ከሮድዋ ደርቢ መጠናቀቅ በኋላ ሁለቱ አሰልጣኞች ለሱፐር ስፖርት ተከታዮቹን አስተያየቶች ሰጥተዋል።
አሰልጣኝ ዘርዓይ ሙሉ – ሲዳማ ቡና
ስለጨዋታው
ጨዋታው ሁለት ዓይነት መልክ ነበረው። መጀመርያ ልንጫወት ያሰብነውን እነሱ ተጫወቱ። ከዕረፍት በፊት ብልጫ ወስደው ተጫውተዋል። በዛም ጎል አስቆጠሩ። ከዛ በኋላ ኳሱን ለመቆጣጠር ተጫዋቾች ቀይረን ሞክረን። ከዕረፍት በኋላም በልጠን ተጫውተን ነበር። እውነት ለመናገር ዳኞች በሚሰሩት ስህተት ዋጋ ከፍለናል። ሞክንያቱም እዚህ ጥፋት ሲሰራ እና በእጅ ሲነካ በዝምታ እየታለፈ ነበር። ቢያንስ አቻ የመሆን ዕድል ነበረን። ይህ ጉዳይ በትኩረት ሊታይ ይገባል።
ስለ ያስር ሙገርዋ ቅያሪ
እነሱ ወደ መስመር እየወጡ ሲጫወቱ ብርሀኑ እየተከተለ ሲያስጥል ነበር። ሆኖም የሱን ቦታ ያስር ሲሸፍን አልነበረም። ያንንም ክፍተት ይጠቀሙት ነበር። ለዛ ነው የቀየርኩት። ከዛ በኋላም እንዳያችሁት ኳሱን መቆጣጠር እና ብልጫ መውሰድ ችለናል። ሆኖም እነሱ ቀድመው ስላገቡ አስጠብቀው ወጡ እንጂ ከእረፍት በኋላ የተሻልን ነበርን።
አሰልጣኝ ሙሉጌታ ምህረት – ሀዋሳ ከተማ
ቡድኑ በቶሎ ግብ ማስቆጠሩ ተጠቃሚ እንዲሆን ስለማድረጉ
በሚገባ። ያው ማንኛውም ቡድን ጎል ሲያገባ በጨዋታው የተሻለ ተጠቃሚ ይሆናል። እኛም ያን ጎል በማግባታችን ተጠቃሚ ሆነን አስጠብቀንም ከዕረፍት በኋላ ደግሞ ደግመን አሸንፈን መውጣት ችለናል።
ሁለተኛው አጋማሽ ላይ ስለመቀዛቀዛቸው
ያው ጨዋታዎች ያስገድዳሉ። ሊጉ ውጥረት የበዛበት ነው። አሁን ያለንበት ቦታም ምቾት የሚሰጥ አይደለም ፤ ሦስት ነጥቡ ያስፈልገን ነበር። የምንፈልገውን ነገር ከዕረፍት በፊት ጨርሰን መውጣት ነበር ዓላማችን። ከእረፍት በፊት የተሻሉ ዕድሎችን አግኝተን ነበር። ያኔ ተጠቅመናቸው ቢሆን ኖሮ በሁለተኛው አጋማሽ እንደታየው ዓይነት አካሄድ አንጠቀምም ነበር። ግን ዞሮ ዞሮ የምንፈልገውን ነገር ከግብ አድርሰናል ብዬ ነው የማስበው።
ሁለተኛው ጎል ላይ የነበረው ደስታ አገላለፅ
እኔ ምንም የተለየ ነገር የለኝም። ትልቁ ዓላማዬ ቡድኔ እንዲያሸንፍ ስለነበር ሁለተኛው ጎል ሲገባ ማረጋገጫም ስለሆነ በጣም ነው ደስ ያለኝ።
© ሶከር ኢትዮጵያ