የ10ኛውን ሳምንት የመጨረሻ ቀን ቀዳሚ ጨዋታ የተመለከቱ ሀሳቦችን በዳሰሳችን ተመልክተናል።
ሀዋሳ ከተማ በሽንፈት ከጀመረው የውድድር ዓመት መሻሻልን አሳይቶ በቀጣዮቹ ስድስት ጨዋታዎች ነጥብ ሳይዝ ከሜዳ የወጣበት ጊዜ አልነበረም። ከጠንካራው ሀዲያ ሆሳዕና ጋር ያደረገው የመጨረሻ ጨዋታም ያለግብ የተጠናቀቀ ነበር። ከአምስት ቀናት ዕረፍት በኋላ ወደ ሜዳ የሚመለሱት ሀዋሳዎች ከከባዱ ጨዋታ በኃላ በቂ ዕረፍት ማግኘታቸው እና ጥሩ ሁኔታ ላይ ከማይገኘው አዳማ ጋር መገናኘታቸው ተጠቃሚ እንደሚያደርጋቸው ይታሰባል።
በመጨረሻዎቹ ሁለት ጨዋታዎች ግብ ያላስተናገደው የቡድኑ የኋላ ክፍል በተለያዩ የአደራደር ምርጫዎች ውስጥ ቢያልፍም ጥንካሬው እንዳለ ነው። በዚህ ረገድ በስድስት ጨዋታዎች ሦስት ግቦችን ብቻ ያስተናገደ የኃላ ክፍልን የሚገጥመው አዳማ ከተማ ካለበት ዕድሎችን የመፍጠር እና የተገኙትንም የመጨረስ ችግር አንፃር ነገ መቸገሩ የሚቀር አይመስልም። ከሆሳዕና ጋር በጉሽሚያዎች ተፈትኖ ያለፈው የኃይቆቹ አማካይ ክፍልም ነገ የተሻለ ክፍተቶችን በማግኘት በአመዛኙ በማጥቃት ላይ ያመዘነ እንቅስቃሴ እንደሚኖረው ይጠበቃል። ለዚህ ሂደትም እንደወትሮው ሁሉ ወደ ታጋጣሚው ሳጥን ውስጥ ለመድረስ ከሁለቱ መስመሮች የሚነሱ ኳሶችን እንደሚጠቀም ይጠበቃል።
አስከፊ የውድድር ዓመቱን መቀልበስ የተሳነው አዳማ ከተማ ነገም የተስፋ ጭላንጭልን ፍለጋ ወደ ሜዳ ይገባል። ካለበት የስብስብ ጥራት ደረጃ እና በማጥቃቱ ረገድ ካለበት ድክመት አኳያ ጥንቃቄ ላይ ያመዘነ አቀራረብ ይዞ መግባትን ምርጫው አለማድረጉ የሚያስገርመው አዳማ ነገም እንደወትሮው ክፍት ጨዋትን እንደሚያደርግ ይጠበቃል። ይህ አኳኋን ተጋጣሚው በመሰል የጨዋታ አቃራረብ ላይ ባገኛቸው ቡድኖች ላይ ይወስድ ከነበረው ብልጫ አንፃር አዳማን አደጋ ላይ ሊጥለው ይችላል። ከዚህ ሁኔታ ውስጥ ለአዳማ መልካም ሆኖ ሊታይ የሚችለው ከሜዳው አጋማሽ በኋላ የተሻለ ክፍተት የማግኘት ዕድሉ ሲሆን ቡድኑ በአግባቡ ይጠቀምበታል የሚለው ጉዳይ ግን አሁንም አጠራጣሪ ነው።
በተለይም እንደ ድሬዳዋው ጨዋታ ከተከላካዮች ጀርባ ሰፊ ክፍተቶች ከተገኘ እንደመስፍን ታፈሰ እና ብሩክ በየነ ዓይነት ፈጣን አጥቂዎች ላሉት ሀዋሳ ነገሮች ቀላል መሆናቸው አይቀርም። አዳማ በየጨዋታው ብቅ ብለው የሚጠፉ በፈጣን ሽግግር የሚገኙ የግብ ዕድሎች እና እንደ በቃሉ ገነነ ባሉ አማካዮች ከርቀት የሚደረጉ ሙከራዎች በጨዋታው ዕድል ሊሰጡት ይችላሉ። ይህን ለማድረግ ግን ሁለቱን መስመሮቹን በትጋት በመዝጋት የሀዋሳን ጥቃት መቆጣጠር እና ከራሱ ሜዳ በፍጥነት የሚወጣባቸውን ቅብብሎች መከወን የግድ ይለዋል።
በጨዋታው ሀዋሳ ከተማ ወንድማገኝ ማዕረግ እና ሀብታሙ መኮንን በጉዳት ምክንያት የማይጠቀም ሲሆን ቅጣት ላይ የሚገኘው አለልኝ አዘነም የመጫወት ፍቃድን አላገኘም። አዳማ ከተማ ደግሞ ጉዳት ላይ የነበሩት ታፈሰ ሰርካ እና ጀሚል ያዕቆብ ቀለል ያለ ልምምድ የጀመሩለት ሲሆን የረጅም ጊዜ ጉዳት ላይ የሚገኘው ሱሌይማን መሀመድ እና የኋላሸት ፍቃዱ ደግሞ በጉዳት የሚያጣቸው ተጫዋቾች ናቸው።
የእርስ በእርስ ግንኙነት
– ሁለቱ ቡድኖች አስካሁን 37 ጊዜ ተገናኝተው ሀዋሳ ከተማ 18 በማሸነፍ ቀዳሚ ሲሆን አዳማ ከተማ 8 ጊዜ ድል አድርጓል፡፡ በ11 አጋጣሚዎች ደግሞ አቻ ተለያይተዋል፡፡ ሀዋሳ 44 ጎሎች ሲያስቆጠር አዳማ ከተማ 36 አስቆጥሯል፡፡
ግምታዊ አሰላለፍ
ሀዋሳ ከተማ (4-3-3)
ሶሆሆ ሜንሳህ
ዳንኤል ደርቤ – ምኞት ደበበ – ላውረንስ ላርቴ –ደስታ ዮሃንስ
ኤፍሬም ዘካርያስ – ዳዊት ታደሰ – ወንድምአገኝ ኃይሉ
ኤፍሬም አሻሞ – መስፍን ታፈሰ – ብሩክ በየነ
አዳማ ከተማ (4-2-3-1)
ዳንኤል ተሾመ
ታፈሰ ሰርካ – ደስታ ጊቻሞ – ትዕግስቱ አበራ – እዮብ ማቲያስ
ሙጃይድ መሐመድ – ደሳለኝ ደባሽ
ፍሰሀ ቶማስ – በቃሉ ገነነ – በላይ አባይነህ
አብዲሳ ጀማል
© ሶከር ኢትዮጵያ