ቅድመ ዳሰሳ | ድሬዳዋ ከተማ ከ ወልቂጤ ከተማ

የአስረኛውን ሳምንት የመጀመርያ ጨዋታ የተመለከቱ ጉዳዮችን እንዲህ አሰናድተንላችኋል።

ከእስካሁኖቹ ጨዋታዎች በተመሳሳይ ሦስት ድሎችን ያስመዘገቡት እና በተከታታይ ደረጃዎች በሰንጠረዡ አጋማሽ ላይ የሚገኙት ድሬዳዋ እና ወልቂጤ እርስ በእርስ በሚያደርጉት የረፋዱ ግጥሚያ የጨዋታ ሳምንቱን ያስጀምራሉ።

ተመጣጣኝ ፉክክር እንደሚደረግበት በሚጠበቀው በዚህ ጨዋታ ጠንከር ያለ የአማካይ ክፍል ፍልሚያ እንደሚታይ ይጠበቃል። በሱራፌል ጌታቸው አዲስ ዓይነት አስተዋፅዖ በተለየ ሁኔታ ለተጋጣሚ የግብ ክልል የቀረበ እንቅስቃሴ ሲያደርግ የተስተዋለው የድሬ የመሀል ክፍል በነገው ጨዋታ ከአዳማው ጨዋታ ይልቅ ጠንከር ያለ ፈተና ይጠብቀዋል። እንደ አብድልከሪም ወርቁ ያሉ በክህሎት ላቅ ያሉ አማካዮችን የያዘው የሠራተኞቹ አማካይ ክፍል በፋሲሉ ጨዋታ ከነበረው የተሻለ የግብ ዕድሎችን የመፍጠር ዓላማ ይዞ በሚገባበት ጨዋታ ይበልጥ በድሬ ሜዳ ላይ ለመገኘት አስቦ የማጥቃት ጉልበቱን ጨምሮ የሚገባ መሆኑ የቦታውን ፍልሚያ ተጠባቂ ያደርገዋል። ከኋላ መስመሩ ጋር ያለውን ክፍተት አጥብቦ እና ከራሱ የግብ ክልል ርቆ ከሚጫወተው ወልቂጤ ጋር ሲተያይ የድሬ ፈጣን የማጥቃት ሽግግር ክፍተቶችን ካገኘ በነ ጁኒያስ ናንጄቦ ድንገተኛ ሩጫዎች በመታገዝ በቶሎ ወደ ሳጥን ውስጥ የመግባት ዕድል እንደሚኖረው ግን መገመት ቀላል ነው።

ሌላው የጨዋታው ትኩረት ሁለቱ ቡድኖች የሚያመሳስላቸው ፊት መስመር ላይ ያላቸው አባካኝነት ጉዳይ ነው። እርግጥ ነው በድሬዳዋ በከል ሙኸዲን ሙሳ በወልቂጤ በኩል ደግሞ ሄኖክ አየለ በቅርብ ጨዋታዎች ያላቸው የመጨረስ ብቃት እንዳለ ሆኖ ቀሪዎቹ የቡድኑ የፊት የመስመር ተሰላፊዎች ግቦችን የሚስቱበት መንገድ ሁለቱን አጥቂዎች የትኩረት ምንጭ ሊያደርጋቸው ይችላል። በሊጉ ምርጥ የመከላከል ሪከርድ ሁለተኛ ደረጃን የሚይዘው ወልቂጤ በዚህ ረገድ የብርቱካናማዎቹን አጥቂዎች እንቅስቃሴ የመቆጣጠር አቅም ሊኖረው ይችላል። ይህን ለማድረግ ግን በእንዳለ ከበደ የቀኝ መስመር የማጥቃት አካሄድ ላይ ያመዘነው ተጋጣሚውን በግራው ወገን ተግቶ መጠበቅ የግድ ይለዋል።

በሌላ ፅንፍም እንዲሁ ከአራት ተከታታይ ጨዋታዎች በኃላ ግብ ያላስተናገደው እና ተደጋጋሚ አስገዳጅ ለውጦችን እያስተናገደ የሚገኘው የድሬዳዋ የኃላ ክፍል ተለዋዋጭ አቀራረብ ባለው የወልቂጤ የማጥቃት ሂደት ሊፈተን የሚችልበት ዕድል ይኖራል። ባለፈው ጨዋታ ላይ ተፅዕኖው ወርዶ ይታይ እንጂ የቡድኑ አማካዮች በፈጣን ቅብብሎች በሳጥን ውስጥ የሚገኙባቸው ዕድሎች በተጋጣሚ የኃላ ክፍል ክፈተት ታግዞ ደክመው የነበሩ የቡድኑ አጥቂዎች እንዲያንሰራሩ በር ሊከፍት ይችላል። በጨዋታው ሳይነሳ የማይታለፈው ሌላኛው ንፅፅር ግን በሁለቱ የግብ ብረቶች መሀል የሚቆሙትን ተጨዋቾች ይመለከታል። በርከት ያሉ ሙከራዎች ሊኖሩት በሚችሉት በነገው ጨዋታ በሊጉ የእስካሁኑ ጉዞ መልካም የውድድር ዓመት እያሳለፉ ከሚገኙት ፍሬው ጌታሁን እና ጀማል ጣሰው ማን ቡድኑን ይታደጋል የሚለው ጉዳይ ተጠባቂ ይሆናል።

የነገው ጨዋታ በሁለቱም ተጋጣሚዎች በኩል ቁልፍ ጉዳቶች ያንዣበቡበት ሆኗል። ድሬዳዋ ከተማ አሁንም የመሀል ተከላካዮቹ ፍቃዱ ደነቀ እና በረከት ሳሙኤል የማይደርሱለት ሲሆን እያገገሙ የሚገኙት የቢኒያም ጥዑመልሳን እና ሄኖክ ኢሳይያስ መድረስም አጠራጣሪ ሆኗል። ወልቂጤ ከተማዎችም በፋሲሉ ጨዋታ በጉዳት ያጡት ፍሬው ሰለሞንን ግልጋሎት ካለማግኘታቸው ሌላ በኃይሉ ተሻገር እና ተስፋዬ ነጋሽም ለጨዋታው አይደርሱም። ከዚህ በላይ ግን አማካይ ክፍሉን በወጥነት ሲያገለግል የነበረው ሀብታሙ ሸዋለም መሰለፍ አጠራጣሪ መሆኑ የቡድኑ ሌላኛው ስጋት ሆኗል። አልሳሪ አልመሐዲ ደግሞ ከቅጣት መልስ ለጨዋታው ዝግጁ ሆኗል።

የእርስ በእርስ ግንኙነት

– በተሰረዘው የውድድር ዓመት ወልቂጤ 1-0 ያሸነፈበትን ጨዋታ ሳይጨምር ሁለቱ ቡድኖች ነገ የመጀመሪያ የሊግ ግንኙነታቸውን ያደርጋሉ።

ግምታዊ አሰላለፍ

ድሬዳዋ ከተማ (4-1-3-2)

ፍሬው ጌታሁን

ምንያምር ጴጥሮስ – ያሬድ ዘውድነህ – ፍሬዘር ካሳ – ዘነበ ከበደ

ዳንኤል ደምሴ

እንዳለ ከበደ – ሱራፌል ጌታቸው – አስቻለው ግርማ

ጁኒያስ ናንጄቦ – ሙኸዲን ሙሳ

ወልቂጤ ከተማ (4-4-2)

ጀማል ጣሰው

ሥዩም ተስፋዬ – ቶማስ ስምረቱ – ዳግም ንጉሴ – ረመዳን የሱፍ

ያሬድ ታደሰ – ሀብታሙ ሸዋለም – አብዱልከሪም ወርቁ – – አሜ መሐመድ

ሄኖክ አየለ – አህመድ ሁሴን


© ሶከር ኢትዮጵያ