ሴቶች ፕሪምየር ሊግ | አዳማ ከተማ የዓመቱን የመጀመርያ ድል አሳክቷል

በኢትዮጵያ ሴቶች ፕሪምየር ሊግ ሰባተኛ ሳምንት የሁለተኛ ቀን የመጀመሪያ ጨዋታ ረፋድ 4:00 በሀዋሳ ተደርጎ አዳማ ከተማ አቃቂ ቃሊቲ ክፍለ ከተማን 4 ለ 1 ረቷል፡፡

ብዙም የፉክክር መንፈስን ባላየንበት የመጀመሪያ አጋማሽ አቃቂዎች በተሻለ ወደ ግብ መጠጋት ቢችሉም የኋለኛውን መስመር ማስጠበቅ አለመቻላቸው ለአዳማ ከተማ የመልሶ ማጥቃት እጅጉን የተመቸ ሆኗል፡፡ በዚህም 18ኛው ደቂቃ ላይ ሰርካለም ጉታ የሰጠቻትን ኳስ የምስራች ላቀው በቀላሉ ወደ ጎልነት ለውጣው ቡድኗን መሪ ማድረግ ችላለች፡፡ ከተቆጠረባቸው በኃላ የታታሪነት ስሜት ይንፀባረቅባቸው የነበሩት አቃቂዎች አስደናቂዋ የመስመር አጥቂ ቤዛዊት ተስፋዬ ከምታደርገው ግላዊ ሙከራዎች ውጪ በቅብብሎሽ ለመሄድ የሚያደርጉት እንቅሴቃሴ እጅጉን መቆራረጦች የበረከቱበት በመሆኑ ያሰቡትን ማሳካት አላስቻላቸውም፡፡

23ኛው ደቂቃ ረጃጅም እና መልሶ ማጥቃት የተመቸው አዳማ ከተማ ከማዕዘን ምት የምስራች ስታሻማ ሰርካለም ጉታ በግንባር ገጭታ በማስቆጠር የቡድኑ የጎል መጠን ወደ ሁለት ከፍ አድርጋለች፡፡ አጋማሹ ሊጠናቀቅ ጥቂት ደቂቃ ሲቀረው አዳማ ከተማዎች የፍፁም ቅጣት ምት ቢያገኙም ምርቃት ፈለቀ ሳትጠቀምበት ቀርታ ወደ መልበሻ ክፍል በአዳማ 2 ለ 0 መሪነት አቅንተዋል፡፡

ሁለተኛው አጋማሽ ላይ በሚገባ ተሻሸለው የተመለሱት አቃቂዎች ቢሆኑም አሁንም የመከላከል አደረጃጀታቸው ደካማ በመሆኑ ለአዳማ ጥቃት ተጋላጭ ሆነው ታይተዌል። በዚህኛው የጨዋታ ክፍለ ጊዜ ከጨዋታው ይልቅ የዕለቱ ዳኞች ከረዳት ዳኛ ጋር ያለመግባባት እና ተደጋጋሚ የውሳኔ መዛባቶች ጨዋታውን በቶሎ ወደ ደብዛዛነት ሊለውጥ የቻለ ክስተት ነበር። በዳኞች ውሳኔ ቅሬታቸውን በየደቂቃው ሲገልፁ የነበሩት አቃቂ ቃሊቲዎች የዕለቱ ዋና ዳኛ ማዕረግ ጌታቸው በደል እየፈጸመችብን ነው በሚል የቴክኒክ ክስ በማስያዝ ጨዋታው ቀጥሏል።

በፈጣን የመልሶ ማጥቃት የሻሉ ሆነው የታዩት አዳማዎች 55ኛው ደቂቃ ላይ ሶስተኛ ጎላቸውን አግኝተዋል፡፡ ምርቃት ፈለቀ ከቀኝ በኩል የሰጠቻትን ኳስ ተጠቅማ ሰርካዲስ ጉታ ለራሷ ሁለተኛ ለቡድኗ ሦስተኛ ጎል ከመረብ አዋህዳለች፡፡ አሁንም ጥቃት መሰንዘር የቀጠሉት አዳማ ከተማዎች 63ኛው ደቂቃ ከአንድ ሳምንት በፊት ከመቐለ አዳማን በተቀላቀለችው ሄለን እሸቱ ግሩም የቅጣት ምት የጎል መጠናቸውን ከፍ ማድረግ ችለዋል፡፡

በቀሪዎቹ አስራ አምስት ደቂቃ አቃቂ ቃሊቲዎች በአዳማ ላይ ብልጫን ወስደው ተጫውተዋል፡፡ በተለይ የቀኝ መስመር ተጫዋቿ ቤዛዊት ንጉሤ ሁለት ያለቀላቸውን ዕድሎች አግኝታ የግቡ ቋሚ ብረት የመለሰባት አጋጣሚ እጅጉን አቃቂ በልጦ ለመጫወቱ ማሳያ ነበር፡፡ በተደጋጋሚ ወደ ጨዋታ ለመመለስ ያለ ኃይላቸውን ሲጠቀሙ የነበሩት አቃቂዎች 81ኛው ደቂቃ ላይ በቤዛዊት ንጉሴ የርቀት ጎል ወደ ጨዋታ ለመመለስ ቢሞክሩም ተጨማሪ ጎል ማስቆጠር ባለመቻላቸው ጨዋታው በአዳማ 4 ለ 1 አሸናፊነት ተደምድሟል፡፡

ከጨዋታው መጠናቀቅ በኃላ ልሳን የሴቶች ስፖርት የአዳማዋ ተጫዋች የምስራች ላቀውን የጨዋታው ምርጥ ብሎ ሸልሟታል፡፡


© ሶከር ኢትዮጵያ