በአራተኛው ክፍል የጨዋታ ሳምንቱ ዐበይት ጉዳያችን ሌሎች ትኩረት ያገኙ ጉዳዮችን ተመልክተናል።
👉በቀይ ካርድ የተሰናበቱት የመጀመሪያው የህክምና ባለሙያ?
በ10ኛ ሳምንት የቤትኪንግ የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ አዳማ ከተማ ሀዋሳ ከተማ 3-1 በረታበት ጨዋታ በእግርኳስ ጨዋታዎች ላይ እምብዛም ያልተለመደ እንግዳ ክስተትን ተመልክተናል። በእግርኳስ ጨዋታዎች ላይ ተጫዋቾች ፣ የአሰልጣኝ ቡድን አባላት አልያም አልፎ አልፎ ኳስ አቀባዮች ያልተገባ ድርጊትን ሲፈፅሙ ጨዋታውን በሚመሩት ዳኞች በቀይ ካርድ ሲሰናበቱ መመልከት የተለመደ ክስተት ነው። ታድያ በሀዋሳ እና አዳማ ጨዋታ ላይ የተመለከትነው ግን ከሁሉም የተለየ ነው።
በጨዋታው የመገባደጃ ደቂቃዎች አዳማ ከተማ 3-1 እየመራበት በነበረበት ቅፅበት የአዳማ ከተማው ተጫዋች እዮብ ማቲዎስ ተጎድቻለው ብሎ በወደቀበት እና ጨዋታው በተቋረጠበት ቅፅበት የህክምና እርዳታ ለማድረግ ወደ ሜዳ የገቡት የአዳማ ከተማው የህክምና ባለሙያ ግን ጨዋታውን ከመሩት የመሐል ዳኛ ባደረጉት የቃላት ልውውጥ በሁለት ቢጫ ካርድ ከሜዳ ለመወገድ በቅተዋል።
ይህን ውሳኔ ተከትሎ በተቀሩት ደቂቃዎች የአዳማ ከተማ ተጫዋቾች ጉዳት ቢያስተናግዱ የህክምና አገልግሎት በምን መልኩ ሊያገኙ ይችላሉ የሚለው ጉዳይ በትኩረት ቢጠበቅም የተጠበቀው ነገር ሳይከሰት ጨዋታው ሊጠናቀቅ ችሏል።
👉 የተሻሻለው የኳስ አቀባዮች የሥራ ዝግጁነት
በሀገራችን በሚደረጉ የእግር ኳስ ውድድሮች ላይ ጥቃቅን ለሚመስሉ ጉዳዮች የሚሰጠው ትኩረት ማነስ ተከታይ ጥፋቶችን ሲያስከትል እና መነጋገሪያ ሲሆን ይታያል፡፡ ከዚህ በተለየ ደግሞ በአንዳንድ ጉዳዮች ላይ የሚታዩ መሻሸሎች ቀጣይነት እንዲኖራቸው ማበረታታት የግድ ይላል፡፡ ከእነዚህ ውስጥም በጅማ ዩኒቨርስቲ ስታድየም እየተካሄደ ባለው የቤት ኪንግ ፕሪምየር ሊግ ጨዋታዎች ላይ እየታየ ያለው የኳስ አቀባዮች ትጋት የሚጠቀስ ነው፡፡
ከዚህ ቀደም የአለባበስ ንጽህናን ባለመጠበቅ ፣ ሰዓት የሚገሉ ቡድኖችን ኳስ በማዝግየት በመተባበር እና በመሳሰሉ ጉዳዮች ይታሙ የነበሩት ታዳጊዎች ጅማ ላይ ጥሩ የሥራ አፈጻፀም እያሳዩ ይገኛሉ፡፡ ይህ መልካም ውጤት እንዲመዘገብም አዲስ አበባ ላይ ይህንን ስራ ከሚያከናውኑ ወጣቶች መሀል አንዱ ሥልጠና ወስዶ በጅማ ለሚገኙት አቻዎቹን እንዲያስተምር መደረጉ እና በሥራ ላይ ሳሉም ቅርብ ክትትል የሚደረግላቸው መሆኑ አስተዋፅኦ አለው፡፡ በዚህ ሳምንት ሀዋሳ እና አዳማ ባገናኘው ጨዋታም ላይ የታዳጊዎቹ ማልያ ከአዳማ ተጫዋቾች ጋር መመሳሰሉን ተከትሎ ማለያቸውን እንዲለውጡ የተደረገበት መንገድ ይበል የሚያሰኝ ነው፡፡
👉ማርፈድ ቦታ በሌለው ሙያ የሚያረፍዱት የቀይ መስቀል አባላት
በጅማ ዩኒቨርስቲ ስታዲየም የመጀመሪያ የህክምና እርዳታ ለመስጠት የተመደቡት የቀይ መስቀል አባላት ባልተለመደ መልኩ ሲዳማ ቡና ከቅዱስ ጊዮርጊስ እንዲሁም ወላይታ ድቻ ከጅማ አባጅፋር ባደረጉት ጨዋታ ላይ ከጨዋታው መጀመር በኃላ ወደ ስታዲየም የመድረሳቸው ነገር ትኩረትን የሚስብ ነበር።
የሰከንዶች መዘግየት እና መፍጠን በትልቁ የሰው ልጅ ጤንነት እና ደህነት ላይ ለውጥ በሚያመጣበት በዚሁ ጊዜ ወሳኝ በሆነበት የሙያ መስክ የተሰማሩ የቀይ መስቀል አባላት ዘግይተው ወደ ጨዋታ ሜዳ መድረሳቸው አይበለው እና ክፉ ነገር ተከስቶ ቢሆን ሊደርስ የሚችለውን ጉዳት ከግምት ላስገባ መሰል ቸልተኝነት የተሞላባቸው ድርጊቶች ሊታረሙ ይገባል።
👉በፌዴሬሽኑ እና በአክሲዮን ማኅበሩ መካከል የሚና መደበላለቅ
ከጥቂት ቀናት በፊት ሰበታ ከተማ ከባህር ዳር ከተማ ያደረጉትን ጨዋታ የመሩት ሁለት አርቢትሮች በአክሲዮን ማኅበሩ የቅጣት እርምጃ የተወሰደባቸው ቢሆንም ከፌደሬሽኑ በወጣ ይፋዊ ደብዳቤ ቅጣት የመጣል እና የማሳወቅ ስልጣን ያለው ፌዴሬሽኑ መሆኑ መገለፁ በሳምንቱ ብዙ ሲያነጋግር የነበረ ጉዳይ እንደነበር አይዘነጋም።
አክሲዮን ማኅበሩ ሊጉን ለማስተዳደር ከተረከበ ወዲህ በፌዴሬሽኑ እና በአክሲዮን ማኅበሩ መካከል የሚና መደበላደቅ ስለመኖራቸው እየታዘብን እንገኛለን። ሊጉ ራሱን ከቻለ ገና ሁለት ዓመታት ያልደፈነ ከመሆኑ አንፃር አሉታዊ አስተያየቶች ለመስጠት ገና ቢሆንም በቀጣይ ግን ፌዴሬሽኑን የሚመለከቱ የዲሲፕሊን፣ የዳኝነት እና የመሳሰሉ ጉዳዮች እና ሊጉን የሚያስተዳድረው ኩባንያ የሚመለከታቸውን ጉዳዮች በመለየት ብሎም በጋራ ማከናከወን የሚገባቸውን ተግባራት በጋራ የመሥራት የቤት ሥራ ከሁለቱም አካላት የሚጠበቅ ነው።
👉 የስታዲየም ውስጥ የድምጽ ማጉያዎች ጉዳይ
ከዚህ ቀደም አዲስ አበባ ላይ በነበረው የቤት የኪንግ ኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ ጨዋታዎች ወቅት ያነሳነው የስታድየሞች የድምጽ ማጉያዎች ችግር በጅማም ተደግሞ ተመልክተናል፡፡ ጅማ አባ ጅፋር እና ወላይታ ድቻን ባገናኘው የሳምንቱ መጨረሸ ጨዋታ መጀመሪያ ላይ ከዚህ ዓለም በሞት ለተለየው የአባ ጅፋር ደጋፊ ይታገሱ ኃይለሚካኤል የተደረገው የህሊና ጸሎት ጉዳዩን ለተረዱትም ሆነ ስለምን የህሊና ጸሎት እየተደረገ እንደሆነ ላላወቁ ሰዎች ገለጻው ሳይሰማ ቀርቷል፡፡ አምስተኛው ሳምንት ላይ የዌ ደማም ዘርፉ ወልዴ ተብለው ይጠሩ ለነበሩት የሀገር ሽማግሌ የህሊና ፀሎትም እንዲሁ መታለፉ የሚዘነጋ አይደለም።
ከጅማ አባ ጅፋር ደጋፊነቱ ባሻገር በወርልድ ቴኳንዶ ስፖርት ተወዳዳሪነት እና አሰልጣኝነት ይታወቅ የነበረው ይታገሱ ኃ/ሚካኤል በርካታ የሀገር ውስጥ ውድድሮች ላይ ተካፍሎ ከማሸነፉም በተጨማሪ ሀገሩ ኢትዮጵያን በስፖርቱ ወክሎ መወዳደርም ችሎ ነበር። ሶከር ኢትዮጵያም በወጣቱ ህልፈት የተሰማትን ሀዘን እየገለፀች ለወዳጅ ዘመዶቹ መፅናናትን ትመኛለች።
© ሶከር ኢትዮጵያ