ፕሪምየር ሊግ | የተለያዩ የቅጣት ውሳኔዎች ተወስነዋል

ቤትኪንግ የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ የስምንተኛ ሳምንት ጨዋታዎች ትናንት መጠናቀቃቸውን ተከትሎ አወዳዳሪው አካል የተለያዩ የቅጣት ውሳኔዎችን አሳልፏል። 

ከአንድ ቀን እረፍት በኋላ ዘጠነኛ ሳምንቱን ነገ የሚጀምረው ሊጉ በ8ኛ ሳምንት ጨዋታዎች በተከሰቱ ግድፈቶች ላይ የሚከተሉት ውሳኔዎች አሳልፏል።

– የሰበታ ከተማ ቡድን መሪ የሆነው አቶ አንበስ መገርሳ ማከሰኞ ጥር 11 ቀን 2013 ክለቡ ከባህርዳር ከተማ ጋር ባደረገው የ8ኛ ሳምንት ጨዋታ ካለቀ በኋላ የዕለቱን ዳኛች አፀያፊ ስድብ መሳደባቸው ከዋና ዳኛውና ከጨዋታ ታዛቢ ሪፖርት የቀረበባቸው በመሆኑ የቡድን መሪው ለፈፀሙት ጥፋት በፌዴሬሽኑ የዲሲፕሊን መመሪያ መሠረት 6 ጨዋታ እንዲታገዱና 5000 ብር ቅጣት እንዲከፍሉ ወስኗል። አቶ አንበስ መገርሳ የሊግ ካምፓኒው የቦርድ አባል መሆናቸው ይታወቃል።

-የሰበታ ከተማው ግብ ጠባቂ ሰለሞን ደምሴ ክለቡ ከባህር ዳር ከተማ ጋር ያደረገው ጨዋታ ካለቀ በኋላ የዕለቱን ዳኛች አፀያፊ ስድብ መሳደቡ ከዋና ዳኛውና ክጨዋታ ታዛቢ ሪፖርት
ቀርቦበታል። ተጫዋቹ ለፈፀመው ጥፋት በፌዴሬሽኑ የዲሲፕሊን መመሪያ መሰረት 3 ጨዋታ እንዲታገድ እና 3000 ብር የገንዘብ ቅጣት እንዲከፍል ወስኗል።

– ሌላው የሰበታ ከተማ ተጫዋች ያሬድ ሀሰን ከባህር ዳር ከተማ ባደረጉት ጨዋታ 71ኛ ደቂቃ ላይ ዳኛን አፀያፊ ስድብ በመሳድብ ከጨዋታ ሜዳ የተወገደ ስለመሆኑ ሪፖርት ቀርቦበታል። በዚህም 3 ጨዋታ እንዲታገድ እና በተጨማሪ የገንዘብ ቅጣት ብር 3000 እንዲከፍል ተወስኗል።


© ሶከር ኢትዮጵያ