ጥቂት ነጥቦች በኢትዮጵያ ከ20 ዓመት በታች ውድድር ዙርያ

በ14 ክለቦች መካከል በሁለት ምድብ ተከፍሎ የሚደረገው የኢትዮጵያ ከ20ዓመት በታች ፕሪምየር ሊግ ከጥር 30 ጀምሮ በአዳማ እና አሰላ ከተማዎች መካሄድ ጀምሯል። እኛም ይህን ውድድር አስመልክቶ በጥቅሉ የታዘብናቸውን ነጥቦች ለማንሳት ወደናል።

👉 የሀዲያ ሆሳዕና ውድድሩን መቀላቀል

በክረምቱ የዝውውር መስኮት በቤትኪንግ የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ የሚካፈለው ሀዲያ ሆሳዕና በተሰረዘው የውድድር ዘመን የተንገዳገውን ቡድን ለመጠገን በማለም ከግማሽ ደርዘን በላይ የሚሆኑ የሀገር ውስጥ እና የውጭ ሀገር ዜግነት ያላቸውን ተጫዋቾችን ማስፈረሙ አይዘነጋም ። በዚህም መነሻነት እና አብዛኞቹ ተጫዋቾች አሰልጣኛቸውን ተከትለው ከአዳማ ከተማ መምጣታቸው ጭምር ሲያነጋግር መቆየቱ የቅርብ ጊዜ ትውስታችን ነው።

ታድያ በዚህ አካሄድ ክፉኛ ሲብጠለጠሉ የሰነበቱት የክለቡ አመራሮች ይህ ጊዜያዊ ውጤትን ታሳቢ ያደረገው አካሄድ አዋጭ አለመሆኑን የተረዱ ይመስላል። በዚህም ቡድኑ ከዚህ ቀደም ያልነበረውን የእድሜ እርከን ቡድኖችን ዘንድሮ ግን ለመጀመሪያ ጊዜ አቋቁመዋል።

ባሳለፍነው ሳምንት ጅማሮውን ባደረገው የኢትዮጵያ ከ20 ዓመት በታች ፕሪምየር ሊግ በመጀመሪያ የጨዋታ ሳምንት ሀላባ ከተማን የገጠመው ቡድኑ 3-1 በሆነ ውጤት በረታበት ጨዋታ የሀዲያ ሆሳዕና ስብስብ በእጅጉ ተስፋ የሚጣልበት ቡድን መሆኑን ፍንጭ ሰጥቷል።

በአካባቢው በቂ ሥራ አለመሰራቱ እንጂ በርካታ አቅም ያላቸው ተጫዋቾች መኖራቸውን ፍንጭ በሚሰጥ መልኩ ጎላ ጎላ ያለ አካላዊ ቁመናን ከአካል ብቃት አጣምረው የያዙ ተጫዋቾችን ያካተተው ቡድኑ ገና ጅምር ቢሆንም በመጀመርያ ጨዋታቸው ያሳዮት አስደናቂ ብቃት ከዚሁ ቡድን ውስጥ በቀጣይ ዓመት በዋናው ቡድን ለመጀመሪያ ተሰላፊነት መፎካከር የሚችሉ ከአምስት በላይ ተጫዋቾችን ማግኘት የሚያስችል ይመስላል።

እርግጥ ገና ጅምር ቢሆንም የቡድኑ አመራሮች ይህን ቡድን እንዲቋቋም በማድረጋቸው ከፍ ያለ ምስጋና የሚገባቸው ሲሆን ይህም አካሄድ በቀጣዮቹ ጥቂት ዓመታት ለዋናው ቡድን የሚኖረው አበርክቶ ቀላል የሚባል እንደማይሆን ይጠበቃል።

👉 ፍሬውን እያጣጣመ ለዛፉ ግድ ያልሰጠው የፋሲል ከነማ አመራር

የቤትኪንግ የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግን በመምራት ላይ የሚገኘው ፋሲል ከነማ በስብስቡ ውስጥ በተለይ በተጠባባቂነት በርከት ያሉ በቡድኑ የእድሜ እርከን ቡድኖች ውስጥ ያለፉ ተስፈኛ ወጣቶችን ይዟል።

እነዚህ ተጫዋቾችም በተደጋጋሚ ተቀይረው ወደ ሜዳ በመግባት የቡድኑን ውጤት ላይ በጎ ተፅዕኖ ሲያሳድሩ እየተመለከተን እንገኛለን። ዓለምብርሃን ይግዛው፣ ናትናኤል ገ/ጊዮርጊስ ፣ አቤል እያዩ የመሰሉ በዋናው ቡድን ተፅዕኖ ለመፍጠር እየተንደረደሩ የሚገኙ ባለተሰጥኦ ታዳጊዎችን ያፈራው የፋሲል ከነማ የእድሜ እርከን ቡድን አሁን ላይ ግን የለም።

ቡድኖች በቀጣይነት ተፎካካሪ ሆነው እንዲዘልቁ ዝውውር መስኮቶች በተከፈቱ ቁጥር በረብጣ ገንዘብ ከሌሎች ክለቦች የበቁ ተጫዋቾችን ማስፈረማቸው አይቀሬ ጉዳይ ቢሆንም በክለቡ ውስጥ ያደጉ ክለቡን ጠንቅቀው የሚያውቁ ታዳጊዎችን መጠቀም ደግሞ ከተጫዋቾቹ ሜዳ ላይ ከሚሰጡት ያልተቆጠበ አበርክቶ ባልተናነሰ ለዝውውር የሚወጣ ወጪን ከመታደግ አልፈው በቀጣይ በሽያጭ ክለቡን ሊጠቅሙበት የሚችሉት መንገድ መኖሩም ይታመናል።

እንደ ፋሲል ከነማ ያለ የዕድሜ እርከን ፍሬ የሆኑትን ተጫዋቾችን ጣዕም እያጣጣመ የሚገኝ ቡድን ጠንካራ የነበሩትን የዕድሜ እርከን ቡድኖቹን መበተኑ ክለቡን ያለ መሰረት በእንጥልጥል እንደማስቀረት ስለሚቆጠር የክለቡ አመራሮች እና ደጋፊዎች ይህን ቡድን ዳግም ለመመለስ መረባረብ ይገባቸዋል።

👉የሁለቱ አካዳሚዎች አለመሳተፍ

በኢትዮጵያ ደረጃ በንፅፅር በተደራጀ ሁናቴ ታዳጊዎችን በመመልመል ስልጠና የሚሰጡት ሁለቱ በመንግሥት የሚደገፉት የኢትዮጵያ ወጣቶች ስፖርት አካዳሚ እና ጥሩነሽ ዲባባ አካዳሚ በተለያዩ የስፖርት መስኮች ብቁ የሆኑ ስፖርተኞችን የማብቃት ዓላማን ሰንቀው መንቀሳቀስ ከጀመሩ ቆይተዋል።

እርግጥ ነው እነዚሁ የተቋቋሙበት ተቀዳሚ ዓላማን ማሳካት እንጅ በተለያዩ የፉክክር ውድድሮች ላይ የመሳተፍ ግዴታ እንደሌለባቸው ቢታመንም ሰልጣኞቻቸው ከስልጠና ባለፈ መሰል የፉክክር ውድድሮች ላይ መካፈላቸው ለሰልጣኞች በልምምድ ከሚያገኙት እውቀት ባለፈ በትክክለኛው የጨዋታ ሜዳ ላይ እጅግ አስፈላጊ የሆኑ ክህሎቶችን ለማግኘት እንደሚረዳ ይታመናል።

ይህም መሆኑ ታምኖት ቡድኑ ከዚህ ቀደም በነበሩት ዓመታት በተካሄዱት ውድድሮች ላይ ሲካፈል የነበረ ቢሆን ዘንድሮ ግን ቡድኖቹ በውል ባልታወቀ ምክንያት በውድድሩ ሳይካፈሉ ቀርተዋል።

ከዚህ ቀደም ከአካዳዎቹ የፈሩ እንደነ በረከት ደስታ ፣ ሱሌይማን ሀሚድ ፣ እሸቱ ጌታሁንን የመሳሰሉ ተጫዋቾችን ቡድኑ በእድሜ እርከን ውድድሮች ላይ በሚካፈልበት ወቅት በሌሎች ክለቦች እይታ ውስጥ ገብተው ወደ ተለያዩ ክለቦች የመዘዋወር እድል ማግኘታቸው አይዘነጋም ታድያ ቡድኖቹ በዚህ ውድድር ላይ አለመካፈላቸውን ተከትሎ በሁለቱ ማሰልጠኛ ተቋማት የሚገኙ ተስፈኛ ተጫዋቾች የመታየት እና ወደ ሌሎች ክለቦች የመዘዋወር እድላቸው እጅጉን ያጠበበ ውሳኔ ይመስላል።

👉ብዙ የወጠኑት ወልቂጤ ከነማዎች?

ጥቂት ወራትን ወደ ኃላ ስንመለስ የወልቂጤ ከተማ ስፖርት ክለብ በወልቂጤ ከተማ የእግርኳስ ማሰልጠኛ አካዳሚ ገንብቶ ስለማጠናቀቁ እና በጥቂት ወራት ስራ ለማስጀመር ከውጭ የሚመጡ በጎ ፈቃደኛ ባለሙያዎች አልያም በራስ አቅም ወደ እንቅስቃሴ ለመግባት ጥረት የመጀመራቸው ዜና በስፋት መወራት ጀምሮ ነበር።

ከጥቂት ወራት በኃላ ግን የአካዳሚው ነገር የተዘነጋ ይመስላል። ይባስ ብሎም በ2012 በተሰረዘው የውድድር ዘመን ወደ ዋናው ፕሪምየር ሊግ ማደጋቸውን ተከትሎ የተቋቋመው ከ20 አመት በታች ቡድን በዘንድሮው የኢትዮጵያ ከ20 ዓመት በታች ፕሪምየር ሊግ እየተካፈለ አይገኝም።

ደፋር እና በሀገሪቱ እግርኳስ ላይ አንዳች በጎ ተፅዕኖን ይፈጥራሉ በተባሉ አመራሮች የሚመራው ቡድኑ አካዳሚውን እንኳን በተለያዩ ምክንያቶች ወደ ሥራ ለማስገባት ቢቸገርም አምና ያቋቋሙትን የታዳጊ ቡድን ግን ማስቀጠል አለመቻላቸው የሚያስወቅስ ተግባር ነው።

[በኤዲት የተካተተ: የወልቂጤ ቡድን ከሁለተኛው ሳምንት ጀምሮ እየተወዳደረ ይገኛል። ሆኖም በወጣው ፕሮግራም ላይ ስሙ የሌለ ከመሆኑ በተጨማሪ በአንደኛው ሳምንት ጨዋታ አለማድረጉ ልብ ይሏል]

👉በግል ጥረት ይንቀሳቀስ የነበረው አፍሮ ፅዮን አመካፈል

በኢትዮጵያ ከ20 ዓመት በታች ፕሪምየር ሊግ በዋናነት በቁጥር በርከት ከሚሉት በከተማ አስተዳደር ከሚደገፉ ቡድኖች ጋር በአንድ በጎ ፈቃደኛ ተቋም የግል ጥረት ይንቀሳቀስ የነበረው የአፍሮ ፂሆን ቡድን በዘንድሮው ውድድር ላይ አይካፈልም።

እንደሚታወቀው የኢትዮጵያ እግርኳስ ትልልቅ የቢዝነስ ተቋማትን የመሳብ አቅሙ ደካማ መሆኑ ይታወቃል። በዚህ ላይ ጥቂት የእግርኳሱ ፍቅር ኖሯቸው ብቻ ገንዘባቸውን ይዘው የሚመጡ ተቋማት እና ግለሰቦችን ተንከባክቦ ማቆየቱም እንዲሁ ትልቁ ፈተናው ሆኗል።

በአፍሮ ፅዮን ኮንስትራክሽን ይደገፍ የነበረው የእግርኳስ ቡድኑ የኮሮና ቫይረስ መከሰት እና የሀገሪቱ ወቅታዊ ፖለቲካዊ እና ማህበራዊ ሆኔታ ክፉኛ የተቀዛቀዘው የኮንስትራክሽኑ ክፍለ ኢኮኖሚ ሰለባ ሳይሆን አልቀረም። ተስፋ ሰጪ ታዳጊዎችን ያበረክት የነበረው ቡድኑ በፌደሬሽኑ ሆነ ሌሎች አካላት በቂ እገዛ ሳያገኝ ከውድድር ለመውጣት ተገዷል።

👉በመጨረሻ

በፋይናንስ እጥረት ለተጫዋቾች ደሞዝ መክፈል እየተቸገሩ የሚገኙ ቡድኖች በሀገሪቱ ከፍተኛው የውድድር እርከን ከእለት ወደ ዕለት እየተበራከቱ መጥተዋል ፤ ይህ ችግርም የጊዜ ጉዳይ እንጂ አሁን ባለው አካሄድ የሁሉን ክለቦች በር ማንኳኳቱ የሚቀር አይመስልም። ፕሪምየር ሊጉ ከፍተኛ ትኩረት በማግኘቱ መነሻነት የፋይናንስ ችግሩ በስፋት ይነሳል እንጂ ደሞዝ ለተጫዋቾች እና አሰልጣኞች ለመክፈል ቅርቃር ውስጥ የገቡ ክለቦች ቁጥር ወደ ታችኞቹ የሊግ እርከኖች ሲወረድ እጅጉን የከፋ ነው።

ስለዚህም ቡድኖች ህልውናቸውን አፅንተው ለመቀጠል የዛሬን ብቻ ከማሰብ ተላቀው በተነፃፃሪነት አነስ ባለ የፋይናንስ ወጪ ቡድናቸውን በቀጣይነት ማስቀጠል የሚችሉ ታዳጊ ተጫዋቾችን ኮትኮቶ ወደ መጠቀም አሁንም ፊታቸውን ማዞር ይገባቸዋል መልዕታችን ነው የዚህ አካሄድ አንዱ ለመሰል የእድሜ እርከን ቡድኖች የሚሰጠው ትኩረት ከመቼውም የበለጠ መሆን ይኖርበታል።


© ሶከር ኢትዮጵያ