ወንድማማቾቹ በወንድማማቾች ደርቢ – ኤፍሬም አሻሞ እና ብርሐኑ አሻሞ ስለ አስገራሚ የፉክክር ስሜታቸው ይናገራሉ

የቤትኪንግ ፕሪምየር ሊግ የተለያዩ በጎ ገፅታዎችን ከነግድፈቱም ቢሆን እያስመለከተን ስምንተኛው ሳምንት ላይ መድረስ ችሏል። እዚህ ቀደም ሦስት ወንድማማቾችን በኢትዮጵያ ቡና እና በሰበታ ከተማ ጨዋታ ወቅት እንዲሁም በወላይታ ድቻ እና በፋሲል ከነማ ጨዋታ ጊዜ አስመልክቶን የወንድማማቾቹን ስሜት ማጋራታችን ይታወቃል። በዛሬው ዕለት በሮድዋ (ወንድማማቾች) ደርቢ ሀዋሳ ከተማን ከሲዳማ ቡና ባገናኘው ጨዋታ ሁለቱን የአሻሞ ወንድማማቾች አገናኝቶ ማለፉ ይታወሳል። 

የታላላቆቻቸው ጌታሁን አሻሞ እና ሰለሞን አሻሞ ዱካ ተከትለው ተጫዋች የሆኑት ኤፍሬም (ሀዋሳ) እና ብርሀኑ (ሲዳማ ቡና) ዛሬ በተቃራኒው ተጫውተው የኤፍሬም ቡድን ሀዋሳ 2-0 ማሸነፉ የሚታወስ ሲሆን ከጨዋታው በፊት የነበረውን የፉክክር ስሜት እና ከጨዋታው መጠናቀቅ በኃላ የነበረውን ሁኔታ አስመልክቶ ከሶከር ኢትዮጵያ ጋር አስገራሚ ቆይታ አድርገዋል።

ኤፍሬም አሻሞ

ከወንድም ጋር በተለያየ ማልያ መጫወት ስሜቱ እንዴት ነው ?

ስሜቱ ትንሽ ከበድ ይላል። በሁለታችንም በኩል ያለመሸነፍ ፉክክር አለ። አንደኛው ከደርቢ አንፃር መሆኑ ትንሽ ከበድ ይላል።

ከጨዋታው በፊት ብሽሽቅ ነበር ስለመሸናነፍ ?

ብዙ ጊዜ ነበር። ከዚህ ከቀደም በተለያየ ጊዜ ተገናኝተናል። እኔ ደደቢት፣ መቐለ አሁን ደግሞ ሀዋሰ ሆኜ እርሱ ወልዋሎ ሁለት ጊዜ፣ ሲዳማ ሆኖ ተገናኝተናል። ከጨዋታ በፊት ብንፎካከርም ብዙ ጊዜ የበላይነት የምወስደው እኔ ነኝ። ይሄን ደግሞ እርሱ ያውቀዋል። ከጨዋታው በፊት እናሸንፋለን ብዬው ነበር። ያው ውጤቱም የሚታይ ሆኗል።

በአንድ አጋጣሚ በሁለታቹሁም መካከል ፍትጊያ ነበር። ይህን እንዴት ይገለፃል ?

ያው ኳስ ነው። ኳስ ላይ ደግሞ ይሄ ወንድምህ ነው የሚባል ነገር የለም። ይሄም ስሜት እርሱም ጋር ይኖራል። እኔም ጥፋት ብሰራበት እርሱም ቢሰራብኝ ያው ሥራ ነው። በመልካም ነው የምናስበው፤ የምራራው ነገር አይኖርም። ዘጠና ደቂቃ ካለቀ በኃላ ሁሉን ነገር እዛው ጨርሰን ነው የምንወጣው።

ከዚህ በኃላ በአንድ ማልያ እንጠብቅ ?

ከዚህ ቀደም ወልዋሎ በአንድ ማልያ የመጫወት ዕድል አግኝተናል። የጊዜ ጉዳይ ሆነና እኔ ወደ መቐለ እርሱ ወደ ሲዳማ አምርቷል። የሚቀጥለውን አብረን የምናየው የሚሆነው። ፈጣሪ ከፈቀደ አንድ ቀን በአንድ ክለብ አብረን የምንጫወት ይሆናል።

ከወንድምህ የምታደንቅለት ምንድነው?

በጣም ታራሪ ነው። ለሥራው ትልቅ ቦታ ይሰጣል። የመጫወት ፍላጎት እና አቅም ያለው ወጣት ነው፤ ብዙ ነገር አለው። ከክለብ አልፎ ለሀገር፤ ከሀገር አልፎ ከኢትዮጵያ ውጭ ወጥቶ መጫወት የሚያስችል አቅም ያለውና ይህንንም የሚያስብ ነው። አሰልጣኝ ዘርዓይም ብዙ ነገሩን አይቶ እየተረዳው ነው። ሲጫወት እንዳየነው አግሬሲቭ ነው። ረጅምም አጭር ኳስም ሲጫወት ጎበዝ ነው። በአጠቃላይ ብዙ ነገር አለው። ኢትዮጵያ ውስጥ አሉ ከሚባሉ የተከላካይ አማካዮች አንዱ እርሱ ነው። በጣም ታጋይ እና ታታሪ ሠራተኛ ነው።

ከጨዋታ በኃላ ከቤተሰብ ያወራችሁት አለ?

አዎ በተለይ እናቴ ደውላለች። ብዙ ጊዜ የምታደላው ወደ እርሱ ነው። ያው ታናሽም ስለሆነ በሞራልም እርሱ ቢያሸንፍ ደስ ይላታል። እኔም ቀድሜ ነግሬያታለው፤ ታላቁን ማክበር ግዴታ አለበት ብዬ መልስ ሰጥቻታለው። የጎሉንም ብዛት ነግሬያት በድንጋጤ ጮሀለች (እየሳቀ…) ያው እርሱ ታዳጊ ስለሆነ ቤተሰቦቼ ብዙ ድጋፍ ያደርጉለታል። ቤተሰቦቼ ለእርሱ ቢያደሉም ውጤቱ ወደ እኔ አድልቷል። ሁሉ ነገር የተሟለው እኔ ጋር ስለሆነ አሸንፌ ወጥቻለው። (እየሳቀ)

ብርሀኑ አሻሞ

በተለያየ ማልያ ከወንድም ጋር መጫወት ያለው ስሜት እንዴት ይገለፃል?

ከወንድሜ ጋር ለሁለተኛ ጊዜ ነው በተለያዩ ክለቦች የተጫወትነው። ያም ቢሆን ከባድ ነው። ከወንድምህ በልጠህ ለመገኘት እልህ ውስጥ ትገባለህ። እርሱ በእግርኳሱ ያሳለፈበት ነገር ጥሩ ስለሆነ እንደርሱ ሆኜ መገኘት እፈልጋለው። የኔ አርአያዬ እርሱ ነው። ብዙ ነገር አድርጎልኛል ብዙ አስተምሮኛል። እርሱን በተለየ ማልያ አብሬው ስጫወት እርሱን በልጬ መገኘት እፈልጋለው። ከእርሱ በላይ ስሜ ገኖ እንዲጠራ እፈልጋለው። ብርሀኑ ማን እንደሆነ ማሳየት ስለምፈልግ ከእርሱ ጋር ተቃራኒ ሆኖ መጫወት በጣም ነው የሚያስደስተኝ።

በአንድ አጋጣሚ በሁለታቹሁም መካከል ፍትጊያ ነበር። ይህ እንዴት ይገለፃል ?

ይገርማቹሀል ሜዳ ውስጥ ስገባ ወንድሜ እንደሆነ እረሳለው። ምክንያቱም የኔ ሥራዬ ነው። የሚከፍለኝ ሲዳማ እንጂ ኤፍሬም አይደለም። ስለዚህ ሜዳ ውስጥ ወንድም እንዳለኝ እረሳለው። ሥራዬ ብቻ ላይ ነው ትኩረት የማደርገው። ኤፍሬም ጋር ፍትጊያ እንደነበረኝ አስታውሳለው ግን ሥራዬ ላይ ነው ትኩረት የማደርገው።

ከጨዋታው በፊት ብሽሽቅ ነበር፤ ስለመሸናነፍ ?

ነበር፤ ያው ፉክክር ይኖራል። በቤተሰብም በኩል እናታችን እንዲህ ያለ ነገር ስለምታነሳ አልሸነፍ ባይነት በሁለታችን በኩል አለ። ምንም ታላቄ ቢሆንም እኔ በእርሱ መሸነፍ አልፈልግም። ለዛሬ ተሳክቶለታል፤ በቀጣይ ግን አይደገምም።

ከጨዋታ በኃላ ቤተሰብ ምን አለ?

የሆነ አጋጣሚ ላይ ኤፍሬም ላይ ጥፋት ሰርቼበት ነበር። እና ማዘር ደውላልኝ ልጄን ልትሰብረው ነው ብላኛለች። (በጣም እየሳቀ) ‘ሁለታችሁ ስትገናኙ እንኳን ሸሸት አትሉም እንዴ? በመሐከላቹ ያለው ችግር ምንድነው?’ ብላ ጠይቃኛለች። አይ ሰላም ነው አታስቢ አልኳት። እርሷም ትረዳናለች ምክንያቱም ብዙ ተጫዋች ያፈራ ቤተሰብ ስለሆነ በሆነው ነገር ተረድታኛለች።

ከኤፍሬም አሻሞ ምኑን ታደንቅለታለህ ?

አልሸነፍ ባይነቱን በጣም አደንቅለታለው። በጣም ጠንካራ ሰው ነው። በብዙ ውጣ ውረድ የተፈተነ ሰው ነው። ይህን ነገሩን በጣም ነው የምወድለት።

ከዚህ በኃላ በአንድ ማልያ እንጠብቅ ?

እንደ ፈጣሪ ፍቃድ በአንድ ማልያ ብንጫወት ደስ ይለኛል። ከወንድም ጋር መጫወት ምን ያህል እንደሚያስደስት አውቀዋለው። እውነተኛ ክፍተትህን አይቶ ሊነግርህ የሚችለው ወንድም ብቻ ነው።

የውድድር ዓመቱ ለአንተ እንዴት ነው? ለብሔራዊ ቡድን መጫወትስ ምን ታስባለህ?

ራሴን ኢትዮጵያ ውስጥ ካሉ የተከላካይ አማካዮች ጋር ማነፃፀር አልፈልግም። መፎካከር የምፈልገው ከውጪዎች ጋር ነው። ለብሔራዊ ቡድን መመረጥ እና መጫወት እፈልጋለው። ለሀገሩ መጫወት የማይፈልግ አለ ብዬ አላስብም። ከድሮም ጀምሮ ምኞትም አለኝ። ከጎኔ ያሉ ተጫዋቾች ሲጠሩ በጣም መንፈሳዊ ቅናት እቀናለው። ምናለ እኔ ተጠርቼ ወንድነቴን ባሳየው እላለው። ብጠራ ደስ ይለኛል።

በመጨረሻ እናቴን፣ ወንድሜን፣ እህቴን፣ ባለቤቴን በጣም ማመስገን እፈልጋለው። በተለይ የምወዳት የማከብራት የማፈቅራት ባለቤቴን አመሰግናለው። እናቴን ደግሞ ከምንም በላይ እወዳታለው። እመብርሀንንም አመሰግናለሁ።


ከዚህ ቀደም ስለ አሻሞ ወንድማማቾች ያዘጋጀነው ፅሁፍን ለማንበብ ከታች ያለውን ሊንክ ይጫኑ:-

አምስት ተጫዋቾችን ያፈራው እና አራቱን ለስኬት ያበቃው የአሻሞ ቤተሰብ


© ሶከር ኢትዮጵያ