ሪፖርት | አብዲሳ ጀማል በደመቀበት ጨዋታ አዳማ ከተማ የዓመቱን ሁለተኛ ድል አስመዝግቧል

በቤትኪንግ የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ 10ኛ ሳምንት የረፋድ ጨዋታ ከመጀመርያው ሳምንት በኋላ ድል ማስመዝገብ ተስኖት የቆየው አዳማ ከተማ በአብዲሳ ጀማል ሐት-ትሪክ ሀዋሳን 3-1 በመርታት ነጥቡን ከፍ አድርጓል።

ሀዋሳ ከሀዲያ ነጥብ ከተጋራው ስብስብ ሦስት ለውጦችን በማድረግ አዲስዓለም ተስፋዬ ፣ ጋብሬል አህመድ እና ሄኖክ ድልቢን በመጀመሪያ አሰላለፍ ተጠቅሞ ዳንኤል ደርቤ ፣ ዳዊት ታደሰ እና ኤፍሬም ዘካርያስን አሳርፏል። በአዳማ ከተማ በኩል ቡድኑ በድሬዳዋ ከተሸነፈበት ጨዋታ የአሞስት ተጫዋቾች ለውጥ በማድረግ ታሪክ ጌትነት ፣ አካሉ አበራ፣ ታፈሰ ሰርካ፣ ቴዎድሮስ ገብረእግዚአብሄር እና ፍስሀ ቶማስ በመጀመርያ አሰላለፉ ተካተዋል።

እንዳለፉት ጨዋታዎች ሁሉ በሀዋሳ ፈጣን የማጥቃት እንቅስቃሴ በተጀመረው ጨዋታ በሁለተኛው ደቂቃ ከማዕዘን የተሻገረውን ኳስ ምኞት ሞክሮ ትዕግስቱ ያወጣበት ሙከራ ሀዋሳን መሪ ለማድረግ የተቃረበች ነበረች። ከሙከራው በኋላ በተሻለ የጨዋታ ፍላጎት የዛሬውን ጨዋታ ያደረጉት አዳማ ከተማዎች በተደራጀ መከላከል እና የመልሶ ማጥቃት ከሀዋሳ ተሽለው ታይተዋል። ከሀዋሳ ተከላካዮች ጀርባ በሚጥሏቸው ኳሶችም ጥቃት ሰንዝረዋል። በዚህም በ24ኛው ደቂቃ ከቴዎድሮስ ገብረእግዚአብሄር የተነሳውን ኳስ አብዲሳ ጀማል በምርጥ አጨራረስ ቡድኑን ቀዳሚ አድርጓል።

ከአዳማ መሪነት በኋላ በቀሪው የመጀመርያ አጋማሽ ደቂቃዎች ብዙም የሚጠቀስ ሙከራ እና የማጥቃት አጋጣሚዎች ያልተፈጠሩ ሲሆን አዳማዎች የሀዋሳ የኳስ ቁጥጥር አደጋ ሳይፈጥርባቸው የመጀመርያውን አጋማሸ በመሪነት አጠናቀውል።

ከእረፍት በፊት እጅግ የተቀዛቀዘው ሀዋሳ ከእረፍት. መልስ በመጀመርያዎቹ ደቂቃዎች ተነቃቅቶ ጨዋታውን የጀመረ ሲሆን በተጋጣሚ የሜዳ ክፍል አመዝኖ በመጫወት ጫና ፈጥሮ ተጫውቷል። በ55ኛው ደቂቃም ኤፍሬም አሻሞ በአካሉ አበራ የተሰራበትን ጥፋት ተከትሎ የተሰጠውን የፍፁም ቅጣት ምት ብሩክ በየነ አስቆጥሮ አቻ ሆነዋል።

ከአቻነቱ ጎል በኋላ አዳማዎች በቶሎ ወደ መሪነት ለመመለስ ጊዜ አልፈጀባቸውም። በድጋሚ ጎል አስቆጥሮ ወደ መሪነት ለመሸጋገር አልመው ሲንቀሳቀሱ የነበሩት ሀዋሳዎች ክፍተትን በሚገባ የተጠቀመው ቡድኑ ከሰባት ደቂቃዎች በኋላ በድጋሚ መሪ ሆኗል። 62ኛው ደቂቃ ላይ በላይ ዓባይነህ በመልሶ ማጥቃት በቀኝ መስመር በኩህ የተቀበለውን ኳስ በግራ የሳጥኑ ክፍል ነፃ አቋቋም ላይ ለነበረው አብዲሳ ጀማል አሻግሮለት አብዲሳ በቀላሉ አስቆጥሯል።

ጨዋታው በሚፈልጉት መንገድ የተጓዘላቸው አዳማዎች ተጨማሪ ጎል የሚሆን እድል 66ኛው ደቂቃ ላይ በአብዲሳ አማካኝነት ፈጥረው አጥቂው አክርሮ የመታው ኳስ የውጪኛውን መረብ ታኮ ወጥቶበታል። በ74ኛው ደቂቃ ደግሞ አብዲሳ ጀማል የአዳማን ድል ይበልጥ ያረጋገጠ ጎል ከታፈሰ ሰርካ ተመቻችቶለት በግንባሩ በመግጨት አስቆጥሯል። ይህ ጎል ለቀድሞ የነገሌ አርሲ አጥቂ ሐት-ትሪክ ሆኖም ተመዝግቧል።

ጨዋታው ከተጠበቀው በተቃራኒው የሆነባቸው የሚመስሉት ሀዋሳዎች ለተቆጠረባቸው ጎሎች የሰጡት ምላሽ ደካማ የነበረ ሲሆን ዓባይነህ ፊኖ በ86ኛው ደቂቃ ከግማሽ ጨረቃ አካባቢ መትቶ የጎሉ አግዳሚ ከመለሰበት ሙከራ ውጪ የተለየ ነገር ሳይፈጥሩ ጨዋታው በአዳማ የበላይነት ተጠናቋል።


© ሶከር ኢትዮጵያ