገፅታ አላብሰውታል።
በሌሎች የዓለማችን ክፍሎች ደጋፊዎች መታደም አለመቻላቸውን ተከትሎ የስታዲየም መቀመጫዎች ላይ የተለያዩ ሞዛይክ እና የህትመት ውጤቶችን በማኖር የስታዲየሙን ድባብ ለማሻሻል የሚደረጉ ስራዎችን ተመልክተናል።
👉በጨዋታ ሳምንቱ ሁለት ጊዜ ያጫወተው ረዳት ዳኛ
በቤት ኪንግ የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ 6ኛ ሳምንት መርሐግብር ቅዱስ ጊዮርጊስ ከኢትዮጵያ ቡና እንዲሁም ባህር ዳር ከተማ ከድሬዳዋ ከተማ ባደረጓቸው ጨዋታዎች ባልተለመደ መልኩ በአንድ ቀን ልዩነት ረዳት ዳኛው ክንዴ ሙሴ በሁለቱም ጨዋታዎችን በመስመር ዳኝነት ጨዋታዎችን መርቷል።
በዚህ ረገድ ከዚህ ቀደም በላይ ታደሰ በመጀመርያው ሳምንት የተደረጉ ሁለት ጨዋታዎችን በዋና ዳኝነት መምራቱ የሚታወስ ነው።
👉ፕሪምየር ሊጉ የአዲስ አበባ ቆይታውን አጠናቋል
የዘንድሮው የቤት ኪንግ የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ በኮሮና ቫይረስ መነሻነት ከተለመደው የደርሶ መልስ አካሄድ በተለየ በወጥ የውድድር ቅርፅ ቡድኖች በተመረጠ የሀገሪቱ ክፍሎች ጨዋታዎችን የሚያደርጉበት ነው። ከአንደኛ እስከ ስድስተኛ ሳምንት ያለውን ውድድሩን የማስተናገድ ኃላፊነት አግኝቶ የነበረው የአዲስ አበባ ስታዲየምም ከቀጣዩ የጨዋታ ሳምንት አንስቶ በተረኛው አስተናጋጅ ከተማ ጅማ ለሚገኘው የጅማ ዩኒቨርስቲ ስታዲየም አስረክቧል።
ለ18 የጨዋታ ዕለታት በኋላ ትናንት በይፋ ሀዲያ ሆሳዕናን ከወልቂጤ አንድ አቻ በተለያዩበት ጨዋታ መቋጫውን ያገኘው ውድድሩ በቀጣይ በጅማ ፣ ባህር ዳር ፣ ድሬዳዋ እና ሀዋሳ ከተማዎች የሚካሄድ ይሆናል።
👉የወልቂጤው ባለውለታ የታወሰበት ጨዋታ
ወልቂጤ ከተማዎች ከሀዲያ ሆሳዕና ባደረጉት ጨዋታ የቀድሞው የወልቂጤ ከተማ አምበል የነበረው እና ከሁለት ዓመት በፊት በድንገተኛ የውሻ ንክሻ ምክንያት ከዚህ ዓለም በሞት የተለየው መዝገቡ ወልዴ የታወሰበት ሳምንት ነበር።
ለተጫዋቹ መታሰቢያነት በተጫዋችነት ዘመኑ ይለብሰው የነበረው ሁለት ቁጥር መለያ በማንም እንዳይለበስ የተደረገለት ተጫዋቹ በጨዋታው ዕለት በስታዲየሙ የካታንጋ ክፍል የመታሰቢያ ባነር ተቀምጦለት አስተውለናል።
ከመታሰቢያ ጋር በተያያዘ በዚህ ሳምንት ሕይወታቸው ያለፈው የቀድሞው ዕውቅ ዳኛ ዓለም ነፀበን ለማሰብ ከሸገር ደርቢ ጨዋታ መጀመር ቀድም ብሎ የአንድ ደቂቃ ህሊና ፀሎት ሲከናወንም ተመልክተናል።
© ሶከር ኢትዮጵያ