የአሰልጣኞች አስተያየት | ሲዳማ ቡና 0-5 ኢትዮጵያ ቡና
ሱፐር ስፖርት ከጨዋታው መጠናቀቅ በኃላ ከአሰልጣኞች ጋር ያደረገው ቆይታ ይህንን ይመስላል።
አሰልጣኝ ዘርዓይ ሙሉ – ሲዳማ ቡና
ዛሬ ቡድናችን ከመጀመሪያው እስከመጨረሻው ጥሩ አልነበረም። በተለይ ተከላካዮቻችን በጣም ይሸሹ ነበር። እኔ ካልኩት ውጪ ነው ሲጫወቱ የነበሩት። ያንን ለማስተካከል ሞክረናል። ግን ያው በተፈጥሮ ፍጥነት ስለሌላቸው የግድ ይሸሻሉ። የቡናን ተጫዋቾች እየጋበዙ ነበር። በዚህ የተነሳ አሸፋፈንም ችግር ስለነበር በተደጋጋሚ በእነሱ ግራ በእኛ በቀኝ በኩል በሚመጡ ኳሶች ነው የተጠቀሙት። በዛ በኩል የሚጫወተው አማኑኤል ዛሬ የአቋቋም ችግር ነበረበት። ታይሚንጉን የጠበቀ አካሄድ አይደለም የሄደው። የእኛ አጨዋወት ያመጣው ነገር ነው። ተነሳሽነትም ይጎል ነበር። በተለይ ጎሎች ሲገቡ እየወረዱ ነው የሄዱት። ያው ኳስ ላይ ያጋጥማል ግን የምንፈልገውን ጨዋታ ለመጫወት አልቻልንም። እነሱ ግን ተሳክቶላቸዋል።ጥሩ ነበሩ ውጤቱም ይገባቸዋል።
ቡድኑን ይበልጥ ስላወረደው ጎል
በተለይ ሁለተኛው ኳስ የእኛን ቡድን ያወረደው ይመስለኛል። ምክንያቱም ለእኔ ባይታየኝም የመጀመሪያው ፔናሊቲ ለእኔ አልታየኝም ፤ ግን ቀረብ ብዬ ሳይ ፔናሊቲ አይደለም። ያ ኳስ አወረደን። ከዛ ሁለተኛው ጎል ሲገባ ደግሞ እየወረዱ ነው የመጡት። ዞሮ ዝሮ ዳኝነቱን በኋላ የምናየው ቢሆንም እርግጠኛ አይደለሁም ፤ ግን እነዛ ኳሶች ናቸው። እርግጠኛ አይደለሁም ግን በፊቱ ያገኘው ነው የሚመስለኝ። ዞሮ ዞሮ ሆኗል ፤ ያ ሰበብ ባይሆንም። እነዛ ናቸው በእንቅስቃሴ ለውጥ ያደረጉት። ልጆች ቀይረን ለማስገባት ሞክረናል። ተቀይረው የገቡትም ጥሩ አልነበሩም። ብቻ ዞሮ ዞሮ ቡድናችን ጥሩ አልነበረም ዛሬ።
አሰልጣኝ ካሳዬ አራጌ – ኢትዮጵያ ቡና
ወደ መሀል ሜዳ ተጠግተው መከላከላቸው ሲዳማ ላይ ስለፈጠረው ተፅዕኖ
ሁሌም እንደምለው ከኃላ ያሉት የእኛ ተጫዋቾች እንቅስቃሴ ውስጥ ስለሚሳተፉ የተከፈቱ ቦታዎችን ተጋጣሚ እንዳይጠቀም መሀል ላይ ያሉ ልጆች ጫን ብለው መጫወት አለባቸው። አንዳንዴ በትክክል ስለማንተገብረው ነው። ያ ጥቅሙ አንደኛ እዛው ውስጥ ኳሱን ልናገኝ እንችላለን። ሁለተኛ እነሱ ፊት ላይ ያለውን ተጫዋች በቀላሉ እንዳያገኙ ይረዳናል። እና አስተዋፅዖ አለው።
ስለመስመር ተጫዋቾች እንቅስቃሴ
ጥሩ ነው ግን የተከፈቱ ቦታዎች የት ናቸው ? ነፃ ሰው የሚተዉልን የት ጋር ነው ? የሚለውን ታሳቢ አድርገን ያን ለመጠቀም ነው። የሰጡንን ክፍት ቦታ መጠቀም የሚገባንን ያህል አልተጠቀምንም። ግን በተከፈተው ቦታ የሄድናቸው ኳሶች ወደ ግብነት መቀየር ችለዋል።
ስለአቡበከር ናስር ብቃት
አጥቂዎች የተመቸ ኳስ ማግኘታቸው ከሂደቱ ጋር የተያያዘ ነው። ስለዚህ ሂደቱ የተሳካ ከሆነ አጥቂዎች የተመቸ ኳስ ያገኛሉ። የተመቸ ማለት ተጋጣሚን የሚቆጣጠሩበት ጎሉን ማየት የሚችሉበት ማለት ነው።
ስለሜዳው ጥራት ተፅዕኖ
ሜዳው ምንም ጥያቄ የለውም። ለሁሉም ቡድን ተፅዕኖ ያደርጋል። ጥሩ ሜዳ ከሆነ በሜዳ ምክንያት የምታጣውን ነገር በጥሩ ሜዳ ልታገኘው ትችላለህ። ይህ ከተመቻቸ አጥቂዎች ብዙ ጎል ማስቆጠር ይችላሉ። ለአቡበከርም እንደቡድን ያን የተመቻቸ ነገር ለመፍጠር ነው እና ከተመቻቸለት በግሉ ደግሞ በደንብ ጨዋታውን አይቶ ድርጊቱን መጨረስ የሚያስችል አቅም ያለው ተጫዋች ነው።