ቅድመ ዳሰሳ | ጅማ አባ ጅፋር ከ ወላይታ ድቻ

የሳምንቱን የመጨረሻ ጨዋታ የተመለከተው ዳሰሳችንን እነሆ።

ጅማ አባ ጅፋር የመጀመሪያ ድሉን ለማሳካት የሚያደርገውን ጥረት ወላይታ ድቻ ላይ ለማሳካት የነገውን ጨዋታ ይጠብቃል። ከተሳካለትም ከሰንጠረዡ ግርጌ የመላቀቅ ዕድል ይኖረዋል።

በምክትል አሰልጣኙ የሱፍ ዓሊ እየተመራ የሚገኘው ጅማ አባ ጅፋር በሁለት ጨዋታዎች ስድስት ግቦችን ያስተናገደ መሆኑ ስለመከላከል አደረጃጀቱ ሁሉንም ነገር የሚጠቁም ነጥብ ነው። በኋላ ክፍሉ ላይ የሚታይበት የመበታተን ችግር አሁንም አብሮት የሚኖር ከሆነ ከፍ ያለ ተነሳሽነት በሚታይባቸው የድቻ አጥቂዎች ዳግም መቀጣቱ የሚቀር አይመስልም። በማጥቃቱ ረገድም የተለየ መሻሻልን ያላሳየው ቡድኑ በአመዛኙ እንደ ሮባ ወርቁ ባሉ ተጫዋቾች የግል ጥረት ላይ ብቻ ተመስርቶ ይታያል። የመጨረሻ የግብ ዕድሎችን ከመፍጠር አንፃር ተቀይሮ ሲገባ የሚታይ ልዩነት ሲፈጥር የሚታየው ቤካም አብደላ ብቻ በደካማው የቡድኑ ጉዞ ውስጥ በበጎው መነሳቱን ቀሏል። ነገም ባለፉት ሁለት ጨዋታዎች ላይ ካሳየው ብቃት አንፃር የተሻለ የመጫወቻ ደቂቃ ሊያገኝ እንደሚችል ይጠበቃል።

ከአሰልጣኝ ዘላለም ሽፈራው መምጣት በኃላ መነቃቃት እየታየበት ያለው ወላይታ ድቻ ከስድስት ጨዋታዎች በኃላ ካሳካው ድል መልስ ጅማ አባ ጅፋርን ይገጥማል። ደካማ አቋም ላይ ከሚገኝ ቡድን ጋር መገናኘቱም አሸናፊነቱን ለማስቀጠል የሚረዳው እንደሚሆን ይገመታል።

ድቻ በጊዮርጊሱ ጨዋታ ካሳየው የበዛ ጥንቃቄ የተሞላበት ጨዋታ በተሻለ ከቡና ጋር የማጥቃት ፍላጎት የተመለከትንበት ሲሆን ነገ ደግሞ ይበልጥ በተጋጣሚው ሜዳ ላይ የመቆየት ድፍረትን ተላብሶ እንደሚቀርብ ይጠበቃል። ከአሰልጣኝ ዘላለም መምጣት በኋላ እንደየቡድኖቹ አጨዋወት አቀራረቡን እየቃኘ የሚገኘው ድቻ ለመስመር ተጫዛቾቹ ከፍ ያለ የማጥቃት ኃላፊነት ሰጥቶ እንደሚገባ የሚገመት ይሆናል። በነገው ጨዋታ ጅማ አባ ጅፋር በአብዛኛው ደቂቃ በራሱ ሜዳ ሊቆይ የሚችል በመሆኑ ከበስተኋላው ክፍት ቦታን ከሚተው ቡድን ጋር ጥሩ ብቃት ያሳዩት ቢኒያም ፍቅሬ እና ፀጋዬ ብርሀኑ ነገ በተለየ ተጋጣሚ ሌላ ፈተና የሚጠብቃቸው ይሆናል። በጥቅሉ ግን ወላይታ ድቻ ከተጋጣሚው እጅግ ተቃራኒ በሆነ የተነሳሽነት ደረጃ ላይ የሚገኝ በመሆኑ ጅማ ሊከተል የሚችለውን ጥንቃቄ አዘል አቅራረብ ለማስከፈት ሰፊ ዕድል እንዳለው ይታመናል።

በጨዋታው በጅማ አባ ጅፋር በኩል ያለውን የቡድን ዜና ለማግኘት ባንችልም ስንታየሁ መንግሥቱ ከጉዳት ያልተመለሰለት ወላይታ ድቻ እንድሪስ ሰዒድንም በ5 ቢጫ ካርድ ቅጣት መጠቀም እንደማይችል ማረጋገጥ ችለናል።

የእርስ በእርስ ግንኙነት

– ሁለቱ ቡድኖች በሊጉ ለአራት ጊዜያት ተገናኝተው ወላይታ ድቻ (አንድ ፎርፌ ጨምሮ) ሁለቱን ሲያሸንፍ በአንዱ አቻ ወጥተው ጅማ አባ ጅፋር አንድ አሸንፏል።

– በአራቱ ግንኙነት ስምንት ጎሎች (የድቻ ሦስት የፎርፌ ጎሎችን ጨምሮ) ሲቆጠሩ እኩል አራት አራት ግቦች አስመዝግበዋል።

ግምታዊ አሰላለፍ

ጅማ አባ ጅፋር (4-4-2)

ጃኮ ፔንዜ

ወንድምአገኝ ማርቆስ – መላኩ ወልዴ –ከድር ኸይረዲን – ኤልያስ አታሮ

ሱራፌል ዐወል – አብርሀም ታምራት – ንጋቱ ገብረሥላሴ– ሙሉቀን ታሪኩ

ሮባ ወርቁ – ብዙዓየሁ እንዳሻው

ወላይታ ድቻ (4-3-3)

መክብብ ደገፉ

ያሬድ ዳዊት – አንተነህ ጉግሳ – ደጉ ደበበ – አናጋው ባደግ

መሳይ ኒኮል – በረከት ወልዴ – ኤልያስ አህመድ

ቸርነት ጉግሳ – ፀጋዬ ብርሀኑ – ቢኒያም ፍቅሬ


© ሶከር ኢትዮጵያ