ፈረሰኞቹ ትናንት በነበረው ጨዋታ የወላይታ ድቻ የመከላከል አቅም ሰብረው ጎል ለማስቆጠር በተቸገሩበት ሰዓት ተቀይሮ በመግባት ወሳኟን ጎል ካስቆጠርው ሳላዲን ሰዒድ ጋር ቆይታ አድርገናል።
ለሁሉም ተጫዋች የፅናት ተምሳሌት መሆኑን በተግባር እያሳየ እዚህ ደርሷል። በ2012 የውድድር ዘመን በኮሮና ምክንያት ውድድሩ እስከ ተቋረጠበት ጊዜ ድረስ ከጉዳት ጋር እየታገለ ፈረሰኞቹን እያገለገለ የቆየውና በቤተሰብ ሁኔታ ምክንያት ለወራት ከሀገር ውጭ የነበረው ሳላዲን በቅርቡ ወደ ሀገሩ ተመልሶ ለቅድመ ዝግጅት ቢሾፍቱ የገባው ውድድሩ ሊጀምር ቀናት ሲቀረው ነው። ከወራት በኃላ የመጀመርያውን ጨዋታውን ከጅማ አባጅ ፋር ጋር ተቀይሮ በመግባት የዚህ ዓመት የመጀመርያ ጨዋታ በማድረግ ልምዱን በመጠቀም በተገኘው ውጤት የራሱን አስተዋፆኦ አድርጎ መውጣቱ ይታወሳል። በትናትናው ዕለት በተደራጀ ሁኔታ መከላከል ላይ በተጠመዱት ድቻዎች ጎል ለማስቆጠር የተቸገሩት ፈረሰኞቹ ሳላዲን ሰዒድን አገልግሎት አግኝተው ወሳኝ ሦስት ነጥብ ማግኘት ችለዋል። ከጨዋታ በኃላ ሳላዲን ስላሳለፈው ጊዜ ከረጅም ወራት በኃላ ተመልሶ ጎል ስለ ማስቆጠሩ እና በቀጣይ ስለሚያስባቸው ነገሮች ከሶከር ኢትዮጵያ ጋር አጭር ቆይታ አድርጓል።
“ያለፉት ጊዜያት አስቸጋሪዎች ነበሩ። ዓምና በኮሮና ውድድሩ ሲቋረጥ ቀይ ካርድ አይቼ ነው የወጣሁት። ከዛ ጊዜ በኃላ ቅጣትም ስለነበረብኝ ቶሎ ወደ ጨዋታ አልተመለስኩም። ትንሽ የቤተሰብ ችግር አጋጣሞኝ ዝግጅት የገባሁት ውድድሩ ሊጀምር ጥቂት ቀናት ሲቀረው ነው። ትንሽ አስቸጋሪ ጊዜ አሳልፌ ነው የመጣሁት ያው ከረጅም ጊዜ በኃላ ወደምወደው ሙያ ተመልሼ መጫወቴ ደስ ብሎኛል።
” ቅዱስ ጊዮርጊስ ቤት እንደሚታወቀው ጎል እና ሦስት ነጥብ አስፈላጊ ነው። ሁሉም ቡድን ከእኛ ጋር ሲጫወት ጠንክሮ እንደሚመጣም እናውቃለን። በትናትናው ዕለት በመጨረሻው ደቂቃ በወሳኝ ሦስት ነጥብ የምናገኝበትን ጎል ወደ ምወደው ሙያ ተመልሼ በማስቆጠሬ ደስ ብሎኛል።
” ሙያዬን በጣም ነው የምወደው በመመለሴ ደስ ብሎኛል። ሁሉም ተጫዋቾች ለቅዱስ ጊዮርጊስ ሦስት ነጥብ እና ጎል ምን ያህል እንደሚያስፈልግ በሚገባ ያውቃሉ። ስለዚህ በቀጣይ ጨዋታዎች ሁላችንም የምንፈልገውን ውጤት ለማምጣት እናስባለን።
© ሶከር ኢትዮጵያ