በቤትኪንግ የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ ሰባተኛ ሳምንት የዕለቱ ሁለተኛ ጨዋታ ወላይታ ድቻ እና ሰበታ ከተማ ያደረጉት ጨዋታ ያለጎል ተጠናቋል።
ወላይታ ድቻ በሀዋሳ ከተሸነፈበት ጨዋታ የሦስት ተጫዋቾች ለውጥ በማድረግ ግብ ጠባቂው መክብብ ደገፉ፣ እንድሪስ ሰዒድ እና ደጉ ደበበን በሰዒድ ሀብታሙ፣ አማኑኤል ተሾመ እና ቸርነት ጉግሳ ምትክ ወደ መጀመሪያ አሰላለፍ በማካተት ጨዋታውን ሲጀምር ሰበታዎች ከጅማ አባ ጅፋር ጋር ነጥብ ከተጋሩበት ጨዋታ ሦስት ለውጥ አድርገው ግብ ጠባቂው ፋሲል ገብረሚካኤል፣ ዳንኤል ኃይሉ እና አብዱልባሲጥ ከማልን በምንተስኖት አሎ፣ አብዱልሀፊዝ ቶፊቅ እና ዳዊት እስጢፋኖስ ምትክ አስገብተዋል።
እጅግ የወረደ የጨዋታ እንቅስቃሴ በታየበት የዕለቱ ጨዋታ ሰበታ ሙሉ የጨዋታ ክፍለ ጊዜውን የኳስ ቁጥጥር የበላይት ይዞ ቢጫወትም በተጋጣሚ የጎል ክልል የተገኙባቸው አጋጣሚዎች በጣም ጥቂት ነበሩ። በዚህም አንድም የጎል ዕድል መፍጠር ሳይችሉ ወጥተዋል።
በግብ ጠባቂው አሰልጣኝ ዘላለም ማቴዎስ መሪነት ወደ ሜዳ የገባው ወላይታ ድቻ በአንፃሩ ከቆሙ ኳሶች እና ከቅብብል ስህተቶች በሚገኙ አጋጣሚዎች በተለይ በመጀመርያው አጋማሽ የተሻለ የጎል ዕድል መፍጠር ችለዋል። በ27ኛው ደቂቃ አንተነህ ጉግሳ ከማዕዘን የተሻማውን ኳስ በግንባሩ ገጭቶ የጎሉ ብረት የገጨበት ሙከራ የጨዋታው ዋንኛ ሙከራ ሲሆን በ42ኛው ደቂቃ ያሬድ ደርዛ በቅብብል ስህተት ጥሩ ኳስ አግኝቶ በጎብ ጠባቂው አናት አሳልፎ ለማስቆጠር ያደረገው ያልተሳካ ሙከራ እና በተመሳሳይ የቅብብል ስህተት ያሬድ በድጋሚ ወርቃማ ዕድል አግኝቶ ወደ ግብ ሲሞክር ፋሲል ገብረሚካኤል ያዳነበት ድቻዎች የፈጠሯቸው ዕድሎች ነበሩ።
ሁለተኛው አጋማሽ ከመጀመርያው በባሰ መልኩ የተቀዛቀዘ እንቅስቃሴ የታየበት ይልቁኑም በተደጋጋሚ ጥፋቶች ምክንያት ተጫዋቾች ለጉዳት የተጋለጡበት ነበር። በዚህም ያሬድ ዳዊት፣ ቢያድግልኝ ኤልያስ እና ታደለ መንገሻ (በቀጥታ ወደ ሆስፒታል ተወስዷል) ባጋጠማቸው ጉዳት ተቀይረው ሲወጡ አብዱልባሲጥ ከማል ሰበታዎች ቅያሪ በመጨረሳቸው ከነጉዳቱ ሲጫወት ተስተውሏል።
ሰበታዎች ዳንኤል ኃይሉ ከቅጣት ምት በቀጥታ መትቶ በቀላሉ በግብ ጠባቂ ከተያዘ ሙከራ ውጪ በዚህም አጋማሽ የጠራ የጎል ዕድል ያልፈጠሩ ሲሆን ወላይታ ድቻዎችም ከርቀት ከሞከሯቸው እና ኢላማቸውን ካልጠበቁ ዕድሎች ውጪ የሚጠቀስ ክስተት ሳይፈጠር ጨዋታው ያለ ጎል በአቻ ውጤት ተጠናቋል።
© ሶከር ኢትዮጵያ