” ከጎል መራቅ የለብኝም ብዬ አምናለሁ” ሙኽዲን ሙሳ

እድገቱ በየዓመቱ እየጨመረ የመጣው እና የአዕምሮ ፍጥነቱን ተጠቅሞ የአጨራረስ ብቃቱን እያስመለከተን ከመጣው ወጣቱ አጥቂ ሙኸዲን ሙሳ ጋር ቆይታ አድርገናል።

ምሥራቃዊቷ ከተማ ድሬዳዋ ልዩ ስሙ ኮኔል አካባቢ ተወልዷል። ሙኸዲን ሙሳ በተወለደበት አካባቢ አሸዋ ሜዳ እግርኳስ መጫወት ጀምሮ በኃላም በቀድሞ ናሽናል ሲሚንት ክለብ ውስጥ አባል ሆኖ በመጫወት ችሏል። ፈጣን እና አስገራሚ እድገቱን የተመለከተው ድሬዳዋ ከተማ በ2010 ወደ ዋናው ቡድን እንዲያድግ አድርገውት ለመጀመርያ ጊዜ በድሬ ማልያ ከቅዱስ ጊዮርጊስ ጋር በነበረ ጨዋታ ተቀይሮ በመግባት የፕሪምየር ሊግ ጨዋታውን ማድረግ ጀምሯል።

“ክሪስ” በሚል ቅፅል ስም ይበልጥ የሚታወቀው የድሬዳዋው አጥቂ ካለፈው ዓመት የጀመረው ጥሩ የሚባለው የእግርኳስ ህይወቱ እየተሻሻለ መጥቶ ዘንድሮ በሦስት የውጪ ሀገር አጥቂዎች መሐል ሆኖ መድመቁን ቀጥሏል። እስካሁን አምስት ጎል በማስቆጠር የከፍተኛ ጎል አስቆጣሪነት ዝርዝር ውስጥ መካተት የቻለው መኸዲን በተለያየዩ መንገዶች የሚያገኛቸውን የጎል አጋጣሚዎች ከሚጨርስበት ብቃቱ አኳያ ከዚህ በኃላም ተጨማሪ ጎሎችን ማስቆጠር እንደሚችል መገመት ይቻላል። አሁን የሚገኝበትን ወቅታዊ ሁኔታ አስመልክተን ፈጣኑን አጥቂን አውርተነው ተከታዩ ሀሳቡን አካፍሎናል።

ስለ እግርኳስ አጀማመሩ

ከልጅነቴ ጀምሮ እግርኳስን በጣም ነው የምወደው፤ ወደ ፊትም ትልቅ ተጫዋች የመሆን ፍላጎት ነበረኝ። የተወለድኩበት ኮኔል አሸዋ ሜዳ ስላለ እዛ ሜዳ ኳስ እጫወት ነበር። እንቅስቃሴዬን ተመልክተው በ2009 ከፍተኛ ሊግ ለነበረው ናሽናል ሲሚንት ለአንድ ዓመት መጫወት ችያለው።

ወደ ድሬዳዋ ከተማ ስለማምራቱ

በ2010 ድሬደዋ ከተማን መቀላቀል ችያለሁ። በተወሰነ መልኩ ታዳጊ ስለነበርኩ በፍጥነት የመሰለፍ ዕድል አላገኝም ነበር። አስታውሳለው ድሬዳዋ ላይ ከቅዱስ ጊዮርጊስ ጋር በነበረው ጨዋታ ለመጀመርያ ጊዜ ተቀይሬ በመግባት ተጫውቻለሁ። በመቀጠል በአዲስ አበባ ስታዲየም በቋሚ አሰላለፍ መግባት ከኢትዮ ኤሌትሪክ ጋር መጫወት ችያለሁ። 

ስለ ሊጉ የመጀመርያ ጎሉ

በጣም የሚገርመው ገጠመኝ ለድሬ የመጀመርያ ጨዋታ የተጫወትኩት 2010 ከቅዱስ ጊዮርጊስ ጋር ነበር፤ ተቀይሬ በመግባት። ከሁለት ዓመት በኃላ ዓምና በድሬ ማልያ የመጀመርያ ጎሌን አዲስ አበባ ስታዲየም በቅዱስ ጊዮርጊስ 3-2 ስንሸነፍ ተቀይሬ በመግባት ሁለተኛ ጎልን ለመጀመርያ ጊዜ አስቆጥሬያለሁ።

የመጀመርያ ጎሉ መሆኑ የፈጠረበት ስሜት

ያው ብዙም የተለየ ነገር አልፈጠረብኝም። ምክንያቱም የማሸነፊያ ጎል አይደለም ያስቆጠርኩት። ያ በመሆኑ የተለየ ስሜት አልፈጠረብኝም። ሆኖም ግን ቅዱስ ጊዮርጊስ በሚያክል ትልቅ ቡድን ላይ የመጀመርያ ጎሌን በማስቆጠሬ የበለጠ መነሳሳት ሊፈጥርብኝ ይችላል።

የድሬዳዋ ቁልፍ ተጫዋች ስለመሆኑ

ሁሌም ጥሩ ተጫዋች ለመሆን እጥራለው። ዘንድሮ ደግሞ ለቡድኑ አንድ ነገር ለመስጠት ስዘጋጅ ቆይቻለው፤ ያም ውጤታማ አድርጎኛል። ይህንን አስቀጥዬ መቀጠል አስባለሁ።

ስለ ጎል አጨራረስ ብቃቱ

በተፈጥሮ ያገኘሁት ቢሆንም አንድ አጥቂ በየትኛው አጋጣሚ የኳሷን አቅጣጫ በመከተል ከጎል መራቅ የለብኝም ብዬ አምናለው። ፍጥነትም ስላለኝ ቶሎ ነው ወደ ጎል የምደርሰው። ከዛ በኃላ ነው ወደ ውሳኔ የምገባው። ለዛ ይመስለኛል በየትኛውም ሁኔታ ፍጥነቴን ተጠቅሜ ይሄን የማደርገው። ያው የአጨራረስ ድክመት ቢኖረብኝም።

ድክመቱን በቀጣይ ስለማስተካከል

የአጨራረስ ችግር አለብኝ። ይህ ደግሞ አንዳንዴ ከልምድ ማጣት የሚመጣ ይመስለኛል። ይሁን እንጂ የአጨራረስ ችግሬን እያረምኩ ጎል የማስቆጠር አቅሜን ከፍ ማድረግ እፈልጋለሁ።

ጎል አግቢ ፉክክር ውስጥ ስለ መግባት

በጣም ትልቁ እቅዴ ይሄ ነው። እስካሁን አምስት ጎል አለኝ ከዚህ በኋላ ኢትዮጵያ ውስጥ አሉ ከሚባሉት ጌታነህ፣ ሙጂብ እና አቡበከር ጋር መፎካከር እፈልጋለው። እነርሱ የደረሱበት ደረጃ መድረስ እፈልጋለው።

ስለ ቅፅል ስሙ

“ክሪስ” የሚለውን ስም ያወጡልኝ በሰፈር ውስጥ አብረውኝ የሚጫወቱ ልጆች ናቸው። የክሪስቲያኖ ሮናልዶን ስም በማሳጠር የሰጡኝ ስያሜ ነው።

ምስጋና

በራሴ ጥረት እዚህ ደርሻለው ይህ እንዳለ ሆኖ የሠፈር ጓደኞቼ ወንድሞቼ ከጎኔ በመሆን ብርታቱን ሰጥተውኛል። የቡድን አጋሮቼ በተለይ ኤልያስ፣ ያሬድ፣ ረመዳን ሁሌም ነው የሚመክሩኝ። ኤልያስ ማሞ ከዓምና ጀምሮ ከአጠገቤ ሳይለይ በጣም ነው የሚመክረኝ፣ ከጎኔ በመሆን ድጋፍ የሚያደርግልኝ፣ እነርሱን አመሰግናለሁ።

ወደ ፊት ስለሚያስበው

አሁን ያለኝን አቅም አሳድጌ ድሬን በደንብ ማገልገል አስባለሁ። በዚህ ብቻ ሳላበቃ ለሀገሬ ብሔራዊ ቡድን መጫወት እፈልጋለሁ።


© ሶከር ኢትዮጵያ