ቅድመ ዳሰሳ | ኢትዮጵያ ቡና ከ ባህር ዳር ከተማ

የነገ ከሰዓቱን ጨዋታ የዳሰስንበትን ፅሁፍ እንዲህ እናስነብባችኋላን።

ተከታታይ ደረጃ ላይ የሚገኙት ቡና እና ባህር ዳር ነገ ጥሩ ፉክክር እንደሚያደርጉ የሚጠበቁበት ጨዋታ ከበላይ ያሉትን ሦስት ቡድኖች አካሄድ ለመቆጣጠር ለሁለቱም ትልቅ ድርሻ ይኖረዋል።

ኢትዮጵያ ቡና ከሦስት ተከታታይ ጨዋታዎች በኋላ ሽንፈት አግኝቶታል። ተመራጭ ባደረገው የማይለዋወጥ የአጨዋወት ዘይቤው ውስጥ በመከላከሉ ረገድ የሚከፍለው መስዕዋትነትም እንደቀጠለ ነው። አስጨናቂ ባልሆኑ እና በቀላሉ ሊድኑ በሚችሉ ኳሶችም ጭምር ግብ ሲያስተናግድ መታየቱ ግን ለችግሩ ከወትሮው የተለየ ትኩረት እንዲሰጥ ምንአልባትም ከኃላ የተጫዋቾች ለውጥ እንዲያደርግ ሊገፋፋው የሚችል ጉዳይ ነው። ያ ካልሆነ ግን ሁሌም በስህተት ከሚቆጠርበት የግብ መጠን በላይ አስቆጥሮ ጉድለቱን ማረም በየጨዋታው የሚጠብቀው ፈተና መሆኑ ነው። ይህ እንዲሆን በተለይም እንደነገው በቁጥር የበረከቱ ዕድሎች እንደልብ ላይገኙ በሚችሉባቸው ጨዋታዎች ላይ የአቡበከር ናስር እና ሀብታሙ ታደሰ የአጨራረስ ብቃት ከፍ ብሎ መገኘት የሌሎች ተሰላፊዎች ግብ አስቆጣሪነት ባህሪ ተሸሽሎ መቅረብ ይኖርበታል፡፡

በወላይታ ድቻው ጨዋታ ወደ መሀል ሜዳው አብዝቶ ከሚጠጋው የኃላ ክፍሉ ጀርባ የሚተወው ክፍተት ለጥቃት እንደሚዳርገው በድጋሚ ያሳየው ቡና ነገም ለባህር ዳር ፈጣን ሽግግር አንዳች መፍትሄ ይዞ ካልገባ ዳግም መቸገሩ የሚቀር አይመስልም። በተለይም ከተከላካይ መስመሩ ፊት በሚኖረው ቦታ ላይ አንድ ተከላካይ አማካይ እንደመጠቀሙ የፍፁም ዓለሙ ቀጥተኛ ሩጫዎች የቡድኑ ስጋት መሆናቸው አይቀርም። በዚህ ረገድ ተጋጣሚ ሜዳ ላይ የሚጀመሩ ጥቃቶችን በፍጥነት የማፈን ስራ ከአማካይ ከፍሉ የሚጠበቅ ወሰኝ ኃላፊነት ይሆናል። በማጥቃቱ ረገድ በብዙ የኳስ ቁጥጥር ሂደት ውስጥ ክፍተቶችን ፈልጎ የማግኘት የሁል ጊዜው የቡድኑ ጥረት ነገም ተጠባቂ ነው። ቡድኑ በዚህ ሂደት ውስጥ በተጋጣሚው የመሀል እና የመስመር ተከላካዮች መካከል ያለውን ክፍተት ዋነኛ ኢላማው እንደሚያደርግም ይገመታል። ከባህር ዳር የመከላከል ሽግግር መሳካት በፊትም ወሳኞቹን ከፍተቶች ማገኘት ከቡና ተሰላፊዎች የሚጠበቅ ጉዳይ ነው፡፡

ባህር ዳር ከተማ ነገ ከጊዮርጊሱ ጨዋታ አንፃር የማጥቃት ድፍረቱ ከፍ ብሎ ለጨዋታው እንደሚቀርብ ይጠበቃል። በዚህም በተለይም ከኳስ ጋር በሚሆንበት ወቅት ከግብ ክልሉ ለቀቅ ብሎ የሚጫወት የኋላ ክፍል ፣ የማጥቃት ተሳትፎ የሚኖራቸው የመስመር ተከላካዮች እና ለተጋጣሚ ሳጥን የተጠጋ የፊት መስመር እንደሚኖረው ይጠበቃል። ከተጋጣሚው ደካማ ጎን አንፃርም በድኑ በፈጣን ሽግግር ኳሶችን ወደ ፊት ማድረስን ምርጫው ሊያደርግ ይችላል። በዚህ ሂደትም የቡድኑ የፊት መስመር ተሰላፊ ባዬ ገዛኸኝም ሆነ ምንይሉ ወንድሙ ፍጥነታቸውን ተጠቅመው በሳጥን ውስጥ የመገኘት ጥሩ ብቃት ያላቸው መሆኑ ለቡድኑ ብርታት ሊሆነው ይችላል። ከእነሱ በተጨማሪ ዘግይተው ሳጥን ውስጥ በመድረስ አደጋ የሚጥሉ እንደ ሣላምላክ ተገኘ ዓይነት ተጫዋቾች ያሉት መሆኑም የሚረሳ አይደለም፡፡

ባህር ዳር የተለየ የመከላከል ሽፋን በማይሰጥባቸው እና በማጥቃት ሀሳብ ውስጥ ሆኖ ጨዋታዎችን በሚያደርግባቸው አጋጣሚዎች የሚታይበት የኋላ መስመር ክፍተቱ በነገው ጨዋታ ስጋት የሚሆንበት ደካማ ጉኑ ነው። ተከላካይ ሰንጣቂ ኳሶችን እንዲሁም ከመስመር የሚነሱ የጎል ዕድሎችን በማቆሙ ረገድ የወትሮው ጥንካሬው ላይ ያልተገኘባቸው የጨዋታ ቅፅበቶች ከተደገሙ ነገ ዋጋ ማስከፈላቸው አይቀሬ ነው። ከሳምሶን ጥላሁን ተደጋጋሚ ጉዳቶች በኋላ ከተከላካይ መስመር ፊት የአሰልጣኝ ፋሲል ተካልኝን ልብ የሚሞላ የሁለትዮሽ ጥምረት አለመገኘቱ ለዚህ ድክመቱ አንዱ መነሻ ሆኖ ሊወሰድ የሚችል ሲሆን ነገ የቦታው ተሰላፊዎች በቡና ፈጣሪ አማካዮች እንቅስቃሴ ላይ ትኩረት ሊያደርጉ መቻላቸው ደግሞ ከኃላው ያለውን ክፍተት ለጥቃት ይበልጥ ምቹ ሊያረገው ይችላል። ለዚህም መፍተሄ ይሆነው ዘንድ የቀሪዎቹ አማካዮች ታታሪነት በእጅጉ ያስፈልገዋል፡፡

በጨዋታው ኢትዮጵያ ቡና ያለምንም ጉዳት እና ቅጣት ወደ ሜዳ የሚገባ ሲሆን ባዬ ገዛኸኝን ከጉዳት መልስ የሚያገኘው ባህር ዳር ከተማ ግን ያላገገሙለትን ሳምሶን ጥላሁን እና አቤል ውዱን ግልጋሎት አያገኝም። ከዚህ በተጨማሪ ልምምድ የጀመረው ዜናው ፈረደም ለጨዋታው መድረሱ አጠራጣሪ ሆኗል።

የእርስ በእርስ ግንኙነት

– ሁለቱ ቡድኖች ለመጀመርያ ጊዜ በሊጉ የተገናኙት በ2011 የውድድር ዓመት ሲሆን አዲስ አበባ ላይ ኢትዮጵያ ቡና 5-0 ፣ ባህር ዳር ላይ ደግሞ ባህር ዳር ከተማ 1-0 አሸናፊ ሆነዋል።

ግምታዊ አሰላለፍ

ኢትዮጵያ ቡና (4-3-3)

ተክለማሪያም ሻንቆ

ኃይሌ ገብረትንሳይ – ወንድሜነህ ደረጄ – አበበ ጥላሁን – አስራት ቱንጆ

ታፈሰ ሰለሞን – አማኑኤል ዮሐንስ – ፍቅረየሱስ ተወልደብርሀን

አቤል ከበደ – አቡበከር ናስር – ሀብታሙ ታደሰ

ባህር ዳር ከተማ (4-2-3-1)

ጽዮን መርዕድ

ሚኪያስ ግርማ – ሰለሞን ወዴሳ – መናፍ ዐወል – አህመድ ረሺድ

ፍቅረሚካኤል ዓለሙ – አፈወርቅ ኃይሉ

ሳላምላክ ተገኝ – ፍፁም ዓለሙ – ግርማ ዲሳሳ

ምንይሉ ወንድሙ


© ሶከር ኢትዮጵያ