ነገ ረፋድ ላይ የሚደረገውን ጨዋታ የተመለከቱ ጉዳዮችን እንዲህ አንስተናል።
በየፊናቸው እስካሁን አንድ ሽንፈት ብቻ የገጠማቸው ሁለቱ ቡድኖች በአዳማ ከተማ ላይ ካስመዘገቧቸው ድሎች መልስ የሚገናኙበት ጨዋታ ጥሩ ፉክክር እንደሚያስመለክተን ይገመታል።
ከስድስት ቀናት ዕረፍት በኋላ ወደ ሜዳ የሚመለሰው ወልቂጤ ከተማ ራሱን ከዋናዎቹ የሊጉ ተፎካካሪዎች ጋር ለመቀላቀል ከነገው ጨዋታ የሚገኙት ነጥቦች በእጅጉ ያስፈልጉታል። ከበላዩ ከሚገኙት ኢትዮጵያ ቡና ፣ ሀዲያ ሆሳዕና እና ባህር ዳር ከተማ ጋር በተገናኘባቸው ጨዋታዎች ሽንፈት ያልገጠመው ወልቂጤ አሁን ላይ በሰንጠረዡ አናት ላይ ለሚገኘው ፋሲል ከነማም ፈተና መሆኑ የሚቀር አይመስልም። በመጠኑ ተለዋዋጭነት የሚታይበት የአሰልጣኝ ደግአረግ ይግዛው ቡድን ጥንቃቄን ያማከለ ዓይነት የጨዋታ ዕቅድ ይዞ ወደ ሜዳ እንደሚገባ ሲጠበቅ የተጨዋቾች እና የአደራደር ምርጫው ላይም ያልተጠበቁ ቅያሪዎችን ሊያደርግ ይችላል።
በመስመር አጥቂነት የሚጠቀማቸውን ተጫዋቾች ጨምሮ በርከት ያሉ አማካይነት ባህሪ ያላቸው ታታሪ ተጫዋቾችን የያዘው ወልቂጤ የፋሲልን ከመስመሮች የሚነሱ እና በቀጥታ ከመሀል ሜዳው የሚመነጩ ጥቃቶችን ለመመከት ይህ የተሰላፊዎቹ ባህሪ ሊጠቅመው እንደሚችል ይገመታል። ፊት መስመር ላይ የነበረበትን ችግር ተከትሎ ተጫዋቾችን ሲለዋውጥ ቢከርምም ሁለት ተከታታይ ጨዋታዎች ላይ ግብ ያስቆጠረው የሄኖክ አየለ መልካም አቋም ላይ መገኘት ለቡድኑ ጥሩ ዜና የሆነም ይመስላል። በነገው ጨዋታ ቡድኑ ጫናው ከበረታበት ሄኖክን በፈጣን ሽግግር በቶሎ ወደ ፊት በሚደርሱ ኳሶች ማግኘትን ሁለተኛ ዕቅዱ አድርጎ ሊገባ የሚችልበት ዕድል ይኖራል።
ምንም ግብ ሳያስተናግድ ሦስት ተከታታይ ጨዋታዎችን በድል የተወጣው ፋሲል ከነማ ከሀያ ነጥብ የተሻገረ የመጀመሪያው የሊጉ ቡድን ለመሆን ነገ ወልቂጤን መርታት ይኖርበታል። ከተጋጣሚው ያነሰ የማገገሚያ ዕረፍት የነበረው ፋሲል አዳማ ከተማን በተለይም በሁለተኛው አጋማሽ የተጋነነ ጉልበት ሳያወጣ መርታት መቻሉ ተጠቃሚ እንደሚያደርገው ይታሰባል። እስካሁን ከኢትዮጵያ ቡናው ጨዋታ ውጪ ግብ ማስቆጠሩን ያላቆመው አጥቂው ሙጂብ ቃሲም አሁንም የፋሲልን የፊት መስመር አስፈሪ እንዳደረገው ቀጥሏል። ነገም ግዙፉ አጥቂ በቶማስ ስምረቱ እና ዳግም ንጉሴ ጥሩ ጥምረት ላይ የደረሰ ለሚመስለው የወልቂጤ ከተማ የኃላ ክፍል ከፍ ያለ ፈተና መስጠቱ የሚቀር አይመስልም።
በፋሲል ወቅታዊ አቋም ውስጥ አማካይ ክፍል ላይ ያለው የተጨዋቾች አማራጭ መበራከት ለአሰልጣኝ ሥዩም ከበደ ለተለዋዋጩ የወልቂጤ አቀራረብ ምላሽ ለመስጠት የተመቸ ዕድል የሚፈጥርላቸው ይመስላል። በቅርብ ጨዋታዎች ላይም አብዛኞቹን አማካዮቻቸውን በጨዋታ ሂደት ውስጥ በመሞከር እና ከእንቅስቃሴያቸውም ውጤት ማግኘት የቻሉት ፋሲሎች ጨዋታውን ከአዳማው ግጥሚያ በመጠኑ ቀነስ ባለ ጀብደኝነት ለማስኬድ የሚረዳ የአማካይ ክፍል ምርጫን እንደሚከተሉ ይጠበቃል። በዚህም ከሀብታሙ ተከስተ ጎን የወልቂጤን የመሀል ክፍል ለመቆጣጠር የሚረዳ አንድ አማካይን ሊጨምሩ ይችላሉ። ይህም ቡድኑ በቅብቡሎች ወደ ሳጥን ለመግባት ከሚያረገው ጥረት በተጨማሪ ከጥልቅ የአማካይ ክፍል ቀጥተኛ ኳሶችን እንዲያገኝ ሊረዳው ይችላል።
በጨዋታው ወልቂጤ ከተማ አሳሪ አልመሀዲን በቅጣት ከማጣቱ በቀር ሌላ በጉዳትም ሆነ በቅጣት የሚያጣው ተጫዋች አይኖርም። በፋሲል በኩልም የረጅም ጊዜ ጉዳት ላይ ከሚገኘው ሰዒድ ሀሰን ውጪ ቀሪው የቡድኑ ስብስብ ለጨዋታው ዝግጁ መሆኑን አረጋግጠናል።
የእርስ በእርስ ግንኙነት
– በተሰረዘው የውድድር ዓመት ወልቂጤ ከተማ 1-0 ያሸነፈበትን ጨዋታ ሳይጨምር ሁለቱ ቡድኖች የመጀመሪያ የሊግ ግንኙነታቸውን ያደርጋሉ።
ግምታዊ አሰላለፍ
ወልቂጤ ከተማ (4-3-3)
ጀማል ጣሰው
ተስፋዬ ነጋሽ – ቶማስ ስምረቱ – ዳግም ንጉሴ – ረመዳን የሱፍ
በኃይሉ ተሻገር – ሀብታሙ ሸዋለም – አብዱልከሪም ወርቁ
ፍሬው ሰለሞን – ሄኖክ አየለ – ያሬድ ታደሰ
ፋሲል ከነማ (4-2-3-1)
ሚኬል ሳማኬ
እንየው ካሳሁን – ከድር ኩሊባሊ – ያሬድ ባየህ – አምሳሉ ጥላሁን
ይሁን እንዳሻው – ሀብታሙ ተከስተ
ሳሙኤል ዮሐንስ – ሱራፌል ዳኛቸው – ሽመክት ጉግሳ
ሙጂብ ቃሲም
© ሶከር ኢትዮጵያ