“በጎዳና ከሚኖሩ ልጆች ጋር አብሬ እውል ነበር” – ቢንያም ፍቅሬ

በቤትኪንግ የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ እየተመለከትናቸው ከመጡ ተስፈኛ ወጣት ተጫዋቾች መከከል አንዱ የሆነው የወላይታ ድቻው ቢንያም ፍቅሬ ስለ እግር ኳስ ህይወቱ ይናገራል።

አባቱ ፍቅሬ የቡሌ ሆራ ክለብ ተጫዋች ነበሩ። የአባቱን የእግር ኳስ እንቅስቃሴ እየተመለከተ በከተማዋ በሚገኝ አንድ ፕሮጀክት ስር እየተጫወተ ወላጅ አባቱም እያሰለጠኑት ያደገው ይህ ተስፈኛ ወጣት በድንገት ያላሰበው አሳዛኝ ክስተት ይፈጠራል፤ ወላጅ እናቱ በድንገት ከዚህ ዓለም በሞት ይለዩታል። ይህ በልጅነት ዕድሜው ያልጠበቀው አሳዛኝ ሁኔታ በእግር ኳሱ ሩቅ አልሞ በሚጓዘው ጉዞ ውስጥ ፈተና ቢሆንበትም ወደ አክስቱ መኖርያ ከተማ ወላይታ ሶዶ በማቅናት የጨለማው ህይወቱ የብርሃን ተስፋ እንዲያይ አድርጎታል። ወደ ፊት ትልቅ ተጫዋች እንደሚሆን የተረዱት የቀድሞ የወላይታ ድቻ ሥራ አስኪያጅ የአሁኑ የሊግ ካምፓኒ የቦርድ አባል አቶ አሰፋ ሀሲሶ በቢንያም እዚህ ደረጃ መድረስ ትልቅ አበርክቶ ይወስዳሉ። በ2011 ከ17 ዓመት ቡድኑን እንዲቀላቀል አስተዋፆኦ አድርገዋል። በታዳጊ ቡድኑ አንድ ዓመት ቆይታ በኃላ በአሰልጣኝ ገብረክርስቶስ ቢራራ አማካኝነት ተስፋ ቡድን ሳይጫወት በቀጥታ ዋናው ቡድን ማደግ ችሏል። በዘንድሮ ዓመት በስምንተኛው እና ዘጠነኛው ሳምንት የቡድኑ ጨዋታዎች ላይ አቅሙን እያሳየ ሲገኝ በተለይ ኢትዮጵያ ቡናን በረቱበት ጨዋታ ጥሩ በመንቀሳቀስ በመልሶ ማጥቃት ያገኘውን ኳስ በነፃ አቋቋም ላይ ለነበረው ፀጋዬ ብርሀኑ አሳልፎለት የተቆጠረው ጎል የልጁን አቅም አጉልቶ የሚያሳይ ነበር። በአጋጣሚውም ወደፊት ተደጋጋሚ የመጫወት ዕድል የሚያገኝ ከሆነ ትልቅ ተስፋ የሚጣልበት መሆኑን አሳይቷል። ብዙም የማያወራው ቢንያም ስለ እግር ኳስ አጀማመሩ እና ስላሳለፈው ህይወት እና በቀጣይ ስለሚያልመው ህልም ለሶከር ኢትዮጵያ ይህንን ብሏል።

” የተወለድኩት ቡሌ ሆራ ከተማ ነው። አባቴ ለቡሬ ሆራ ይጫወት ስለነበር እኔ እግርኳስ ተጫዋች እንድሆን ምክንያት ሆኖኛል፤ በተለያየ ጊዜም እያሰራኝ ቆይቷል። በኋላም ፕሮጀክት እየተጫወትኩ እናቴ ህይወቷ በማለፉ አክስቴ ወደምትኖርበት ከተማ ወላይታ በመምጣት መኖር ጀመርኩ። ያው አንዳንድ ሰዎች ከጎዳና ከሚኖሩ ልጆች ጋር አብሬ ስውል ስለሚያዩኝ በጎዳና የምኖር ይመስላቸዋል እንጂ የጎዳና ኑሮ አልኖርኩም። ወላይታ ድቻ የታዳጊዎች ምልመላ እንደሚያደርግ ሲነገር ስሰማ እዛ በመሄድ ሙከራ አድርጌ በ2011 ከ17 ዓመት በታች ቡድን እንድጫወት ተደርጎ ብዙም ሳልቆይ በአሰልጣኝ ገብረ ክርስቶስ ቢራራ አማካኝነት ወደ ዋናው ቡድን በ2012 ማደግ ችያለሁ።

” በአሁኑ ወቅት የመጫወት ዕድል እያገኘሁ ነው። በዚህም ደስተኛ ነኝ። የበለጠ ራሴን ወደ መጀመርያ አሰላለፍ ውስጥ ማስገባትን አስባለሁ። ሁሌም ይሄ እንዲሳካ ጠንክሬ እየሰራሁ ነው። የባለፈው የቡና ጨዋታ ወቅት ጥሩ ለመንቀሳቀስ ችያለሁ ፤ የጎል አጋጣሚ ለመፍጠር ሞክሬም ግብ ጠባቂው አድኖብኛል። ፀጋዬ ላስቆጠራት ጎል ምክንያት በመሆኔ የበለጠ እንድሰራ ብርታት ሆኖኛል።

” ወደፊት ብዙ ነገር አስባለሁ። ማንኛውም ተጫዋች ማሳካት የሚፈልገውን ትልቅ ተጫዋች የመሆን፣ ለብሔራዊ ቡድን የመጫወት እና ከሀገሬ ውጪ መጫወትንም አስባለሁ።” ብሏል

ይህ ተስፈኛ ወጣት በወላይታ ድቻ ታዳጊ ቡድን የመጫወት ዕድል እንዲያገኝ ከፍተኛውን ሚና የተወጡት የክለቡ የቀድሞ ሥራ አስኪያጅ አቶ አሰፋ ሞሲሳ ስለ ቢንያም ፍቅሬ ይህን ምስክርነት ሰጥተውናል።

” ልጁ አቅም እንዳለው ያየሁት ከ17 ዓመት በታች ምልመላ ሲደረግ ነው። እንዲያውም በምልመላው ወቅት ከአንዴም ሁለቴ ቀንሰውት የነበረ ቢሆንም ‘ይህ ልጅ ወደ ፊት ትልቅ ተጫዋች ይሆናል’ ብዬ ነግሬያቸው ነው በቡድኑ እንዲቆይ የሆነው። በታዳጊ ቡድኖች ካምፕ እንዲኖሩ አይፈቀድም ፤ በክለቡ ደንብ መሠረት። እርሱ ግን የተለየ ምክንያት ስለነበረው በካምፕ እንዲኖር አድርጌዋለሁ። ይገርማችኋል ከ17 ዓመት በታች ቡድን በአንዴ ነው ወደ ዋናው ቡድን ማደግ የቻለው። በዚህ ዕድሜው ብዙ አቅም እንዳለው እያሳየ ነው። ለድቻ ጥሩ አገልግሎት እየሰጠ ይገኛል። የበለጠ ልምድ እያገኘ ሲሄድ ትልቅ ደረጃ እንደሚደርስ እርግጠኛ ነኝ። እዚህ ደረጃ ደርሶ በማየቴም በጣም ነው ደስ የሚለኝ።” ብለዋል።


© ሶከር ኢትዮጵያ