ሪፖርት | ወላይታ ድቻ አሸናፊነቱን አስቀጥሏል

በአስረኛው ሳምንት የመጨረሻ ጨዋታ ወላይታ ድቻ ጅማ አባጅፋርን 3-1 በሆነ ውጤት ማሸነፍ ችሏል።

ጅማ አባ ጅፋር ከቡናው ጨዋታ ተመስገን ደረሰ ፣ ሀብታሙ ንጉሴ እና ቤካም አብደላን በከድር ኸይረዲን ፣ አብርሀም ታምራት እና ሮባ ወርቁ ተክቷል። በድቻ በኩል ደግሞ መልካሙ ቦጋለ ፣ መሳይ አገኘው ፣ ነጋሽ ታደሰ እና ቢኒያም ፍቅሩ ጨዋታውን ሲጀምሩ ኤልያስ አህመድ ፣ ፀጋዬ አበራ ፣ ቸርነት ጉግሳ እና መሳይ ኒኮል አርፈዋል።

ሦስት ጎሎችን ባስመለከተን የመጀመሪያ አጋማሽ የጨዋታ እንቅስቃሴ በሁለቱም ቡድኖች በኩል የፈጣን ጥቃት ፍላጎት መኖሩ በግልፅ ቢታይም ሙከራዎች ግን በቶሎ አልተገኙም። በተሻለ ሁኔታ ወደ ተጋጣሚ የግብ ክልል በተደጋጋሚ ይደርሱ የነበሩት ድቻዎች የመጨረሻ ንክኪዎቻቸው ስኬት መውረድ ከሙከራ ሲያርቃቸው በርከት ብለው ወደ ተጋጣሚ ሜዳ ለመድረስ ይጥሩ የነበሩት ጅማ አባ ጅፋሮችም የድቻን የሦስትዮሽ የኃላ ክፍል ማለፍ ሳይችሉ ቆይተዋል። በዚህም በመጀመርያዎቹ ሠላሳ ደቂቃዎች ከቆመ ኳስ ውጪ የጠራ የጎል ዕድል ሳንመለከት ቀርተናል።

ይህ የጨዋታ ሒደት የተቀየረው 30ኛው ደቂቃ ላይ ሲሆን ደጉ ደበበ የመሳይ አገኘውን የማዕዘን ምት በግንባሩ በመግጨት አስቆጥሯል። ከዚህ በኃላ ድቻዎች የቀኝ መስመር ጥቃታቸው ይበልጥ አይሎ ሲታይ 33ኛው ደቂቃ ላይ በፀጋዬ ብርሀኑ አማካይነት በዚሁ አቅጣጫ ሌላ ሙከራም አድርገው ነበር።

33ኛው ደቂቃ ላይ የመጀመሪያ ኢላማውን የጠበቀ ሙከራ ያደረጉት አባ ጅፋሮች ግን 43ኛው ደቂቃ ላይ መላኩ ወልዴ ከርቀት አክርሮ መትቶ ባስቆጠረው ድንቅ የቅጣት ምት ጎል አቻ ሆነዋል። ሆኖም በመልሶ ማጥቃት በጅማ ሳጥን ውስጥ በፍጥነት የተገኙት ድቻዎች መሳይ አገኘው ከፀጋዬ ብርሀኑ የተቀበለውን ኳስ በጃኮ ፔንዜ እግር መሐል አሾልኮ ሲያስቆጥር ዳግም መሪ በመሆን አጋማሹን አጠናቀዋል።

ሁለተኛው አጋማሽ ሲጀምር ጅማ አባ ጅፋሮች በማጥቃቱ ረገድ ተሻሽለው የገቡ ይመስል ነበር። በመጀመሪያ ጥረታቸውም 46ኛው ደቂቃ ላይ ቤካም አብደላ በግራ መስመር ከተመስገን ደረሰ የተቀበለውን ኳስ ሞክሮ መክብብ ደገፉ አድኖበታል። ከዚህ በኋላ ግን የቡድኑ እንቅስቃሴ እየተገደበ መጥቶ ዳግም ለሙከራ ወደ ድቻ ሳጥን መድረስ ሲከብደው ተስተውሏል። በረጅሙ ወደ ግብ ይላኩ የነበሩ ኳሶችም በድቻ የከላካዮች ጥረት እየከሸፉ ጅማ አጋማሹን በጀመረበት ጉልበት መቀጠል ሳይችል ቀርቷል።

የተጋጣሚያቸውን መነቃቃት በቶሎ መቆጣጠር የቻሉት ድቻዎችም በመከላከሉ ረገድ ተሳክቶላቸው ውጤቱን አስጠብቀው ቢዘልቁም እንደመጀመሪያው የግብ ዕድሎችን እምብዛም አልፈጠሩም። ከጅማ የተከላካይ መስመር ጀርባ የነበረውን ክፍተት ለመጠቀም በፈጣን ጥቃት ለመግባት ሲጥሩ ቢታዩም የግብ ልዩነቱን ማስፋት የሚያስችሉ አስፈሪ ሙከራዎችን አላደረጉም። ሆኖም 80ኛው ደቂቃ ላይ በዛሬው ጨዋታ ስኬታማ የቆሙ ኳሶችን ሲያደርስ የዋለው መሳይ አገኘሁ ከማዕዘን ምት ያሻማውን ኳስ ራሱን ነፃ አድርጎ የቆመው ተከላካዩ አንተነህ ጉግሳ በግንባሩ በመግጨት አስቆጥሯል። ጨዋታውም ሌላ ግብ ሳያስተናግድ በድቻ 3-1 አሸናፊነት ተጠናቋል።




© ሶከር ኢትዮጵያ