ከፍተኛ ሊግ | ሀምበሪቾ ኢኮሥኮን አሸንፎ ዓመቱን በድል ጀምሯል

በኢትዮጵያ ከፍተኛ ሊግ ምድብ ለ የመጀመሪያ ሳምንት አምስተኛ ጨዋታ ዛር ረፋድ 4:00 ላይ በሀዋሳ ቀጥሎ ብርቱ ፉክክር በታየበት የሀምበሪቾ እና ኢኮሥኮ ጨዋታ ሀምበሪቾ 1 ለ 0 አሸነፈ፡፡

የመጀመሪያው አጋማሽ በሁለቱም በኩል የመሐል ክፍላቸው ጨዋታውን ውበት አዘል መልክ እንዲይዝ ያደረገ ሲሆን ደቂቃዎች እየገፉ በመጡ ቁጥር ግን ሀምበሪቾዎች በቀኝ በኩል አድልተው ከአማካዩ ፀጋአብ ዮሴፍ እግር በሚነሱ ወደ ራምኬል ሎክ በሚጣሉ ረጃጅም ኳሶች ወደመጫወቱ ተሸጋግረዋል፡፡ 

ተመሳሳይ መልክ ያለውን የጨዋታ መንገድ እንደ ሀምበሪቾ ለመጫወት የዳዱት ኢኮሥኮዎች የኃላሸት ፍቃዱን ማዕከል በማድረግ ዋነኛ የማጥቂያ መስመራቸው ማድረግ ቢችሉም ተጫዋቹ ኳስን ሲያገኝ ነፃ አቋቋም ለነበሩ ተጫዋቾች ከማቀበል ይልቅ ምቹ ባልሆኑ አጋጣሚዎች ሲሞክር የነበራቸው ኳሶች ሲባክኑ ውለዋል፡፡ በዚሀም በመጀመሪያዎቹ አስራ አምስት ደቂቃዎች የኃላሸት ከተሻጋሪ ያገኘውን ዕድል ከግብ ጠባቂ ጋር ተገናኝቶ ሳይጠቀምባት በቀረው ወደ ጎል መቅረብ ጀምረዋል፡፡ በተቃራኒው ፈጣን ሽግግር ይታይባቸው የነበሩት እና መሀል ሜዳው ላይ በፀጋአብ ዮሴፍ እና ዋቁማ ዲንሳ ወደ ራምኬል ሎክ በቀኝ በኩል ጥቃት በተደጋጋሚ ሲሰነሩ የነበሩት ሀምበሪቾዎች ያለቀላቸውን አጋጣሚ አግኝተው ከሀዋሳ ከተማ የተገኘው ግብ ጠባቂው አላዛር መርኔ በሚገርም ብቃት አድኗቸዋል፡፡

ራምኬል በቀኝ በኩል የሰጠውን ዋቁማ አክርሮ መቶ አላዛር ያወጣበት እና 20ኛው ደቂቃ ዋቁማ ዲንሳ ከማዕዘን ሲያሻማ ዳግም በቀለ በግንባር ገጭቶ የአላዛር አስደናቂ ብቃት ከግብ ጠርዝ ላይ ከጎልነት አትርፏታል፡፡ ጨዋታው ቀጥሎ የቀድሞው የወላይታ ድቻ አጥቂ ዳግም በቀለ በተደጋጋሚ ተከላካዮችን ሲረብሽ ውሎ በስተመጨረሻም ጎል አስቆጥሯል፡፡ ራምኬል ሎክ በቀኝ መስመር ሰብሮ ገብቶ በቀጥታ ሲመታ ተጨራርፋ ስትመለስ የኢኮስኮ ተከላካዮች ስህተት ታክሎበት ዳግም በቀለ ሀምበሪቾን ቀዳሚ አድርጓል፡፡ በመጨረሻው የመልበሻ ክፍል ማምሪያ ደቂቃ ቃልፍቅር መስፍን ኢኮስኮን አቻ የምታደርግ አጋጣሚን አግኝቶ ሳይጠቀምባት ቀርቷል፡፡

ከእረፍት መልስም በጥሩ ፉክክር በቀጠለው እና ኳስ ላይ በተመሠረተው የአጋማሹ ጉዞ ኢኮሥኮዎች ወደ ጨዋታ ተመልሶ ግብ ለማስቆጠር የታተሩበት ሀምበሪቾዎችም ሌላ የግብ ዕድልን ለማግኘት ሙከራን አድርገዋል፡፡ ነገር ግን በእንቅስቃሴ የተገደዱ መሆኑ በክፍለ ጊዜው የጠሩ የግብ ዕድሎችን መመልከት ሳንችል እንዲሁም ከስልሳ ደቂቃዎች በኃላ ጨዋታው መቀዛቀዞች ታይተውበት በመጀመሪያው አጋማሽ በተቆጠረ ግብ ሀምበሪቾ 1 ለ 0 አሸናፊ ሆኗል፡፡


© ሶከር ኢትዮጵያ