ታታሪዋ ማዕድን ሳህሉ

“በኮቪድ ምክንያት ሰባት ወሩን እንደ ሌሎች ተጫዋቾች ቁጭ አላልኩም፤ሰርቻለሁ። የእሱ ውጤት ነው ብዬ አምናለሁ”

የኢትዮጵያ ሴቶች ፕሪምየር ሊግ አንደኛ ዲቪዚዮን የ2013 የውድድር ዓመት በሀዋሳ ከተማ ከጀመረ አንድ ወር ሞልቶታል፡፡ በውድድሩ ላይ በርካታ አዳዲስ እና አስገራሚ ተጫዋቾችን በሜዳ ላይ በሚያደርጉት እንቅስቃሴ እየተመለከትን እንገኛለን። ጎልተው ከወጡ እና በርካቶችን ካስገረሙ ተጫዋቾች መካከል የድሬዳዋ የመሐል ተጫዋች ማዕድን ሳህሉ ከሁሉም ላቅ ያለውን ቦታ ትይዛለች፡፡ ዳንግላ ከተማ ተወልዳ ያደገችው ተጫዋቿ በትውልድ ከተማዋ ከፕሮጀክት እስከ አማራ ክልል ውድድር ድረስ ተመርጣ በመጫወት ብቃቷን በሚገባ አሳይታለች። በልጅነቷ በራሷ ጥረት እግር ኳስን መጫወት የቀጠለችሁ እንስቷ ከነበራት ዕድገት የተነሳ በቶሎ ኢትዮጵያ ቡና ውስጥ የክለብ ህይወቷን የጀመረች ሲሆን በኃላም በጥረት ኮርፖሬት ገብታ ተፅኖ ፈጣሪነቷን አስመስክራለች፡፡ ከተሰረዘው የ2012 የውድድር ዓመት ጀምሮ ድሬዳዋ ከተማን ከተቀላቀለች በኃላ በሒደት አቋሟን ማሳደግ የቻለችው ማዕድን በኢትዮጵያ ከ17 ዓመት በታች የሴቶች ቡድንም ውስጥ ተጠርታ መጫወት ችላለች፡፡

ዘንድሮ ድሬዳዋ ከተማ በፕሪምየር ሊጉ አጀማመሩ ደካማ የነበረ ቢሆንም ተጫዋቿ ከጨዋታ ወደ ጨዋታ የነበራት እንቅስቃሴ እና የቡድኑን ሚዛን በመጠበቅ ረገድ የምታሳየው ብቃት ተደምሮ ወደ ድል ክለቡ እንዲመለስ ያደገችው አስተዋጽኦ ቀላል የሚባል አይደለም። እንደ መጠርያ ስሟ በማንፀባረቅ ከብዙሀኑ አድናቆት የተቸራት ማዕድን ትናንት ድሬዳዋ ከተማ አርባምንጭ ከተማን 2 ለ 1 ከረታበት ጨዋታ መጠናቀቅ በኃላ ስለ ምታሳየው የሜዳ ላይ እንቅስቃሴ እና በግሏም ሆነ ከቡድኗ ጋር በዚህ ዓመት ስላቀደችሁ ዕቅድ ከሶከር ኢትዮጵያ ጋር ቆይታን አድርጋለች፡፡

“ዘንድሮ ቡድናችን ከዓምናው የተሻለ እየተንቀሳቀስን ነው፡፡ ጥሩ አቋም ላይ ነን ብዬም አስባለሁ፡፡ ውጤት ማምጣታችን ምንም የተጨመረ ነገር የለውም። በፊትም አቅም አንሶን አይደለም። ብዙ የወዳጅነት ጨዋታን አላደረግንም፤ እንደ ቡድንም አልተቀናጀንም ነበር፡፡አሁን ግን ወደ ቡድኑ ቅንጅት ስለተመለስን ነው ውጤታማ መሆን የቻልነው። በእርግጥም እኔ ለማሳየው እንቅስቃሴ ኮቪድ ረድቶኛል። ሰባት ወሩን ያው እንደ ሌሎች ተጫዋቾች ቁጭ አላልኩም፤ ሰርቻለሁ። የእሱ ውጤት ነው ብዬ አምናለሁ።

“እኔ የምመኘው በዚህ ዓመት ቡድኔ ከአንድ እስከ ሦስት ደረጃን እንዲይዝ ነው። ፈጣሪ ካለ ደግሞ እንደ ዕድልም ዋንጫ ልናነሳ እንችላለን፡፡ በግሌ ደግሞ በብሔራዊ ቡድን ተጠርቶ ጥሩ ነገርን ማሳየት ነው፡፡”


© ሶከር ኢትዮጵያ