የስምንተኛው ሳምንት የመጨረሻ ቀን ውሎ የሚጀምርበትን ጨዋታ በዳሰሳችን እንዲህ ተመልክተነዋል።
የስድስተኛው እና የሰባተኛው ሳምንት ጨዋታዎች የሚፈልጉትን ውጤት ይዘውላቸው ያልመጡት ድሬዳዋ እና ሀዲያ ሆሳዕና ዳግም ከሦስት ነጥብ ጋር ለመገናኘት ይፋለማሉ።
ደካማ አቋም ላይ ይገኙ የነበሩት ጅማ አባ ጅፋር እና ወላይታ ድቻን መርታት የቻለው ድሬዳዋ በባህር ዳር እና ሲዳማ ተከታታይ ሽንፈት አግኝቶታል። ከምንም በላይ በሲዳማው ጨዋታ የታየው የቡድኑ እጅግ የተዛባ የመከላከል አደረጃጀት ለነገው ጨዋታ ትልቁ ስጋቱ ነው። በዚህ ደካማ ጎኑ ላይ ደግሞ የቦታው ተሰላፊዎቹ ጉዳት ያለባቸው መሆኑ ሁኔታውን ይበልጥ አስከፊ ሊያደርግበት ይችላል። ቡድኑ በአንድ ለአንድ ግንኙነቶችም ሆነ በረጅሙ የሚጣሉ ኳሶችን በማቋረጥ ረገድ በሲዳማው ጨዋታ ያሳየው ድክመት ነገ የሚደገም ከሆነ ከሀዲያ አጥቂዎች ጠንካራ ጎን አንፃር ግቦችን ሊያስተናግድ ይችላል። በዚህ ውስጥ ግን ተደጋጋሚ ሙከራዎችን ሲያድን የሚታየው የፍሬው ጌታሁን ብቃት ነገም ድሬን ሊታደገው እንደሚችል መርሳት ስህተት ይሆናል።
በማጥቃቱም ረገድ እየተቀዛቀዘ የመጣው ድሬዳዋ እንደኤልያስ ማሞ እና አስቻለው ግርማ ዓይነት አጋጣሚ በመፍጠርም ሆነ ግብ በማስቆጠር የተካኑ ተጫዋቾች ወደ ብቃታቸው ጫፍ እንዲመጡ አበክሮ ይጠብቃል። በግል ጥረቱ ግብ ሲያስቆጥር ካየነው ሙኸዲን ሙሳ በተጨማሪ ጁኒያስ ናንጄቤ እና ሌላኛውን ናሚቢያዊ አጥቂ ኢታሙና ኬይሙኒንን ውጤታማ ሊያደርግ የሚችል የማጥቃት ዕቅድ ይዞ መግባት ለብርቱካናማዎቹ ስብስብ ከነገው ጨዋታ ነጥብ ለማግኘት በዋነኝነት የሚያስፈልጉት ነገሮች ናቸው።
ሀዲያ ሆሳዕና የአራት ተከታታይ ድሎቹ መልካም አጀማመር ባለፉት ሁለት ጨዋታዎች አራት ነጥብ ብቻ በማሳካቱ የተበረዘ ይመስላል። አስፈሪ አጀማመሩን ለመመለስም ከነገው ጨዋታ ሙሉ ነጥቦች ማሳካት የግድ ይለዋል። ባልተጠበቀ ሁኔታ ወሳኝ ተጫዋቾቻቸውን በምግብ መመረዝ ሳቢያ አጥተው ፋሲልን የገጠሙት ሆሳዕናዎች ጥንቃቄ ተኮር አቀራረብ ነበራቸው። በነገው ጨዋታ ግን ይህ ሁኔታ ይደገማል ተብሎ አይታሰብም። የአሰልጣኝ አሸናፊ በቀለ ቡድን የሳሊፉ ፎፋና ፣ ዳዋ ሆቴዋ እና ቢስማርክ አፒያን ጥምረት ዳግም ካገኘ ፊት መስመር ላይ ያለው ስልነት መመለሱ አይቀርም። በመሆኑም በድፍረት የሚያጠቃ እና ከመሀል ክፍሉ ድንገተኛ ኳሶችን ወደ ፊት የሚጥል ቡድን ከነብሮቹ ይጠበቃል።
በመከላከሉም ረገድ ምንም እንኳን ሦስት ተከላካዮችን የተጠቀመ ቢሆንም በአደገኛ ሁኔታ ይከፈት የነበረባቸው ቅፅበቶች የቡድኑ የማጥቃት ሂደት ከተስተካከለ ጫና ስለሚቀልንስለት እርጋታውን መልሶ ሊያገኝ ይችላል። ያ ካልሆነ ግን እንደ ሙኸዲን ሙሳ ዓይነት ላሉ ተከላካይ ሰንጣቂ ኳሶችን የመጠቀም አቅም ላላቸው ተጫዋቾች አጋልጦ ሊሰጠው እና በፋሲል ከነማ የተቆጠረበት ግብ ዓይነት ክፍተቶችን ሊፈጥር ይችላል። ያም ቢሆን ቡድኑ በጨዋታው የሦስትዮሽ አጥቂ ጥምረቱን አስቀድሞ በአራት ተከላካዮች ለሚጀምር አደራደር ቅድሚያ እንደሚሰጥ ይጠበቃል።
ድሬዳዋ ከተማ ባሳለፍነው ጨዋታ የጡንቻ መሳሳብ ጉዳት ያስተናገደው በረከት ሳሙኤልን ጨምሮ ሄኖክ ኢሳያስ በቁርጭምጭሚት ጉዳት ሰያጣ ሱራፌል ጌታቸው ፣ ያሬድ ዘውድነህ እና ቢኒያም ጥዑመልሳንን ግልጋሎትም እንደማያገኝ ሰምተናል። በአንፃሩ በጉዳት ብሩክ ቃልቦሬን ብቻ የሚያጣው ሀዲያ ሆሳዕና የመጀመሪያ ተመራጭ ግብ ጠባቂው መሀመድ ሙንታሪ በቅጣት የማይሰለፍበት የመጨረሻ ጨዋታው ይሆናል። ከዚህ ውጪ በምግብ መመረዝ ሳቢያ በፋሲሉ ጨዋታ ያልነበሩ ተጫዋቾች ልምምድ በመጀመሪያቸው ወደ ሜዳ እንደሚገቡ ይጠበቃል። አዲሱ የቡድኑ ፈራሚ ዮናስ ገረመውን መጠቀም የሚችለው በሁለተኛው ዙር መሆኑን ሰምተናል፡፡
የእርስ በእርስ ግንኙነት
– በ2008 የውድድር ዓመት አብረው ሊጉን ተቀላቅለው የነበሩት ሁለቱ ቡድኖቹ ሁለት ጊዜ የተገናኙ ሲሆን ሁለቱንም ድሬዳዋ ከተማ በበላይነት አጠናቋል። ብርቱካናማዎቹ በሜዳቸው 3-2 ሲያሸንፍ ሆሳዕና ላይ ደግሞ 2-0 መርታት ችለው ነበር።
ግምታዊ አሰላለፍ
ድሬዳዋ ከተማ (4-1-3-2)
ፍሬው ጌታሁን
ምንያምር ጴጥሮስ – ፍቃዱ ደነቀ – ፍሬዘር ካሳ – ዘነበ ከበደ
ዳንኤል ደምሴ
ኢታሙና ኬይሙኒ – ኤልያስ ማሞ – አስቻለው ግርማ
ሙኽዲን ሙሳ – ጁኒያስ ናንጄቦ
ሀዲያ ሆሳዕና (4-3-3)
ደረጄ ዓለሙ
ሱሌይማን ሀሚድ – ኢሴንዴ አይዛክ – ተስፋዬ በቀለ – ሄኖክ አርፌጮ
ካሉሻ አልሀሰን – ተስፋዬ አለባቸው – አማኑኤል ጎበና
ቢስማርክ አፒያ – ሳሊፉ ፎፋና – ዳዋ ሆቴሳ
© ሶከር ኢትዮጵያ